የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምርታማነት ማሻሻያ እና ልህቀት ማዕከል በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምርታማነት ማሻሻያ እና ልህቀት ማዕከል በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
ሁለቱ ተቋማት በተለይም በአቅም ግንባታ እና ስልጠና መስኮች በትብብር እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
ስምምነቱን የተፈራረሙት የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ(ተባባሪ ፕሮፌሰር) እና የማዕከሉ ዲን አቶ አድማሱ በቀለ ናቸው፡፡
የአባላትንና የንግዱን ማኅበረሰብ አቅም መገንባት፣ ንግድና ኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን፣ የምርምርና አድቮኬሲ እንዲሁም ምቹ የቢዝነስ ከባቢ መፍጠር ምክር ቤቱ የሚሰራቸው ዋና ዋና ተግባራት መሆናቸውን ያነሱት ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ ለቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ ለወጣቶች፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ለሴቶችም ትኩረት በመሰጠቱን ከማዕከሉ ጋር በትብብር ውጤታማ ተግባራትን ማከናወን እንደሚቻል አንስተዋል፡፡

የማዕከሉ ዲን አቶ አድማሱ በቀለ በበኩላቸው ለቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ውጤታማነት እንዲሁም የኢንዱስትሪ ባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት ከምክር ቤቱ ጋር በጋራ መስራት እንደሚሹ አብራርተዋል፡፡
በማዕከሉ የተለዩ እንደ አይሲቲ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የግንባታና የመሳሰሉት ዘርፎች በትኩረት እየተሰራባቸው ነው ብለዋል አቶ አድማሱ፡፡
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ውጤታማ እንዲሆን እንደ GIZ ካሉ የልማት አጋሮች እና የመንግስት ተቋማት ጋር በመተባበር ሲሰራ መቆየቱም የሚታወቅ ነው፡፡

