Mar 17, 2026 .
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ለወጣት ስራ ፈጣሪዎች በዲጂታል ማርኬቲንግና ኢ-ኮሜርስ ዙሪያ ስልጠና መስጠት ጀመረ፡፡



የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ለወጣት ስራ ፈጣሪዎችና የኢንተርፕራይዝ ባለቤቶች በዲጂታል ማርኬቲንግና ኢ-ኮሜርስ ዙሪያ ስልጠና መስጠት ጀመረ፡፡
ስልጠናው አሁን ካለው ዘመናዊ አሰራርና ግብይት እንዲሁም ምርትና አገልግሎትን በቀላሉ ለደንበኞች ለማድረስ ትልቅ አማራጭ ሆኖ ያገለግላል ተብሏል፡፡
ስልጠናው ምርትና አገልግሎትን ለአካባቢያዊ፣ ለቀጣናዊና አለም አቀፍ ገበያ በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ ያለው ፋይዳ የላቀ መሆኑን የምክር ቤቱ ምክትል ዋና ጸሐፊ ወ/ሮ ሔለን ረታ በስልጠናው ማስጀመሪያ ላይ ተናግረዋል፡፡


በዚህ የዲጂታል ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ ለመሆን በየትኛውም ቦታ ሆኖ ምርትና አገልግሎትን በማስተዋወቅ የጉዞ እና የርቀት ችግርን በመቅረፍ በቀላሉ ተወዳዳሪ መሆን ያስችላል ነው ያሉት፡፡
ዲጂታል ማርኬቲንግና ኢ-ኮሜርስ ሰዎች ባሉበት ሆነው የተቋማቸውን ብራንድ፣ ስምና ዝና የሚገነቡበት፣ ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበትና ግብይት የሚፈጽሙበት የዲጂታል አማራጭ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በቢዝነስ አመራር አካዳሚው በኩል በተለያዩ መስኮች ፍላጎትን መሰረት በማድረግ ስልጠናዎችን በመስጠት የቢዝነስ ተቋማት ውጤት እንዲያመጡና ራሳቸውን እንዲያዘምኑ እያደረገ ነው።

