ምክር ቤቱ ከቲኤምኢኤ ጋር የንግድ ሥራ አመቺነትን ለማቀላጠፍ በሚያስችለው የትብብር ማዕቀፍ ላይ ተወያየ

የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ የሱፍ አደምኑር ትሬድማርክ ኢስት አፍሪካ የተባለን ድርጅት ወክለው የመጡ አራት አባላትን የያዘውንና በሚካኤል ሚቴይ የድርጅቱ አይሲቲ ለንግድና ትራንስፖርት ፋሲሊቴሽን ዳይሬክተር የተመራውን ልዑካን ቡድን ጥር 7 ቀን 2012 ዓ.ም. በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡

የጉብኝቱ ዓላማ ከምክር ቤቱ ጋር የንግዱን ማኅበረሰብ የንግድ ሥራ አመቺነትን (trade facilitation) አሠራር መዘርጋት የሚያስችል የድጋፍ ትብብር ለማድረግ ነው፡፡ ድርጅቱ በተለይ ለምሥራቅ አፍሪካ የግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሾች የአይሲቲ ሥርዓትና ሥርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዳውን መሠረተ ልማት በመዘርጋት፣ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በመሥጠትና አገልግሎቶችን ቀላል፤ ተገማች፤ ቀልጣፋና ፈጣን የሚያደርጉ አሠራሮችን የተመለከቱ ድጋፎችን በማድረግ በዓለም አቀፉ የንግድ ምህዳር ውስጥ የመጠቀም ዕድላቸውን ለማሳደግ በእጅጉ እየሠራ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ የሱፍ አደምኑር ሀሳቡ እንዳስደሰታቸው ገልጸው በዚህ ረገድ ምክር ቤቱ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ጠቁመዋል፡፡ እንደ ዋና ጸሐፊው ገለጻ የምክር ቤቱን አገልግሎት ቀልጣፋ ለማድረግ ይረዳ ዘንድ የምክር ቤቱን የኤሌክትሮኒክ አንድ መስኮት እና የአምራች ሀገር የምስክር ወረቀት (certificate of origin) አሠራርን ማዘመን፣ የመረጃ አሰጣጥና የሥልጠና አገልግሎትን ማመቻቸትና የድረ-ገጽ ማበልጸግን የመሳሰሉ አገልግሎቶች ትብብር ማድረግ ከሚፈልጉባቸው ነጥቦች ዋነኞቹ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

የግሉ ዘርፍ ተወካይ እንደመሆኑ ምክር ቤቱ ዋነኛው የቢዝነስ መረጃ ምንጭ መሆን ይፈልጋል የሚሉት የሱፍ በንግግራቸው ለንግዱ ማኅበረሰብ ፈጣንና ቀልጣፋ የገበያ መረጃና ሌሎች ተዛማጅ አገልግሎቶችን ለመስጠት የምክር ቤቱን የኤሌክትሮኒክ አንድ መስኮት አገልግሎት የማዘመን አስፈላጊነትን አስምረውበታል፡፡ ለምክር ቤቱ ሠራተኞችና አባል ምክር ቤቶችም ስልጠናዎችን ማመቻቸትን በተመለከተ የቲኤምኢኤ የድጋፍ ትብብር ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም የትብብር ማዕቀፍ መንደፉ አስፈላጊ በመሆኑ የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ወደ ሥራ መግባት እንደሚቻልም መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡

ተቀማጭነቱን ኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ያደረገው ቲኤምኢኤ በየንግድ ሥራ አመቺነት በዓለም ግንባር ቀደም ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ስኬታማ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑም ታውቋል፡፡

መዲናችን የመጀመሪያውን የጎዳና ላይ ትርዒት ልታስተናግድ ነው

‹‹ዋን አፍሪካ ካርኒቫል›› በሚል መሪ ቃል በአፍሪካ የመጀመሪያውን የጎዳና ላይ ትርዒት (ካርኒቫል ፌስቲቫል) በአዲስ አበባ ለማካሄድ ዕቅድ እንዳለ የአይ. ጂ. ኢንተርቴይንመንት ባለቤትና የዝግጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ይስሀቅ ጌቱ ገለጹ፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ ይህን የተናገሩት ጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት መልአኩ እዘዘው (ኢንጂነር) ጋር በፕሬዚደንቱ ጽ/ቤት በዝግጅቱ ዙሪያ በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡

በዕለቱ ከኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ከቱሪዝም ኢትዮጵያና ከግል ድርጅቶች የተውጣጡ ሰባት አባላትን የያዘ ልዑካን ቡድን ከፕሬዚደንቱ ጋር በዝግጅቱ ዓላማና ከምክር ቤቱ ጋር በጋራ በሚሰሩ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርጓል፡፡ የዝግጅቱ ዓላማ የአፍሪካን ባህል፣ ታሪክ፣ ንግድና ኢንቨስትመንት ትሥሥር በማበረታታት በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ለማስተዋወቅ እንደሆነ የዝግጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ይስሀቅ ገልጸዋል፡፡

ቀደም ሲል አፍሪካን የሚመጥን የጋራ መድረክ ኖሮ አያውቅም የሚሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ 15 ቀናት ያህል እንደሚቆይ በሚጠበቀው ዝግጅት የመጀመሪያ ቀን የጎዳና ላይ ትርዒት እንደሚካሄድና በቀሩት ቀናት 54ቱም የአፍሪካ ሀገሮች ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበትና የሚሸጡበት ኤግዚቢሽንና ባዛር እንዲሁም አፍሪካዊ ባህሎችና ታሪኮች የሚተዋወቁበት ዝግጅት በግዮን ሆቴል ለህዝብ እንደሚታይ አብራርተዋል፡፡

ሀገራችን ዘርፈ ብዙ የሆኑ እምቅ ሀብቶቿን ወደ ገንዘብ ያልቀየረች ሀገር መሆኗን በአጽንዖት የተናገሩት የምክር ቤቱ ፕሬዚደንት ኢንጂነር መልአኩ እንደተናገሩት እንደ ቡናና ሰሊጥ ያሉ ጥሬ ምርቶችን በቅናሽ ዋጋ ወደ ውጭ እየላክን በምትኩ የኛኑ ምርት እሴት ተጨምሮበት ከእጥፍ በላይ በሆነ ዋጋ መልሰን እንሸምታለን ካሉ በኋላ እንዲህ ዓይነቱ ዝግጅት ሀብታችንን በአግባቡ ለመጠቀም ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

ዝግጅቱ ለሀገራችን ብሎም ለአህጉራችን አዲስ የቢዝነስ እይታ እንደመሆኑ በጋራ መሥራቱ ጅማሮው እንዲያምር ስለሚያደርግ ምክር ቤቱ በዚህ ረገድ የድርሻውን እንደሚወጣም ተናግረዋል፡፡ በቆይታው በየዕለቱ ከ10 ሺ በላይ ጎብኚዎች እንደሚገኙ የሚገመት ሲሆን ዝግጅቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል ተብሎለታል፡፡ የፊታችን የካቲት 21 ቀን 2012 ይጀመራል ተብሎም ቀጠሮ ተይዞለታል፡፡

አይ. ጂ. ኢንተርቴይንመንት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከአ/አ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ከቱሪዝም ኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር በመተባበር እንደሚያዘጋጀውም ታውቋል፡፡

የኤሌክትሮኒክስ አንድ መስኮት አገልግሎት አሠራሮችን ያቀላጥፋል ተባለ


የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን ጨምሮ 16 መስሪያ ቤቶች የኢትዮጵያ ኤሌክትሮኒክስ አንድ መስኮት አገልግሎትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን፤ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በተገኙበት ታህሳስ 25/2012 ዓ.ም ስራውን በይፋ አስጀምረዋል፡፡ አገልግሎቱ በአገሪቱ በተለያዩ መስሪያ ቤቶች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ቀላል፤ ተገማች፤ ቀልጣፋና ፈጣን ያደርገዋልም ተብሏል፡፡

አሰራሮችን ወረቀት አልባ በማድረግ አለም አቀፍ የንግድ ስርዓትና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጠዉ ይህ ስርዓት አገራዊ ገቢን በማሳደግ፤ወጪን የሚቆጥብና የአገልግሎት አሰጣጥ ግዜን የሚቀንስ ከመሆኑም በላይ አሰራሩ ሙስናን በመቀነስ የደንበኞች እርካታን ይጨምራል፤ አለም አቀፍ ንግድን በማበረታታት ግልፅነትን ያሰፍናል፤ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን ጨምሮ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የንግድና ኢንዱስቴር ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር፣የትራንስፖርት ሚኒስቴር፣የመዓድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣የኢትዮጵ ብሄራዊ ባንክ፤ የጉምሩክ ኮሚሽን፤የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፤ የኢትዮጵያ መረጃና መረብ ደህንነት ኤጄንሲ ጨምሮ በአጠቃላይ በመጀመሪያዉ ዙር 16 የግልና የመንግስት ተቋማት ስራውን ለማስጀመር የሚስችል ስምምነትተፈራርመው ወደስራ ገብተዋል፡፡

ምክር ቤቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አዘጋጀ


የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ዘርፍ ያሉ የኢንቨስትመንት አቅሞች፣ ዕድሎች እና ተግዳሮቶችን አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ታህሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. በኢሊሌ ሆቴል አካሄደ፡፡

ምክር ቤቱ ከሚሰራቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል አንዱ የንግድና ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት ስራ መሆኑን በመጥቀስ የኢንቨስትመንት ማስፋፋፊያ ስራውን ለመስራት ያሉትን ምቹ ሁኔታ፣ አማራጮች እና ድጋፎች የአገር ውስጥ ባለሀብቱን ግንዛቤ ማሳደግ ነው፡፡

ከዚህ በፊት በአዋሳና በኮምቦልቻ ተመሳሳይ የግንዛቤ መፍጠሪያ ስልጠናዎች በምክር ቤቱ መሰጠቱን ያስታወሱት የምክር ቤቱ ም/ዋና ፀሀፊ አቶ ውቤ መንግስቱ መድረኩ በጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ዘርፍ ያሉትን የኢንቨስትመንት አማረጮች እና ተግዳሮቶች በማሳወቅ እና ለእነዚህም ችግሮች መፍትሄ በሚሰጡባቸው መንገዶች ላይ በመወያየት ተሳታፊዎች ለራሳቸው ተጠቅመው ለሌሎችም እነዲጠቀበት የማድረግ ስራ ለመስራት እንዲቻል ነው ብለዋል፡፡በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ በኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ዘርፍ ያሉ የኢንቨስትመንት አቅሞች፣ ዕድሎች እና ተግዳሮቶች እንዲሁም በቅርቡ በኢትዮጵያ የሚካሄደውንእና በጨርቃጨርቅ ማሽነሪዎች እና ተያያዥ ሁነቶች ላይ የሚያተኩረውን የ ITME Africa 2020 ኤክስፖን አስመልክቶ ገለፃዎች የተደረጉ ሲሆን፤ ይህን ተከትሎ በተሳታፊዎች በተነሱ በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ ውይይት ተካሂዷል ፡፡


ምክር ቤቱ ከፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈራረመ

የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና የኢፌዲሪ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በትብብር ለመስራት ታህሳስ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. በምክር ቤቱ አዳርሽ የጋራ ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ ለማከናወን የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡ ስምምነቱ የተፈረመው በምክር ቤቱ ዋና ፀሀፊ አቶ የሱፍ አደምኑር እና በኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ አለበል ደሴ ነበር፡፡

የመግባቢያ ሰነዱ ስምምነት ዋና ዓላማ ሁለቱ ተቋማት የንግዱ ማህበረሰብ የሚያጋጥሙትን ፈታኝ ችግሮች በመለየት እና በጥናትና ምርምር በማስደገፍ ለፖሊሲ አውጪ የመንግስት አካላት የመፍትሄ ሀሳብ ለማቅረብ በሚያስችል ሁኔታ በትብብር ለመስራት ነው፡፡

በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ አቶ የሱፍ አደምኑር እንደተናገሩት ምክር ቤቱ ከሚሰራቸው ንግድና ኢንቨስትመንት የማስፋፋት፣ የአቅም ግንባታና ስልጠና የመሳሰሉት አበይት ተግባራት መካከል የንግዱን ማህረሰብ መብትና ጥቅም ከማስከበር እና ምቹ የንግድ ከባቢ ለመፍጠር ከመስራት አንፃር የንግድና ኢንቨስትመንትን የሚመለከቱ ፖሊሲዎች፣ ህጎች፣ ደንቦችና የአሰራር ስርዓቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በጥናት በመለየት አማራጭ የመፍትሄ ሀሳቦች የሚያቀርቡበት እስከ ጠቅላይ ሚንስትሩ የሚደርስ የውይይት መድረክ ከመንግስት ጋር ያዘጋጃል፡፡ ምክር ቤቱ ለመንግስት የሚሆኑ ግብዓቶችን ከማዘጋጀት አንፃር በሚያካሂደቸው ጥናቶች፣ ከኢንስቲትዩቱ ጋር በመተባበር የሚሰራበትን መንገድ ለማመቻቸት ስምምነቱ ያስችለዋል፡፡

ምክር ቤቱ ለንግዱ ማህበረሰብ የሚሰጣቸውን ስልጠናዎች እና የንግድና ኢንቨስትመንት፣ የገበያና አጠቃላይ ጠቃሚ መረጃዎችን በተጠናከረ መልኩ ለመስራት ብሎም የዳታ አሰባሰብና አተናተን አሰራር ስርዓትን ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ለማድረስ ኢንስቲትዩቱ ካለው ልምድ አኳያ አብሮ መስራቱ አስፈላጊ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ከመንግስት ጋር በሚያደርገው ውይይት ከፖሊሲ ጥናቶች ጋር ተያይዞ ይህን ከመሰለ የመንግስት ኢንስቲትዩት ጋር አብሮ መስራቱ ተአማኝነቱን ስለሚጨምር በተደረገው ስምምነት ደስተኛ እንደሆኑ የተናገሩት አቶ የሱፍ ምክር ቤቱ ከተቋሙ ጋር በጋራ የተሻለ ስራ እንደሚሰራ ተስፋቸውን ገልፀዋል፡፡

አቶ አለበል ደሴ በበኩላቸው ተቋማቸው በነፃ ኢኮኖሚው ውስጥ ስለማክሮ ኢኮኖሚና ስለ አገር እድገት ተከታታይ የሆኑ በተለይ ለፖሊሲ ጠቃሚ የሆኑ ሳይንሳዊ ጥናቶችና ምርምሮችን በማካሄድና መንግስትን በማማከር የሚሰራ መሆኑን በመጥቀስ የግል ዘርፉንም አስመልክቶ ከዚህ በፊት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ፣ የፋይናንስ፣ ከኢንቨስትመንት ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶች ላይ ጥናቶችን በማካሄድ የፖሊሲ የመፍትሄ ሀሳቦችን ለመንግስት ያቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ምክር ቤቱ በቀጣይ የግሉን ዘርፍ ችግሮች በጥናት አስደግፎ የፖሊሲ ሀሳብ በማቅረብ ረገድ በጋራ ለመስራት ፍላጎቱን ማሳየቱ ለተቋሙ እንደ መልካም አጋጣሚ ይቆጠራል በማለት ስምምነቱ እንዳስደሰታቸውም ገልፀዋል፡፡ አቶ አለበል ጨምረው በስምምነቱ መሰረት በጋራ እቅድ በማዘጋጀት ወደ ተግባር መግባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱን ተግባራዊ ከማድረግ ረገድ የጥናትና ምርምር፣የምክር አገልግሎት፣ የአጭርና መካካለኛ ስልጠናዎች፣የግንዛቤ ማስጨበጫ አገልግሎት፣ የልምድ ልውውጥ ስራዎች በጋራ ከሚሰሩ ዋና ዋና ተግባራት መካከል እንደሚገኙባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

ምክር ቤቱ በኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ላይ ከንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ተወያየ

የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አዲስ በወጣው የኢክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቁጥር ........./2012 ዙሪያ ከተለያዩ ኩባንያዎች ከተውጣጡ የንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ታህሣሥ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. በምክር ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት አደረገ፡፡

ውይይቱን የመሩት የምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ አቶ የሱፍ አደምኑር ከም/ዋና ፀሀፊው አቶ ውቤ መንግስቱ ጋር በመሆን እንደተናገሩት የውይይቱ መሠረታዊ ዓላማ በአዋጁ ላይ የንግዱን ማኅበረሰብ አስተያየት በማድመጥ የአቋም መግለጫውን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉዳዩ ለሚመለከተው የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለማቅረብ ነው፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች ከጨርቃ ጨርቅ አምራቾች ማህበር፣ ከታሸገ ውሃ እና ለስላሳ መጠጦች አምራቾች ኢንዱስትሪ ማህበር፣ ከበላይነህ ክንዴ ኦቶሞቲቭና በላይ አብ ሞተርስ፣ ከሆራይዘን ጎማ እንዲሁም ከጄቲአይ የትንባሆ ሞኖፖል እና ሌሎችም ኩባንያዎች የተውጣጡ ሲሆን አዋጁ በንግዱ እንቅስቃሴ ላይ በሚያሳደረው አሉታዊና አዎንታዊ ተፅዕኖዎች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት አድርገዋል፡፡

በተለይ፣ በአዋጁ መግቢያ ላይ እንደተቀመጠው ቀደም ሲል በነበረው አዋጅ ላይ ከተዘረዘሩት መሠረታዊ ነጥቦች አንዱ በተመረጡ ዕቃዎች ላይ የማምረቻ ወጪ የኤክሳይዝ ታክስ መጣል ሲሆን በአዲሱ አዋጅ ላይ በማምረቻ ወጪ ላይ ሲሰላ የነበረው የኤክሳይዝ ታክስ በፋብሪካ የመሸጫ ዋጋ እንዲተካ መደረጉ በገቢያቸውም ሆነ ባጠቃላይ እንቅስቃሴያቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል ብለዋል፡፡

እንደ ተወያዮቹ አስተያየት ከሆነ በአዲሱ አዋጅ የተቀመጠው የኤክሳይዝ ታክስ በመቶኛ ሲሰላ ከበፊቱ ያነሰ ቢሆንም በፋብሪካ የመሸጫ ዋጋ ላይ የተጣለ በመሆኑ የታክስ መጠኑን በእጅጉ ከፍ ያደርገዋል፡፡

የኤክሳይዝ ታክስ መጣል የሚገባው በቅንጦት ዕቃዎችና ለጤና ጎጂ በሆኑ ዕቃዎች ላይ ሆኖ ሳለ ከምግብነት በሚመደቡ የታሸጉ ውሃዎች ላይ መጣሉም አግባብ አለመሆኑ በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡

አዲሱ አዋጅ በተለይ በሀገር ውስጥ በሚያመርቱ አምራቾች ላይ የተጣለው ተጨማሪ የታክስ መጠን የሀገር ውስጥ አምራቾችን ከማበረታታት ይልቅ ገቢ ምርት ላይ እንዲሰማሩ እንደሚያደርግም ተወያዮቹ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

በአንዳንድ ምርቶች ላይ የተጣለው ከፍተኛ ታክስ ደግሞ ለኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት በር ስለሚከፍት ከታክስ ለመሰብሰብ የታቀደውን ዓላማ ላያሳካ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸውም ተወያዮች በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ዋና ፀሐፊው የተወካዮቹን የአቋም መግለጫ የተጠቃለለ ሰነድ ለሚመለከተው አካል እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል፡፡

ምክር ቤቱ የዋና ፀሐፊ መደበየኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ አቶ የሱፍ አደምኑርን ከህዳር 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በዋና ፀሐፊነት በይፋ መቅጠሩን አስታወቀ፡፡

አቶ የሱፍ አደምኑር የምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ በመሆን የተመረጡት በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በተመደቡበት መስክ ባላቸው ሰፊና የካበተ ልምድ እና እንዲሁም ባሳለፉት የሥራ ዘመን ለዘርፍ ባሳዩት ቁርጠኝነት መሆኑን ቦርዱ አስታውቋል፡፡


ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸዉን ለማሳደግ ተስማሙ

የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ዓይናለም አባይነህ (ዶ/ር) የኢትዮጵያና የደቡብ ኮሪያ ሪፐብሊክ የንግዱ ማኅበረሰብ አንቀሳቃሾች የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነታቸውን ቀጣይነት ያለው ውጤት ሊያመጣ በሚችል ደረጃ ለማሳደግ በላቀ ደረጃ ሊሰሩ እንደሚገባ አሳሰቡ፡፡

ዶ/ር ዓይናለም ይህን የተናገሩት ህዳር 19 ቀን 2012 ዓ.ም. የፌዴራል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከምክር ቤቱና የደቡብ ኮሪያ ቢዝነስ ኩባንያ ከሆነው ቡሳን-ኡልሳን ኢኖቢዝ ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባዘጋጀው የኢትዮጵያ-ኮሪያ ቢዝነስ ፎረም ላይ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ነው፡፡ የቦርድ አባሉን ንግግር ተከትሎ የፌዴራል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ ዶ/ር አክሊሉ ኃ/ሚካኤል፣ በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር የተከበሩ ሊም ሁን ሚ እና በኢትዮጵያ የቡሳን ከተማ የክብር ቆንስላ ጄኔራል ኪም ሳንግ ጂን የመክፈቻ ንግግር አድረገዋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት የግሉ ዘርፍ ተወካዮችም ወደተሻለ የንግድ ትሥሥር ሊያደርሳቸው በሚችሉ ጉዳዮች ላይ የአቻ ለአቻ ውይይት አድርገዋል፡፡

ዶር ዓይናለም በንግግራቸው የሀገር ውስጥ የግል አንቀሳቃሾችን እያደገ ካለው የኮሪያ ንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ጋር ይበልጥ የሚያስተዋውቃቸው በመሆኑ መድረኩ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን አጽንዖት በመስጠት ገልጸዋል፡፡ መድረኩ በንግድ ማኅበረሰቡ መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር መልካም አጋጣሚ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ዶር ዓይናለም አያያዘውም የሁለቱን ሀገራት የንግዱን ማኅበረሰብ የማስተሳሰሩ ጉዳይ የምክር ቤቱና የኢኖቢዝ ኩባንያ ጥቅል የቤት ሥራ ሊሆን እንደሚገባም እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታው ዶ/ር አክሊሉ ኃ/ሚካኤል ባደረጉት ይፋዊ የመክፈቻ ንግግር ኢትዮጵያ ከሠሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት 2ኛዋ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንደመሆኗ ለኮሪያ ኩባንያዎች ክፍት ናት ሲሉ በሀገሪቱ ያለውን የኢንቨስትመንት መልካም ዕድል አስረድተዋል፡፡

ሀገራቸው ሰፊ የሀገር ውስጥና የውጭ ገበያ፣ እጅግ ከፍተኛና በተመጣጣኝ ከፍያ የሚሰራ አምራች ኃይል ያላት እንደመሆኗ የኮሪያ ኩባንያዎች ይህን መልካም አጋጣሚ መጠቀም እንደሚችሉ አብራርተዋል፡፡ የሁለቱ ሀገሮች የግሉ ዘርፍ አጋርነትም በመንግሥታቸው አጽንዖት ይሰጠዋል ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ሁን ኢትዮጵያና ኮሪያ ልዩና ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው በኮሪያ ጦርነት ወቅት የተሰዉትን ኢትዮጵያውያን በማስታወስ የገለጹ ሲሆን ሀገራቱ ይህን የረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፉም ይበልጥ ለማጠናከር እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የኮሪያ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር የጋራ ጥቅማቸውን በሚያስጠብቅ መልኩ መሥራት እንደሚፈልጉም እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያንና የደቡብ ኮሪያን የንግድ ግንኙት አስመልክቶ በተደረገው ማብራሪያ ኢትዮጵያ እንደ ቡና፣ የቅባት እህሎች ቆዳ ወደ ኮሪያ ስትልክ እንደ መድኃኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የኤሌክትሪክ ዕቃዎችና ጎማ እንደምታስገባ ተገልጿል፡፡ ደቡብ ኮሪያ የእስያ ገበያ መተላለፊያ ላይ ያለች እንደመሆኗ እንደ ቡና፣ ሰሊጥ፣ አበባ፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳና የቁም ከብት የመሳሰሉትን ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን የኢትዮጵያ ምርቶች በከፍተኛ ቁጥር ወደ ኮርያ ለማስገባት እየሰሩ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ .ኤ.አ. የ2018 መግለጫ እንደሚያመለክተው የሁለቱ ሀገራት ያለፉት አሥርት ዓመታት የንግድ ልውውጥ መጠን 1.8 የአሜሪካ ዶላር ሲሆን ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ መጠን 226 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የገቢ ንግዷ ደግሞ 1.6 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር መሆኑም ታውቋል፡፡

በመድረኩ ላይ 100 ያህል የኢትዮጵያ ኩባንያዎች በማዳበሪያ ምርት፣ ሰሊጥና ቡና ማቀነባበሪያ፣ አውቶሞቢል፣ ኬሚካል ምርት፣ ኮንስትራክሽንና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች፣ ሪል ኢስቴትና የኢንዱስትሪ መንደር ማልማት ላይ ከተሰማሩ ከ12 በላይ የኮሪያ ባለሀብቶች ጋር በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ ሊያደርሳቸው የሚያስችል ውይይት አድርገዋል፡፡

ሁለቱ ሀገሮች በቅርቡ ከሁለት ሳምንታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ተመሳሳይ ቢዝነስ ፎረም ማካሄዳቸውም ይታወቃል፡፡

አመታዊ የዘርፈ ብዙ ባለድረሻ አካላት የጋራ ውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው


የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያዘጋጀው አመታዊ የውሃ አቅርቦት፣ ሳኒቴሽንና ሀይጅን እና የውሃ ሀብት አስተዳደር የዘርፈ ብዙ ባለድረሻ አካላት የጋራ ውይይት መድረክ ከህዳር 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በሂልተን ሆቴል እየተካሄደ ነው፡፡

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኢነጂ. ስለሺ በቀለ በእንኳን ደህና መጣችሁና በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት የዘርፈ ብዙ ባለድረሻ አካላት የጋራ ውይይት መድረክ እ.ኤ.አ. ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በውሃ ዘርፍ ላይ የሚሰሩ አካላት በየአመቱ ውይይት የሚያካሂዱበት መድረክ ሲሆን ዘንድሮ አስረኛ አመቱን እና የውሃ ሀብት አስተዳደርን በማካተት ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ሚኒስትሩ አክለው የዘንድሮው አመታዊ የውይይት ጉባኤ በዋናነት በውሃ ዘርፍ ላይ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ያሉበትን ሁኔታ እና ፈታኝ ሁኔታዎች እንዲሁም የወደፊት ስትራቴጂካዊ እቅዶች በመንደፍ የሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እና ዘላቂ የልማት ግቦችን እውን ለማድረግ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች በመለየት