የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዴሬክተሮች ቦርድ በጣሊያን በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የግብርና ማሽነሪ ኤግዚቢሽን ላይ ተሳትፎ እያደረግን ነው።

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዴሬክተሮች ቦርድ እና በዘርፉ የተሰማሩ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ዛሬን ጨምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በጣሊያን በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የግብርና ማሽነሪ ኤግዚቢሽን ላይ ተሳትፎ እያደረግን ነው።
እየተካሄደ ያለው የንግድ ትርሂት በዘርፋ ያሉ የግሉ ዘርፍ ተዋንያን ከአቻ የንግዱ ማኅበረሰብ ጋር እንዲተዋወቁና የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ እንዲሁም ተሞክሮ እንዲለዋወጡ እና በጋራ የሚሰሩበት ሁኔታን በማመቻቸት ረገድ ሚናው ከፍ ያለ ነው ።
በተጨማሪም ከጣሊያንና ከሌሎች ሀገራት ከመጡ ኩባንያዎች፣ ባለሀብቶች፣ አስመጪዎችና ላኪዎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በመፍጠር ለሀገራችን ምርቶች የገበያ ዕድሎችን ማስፋት እና የንግድ አጋርነትን ማሳደግ ሌላኛው ግብ ነው።

በሌላም በኩል “Buy Ethiopian-Invest in Ethiopia ” ወይም “የኢትዮጵያን ይግዙ- በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ” በሚሉት መልዕክቶቻችን የኢትዮጵያን የምርት ጥራት፣ የንግድ ተወዳዳሪነትና የኢኮኖሚ አቅም ለዓለም የምናሳይበት መድረክም ጭምር ነው።
በተጎዳኝም ፤ ዘመኑ የደረሰበት የንግድ አመራር እና አሠራሮች፣ የምርት ማስተዋወቂያ ዘዴዎች፣ የግሉ ዘርፍ የውድድር አቅም ማሳደጊያ ልምዶችን ለመቅሰም በማስቻል ረገድ የዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽኑ ሚና ከፍ ያለ ነው።

በመሆኑም ፤ ከላይ በመግቢያዬ ከተነሱት ጭብጦች መነሻነት የዚህ መድረክም ሆነ ተመሳሳይ ተሳትፎዋች ስኬት የሚለካው በምናስገኛቸው አዳዲስ የንግድ ግንኙነቶች፣ በሚፈጠሩ የኢንቨስትመንት ዕድሎች፣ በሚጠናከሩ የአቻ ተቋማት ግንኙነቶች እንዲሁም በሀገራችን የንግድ ማኅበረሰብ ላይ እያመጣ ካለው ተጨባጭ ተጽዕኖ አንፃር በመሆኑ አሰራሩን የበለጠ እያጠናከርን እና እያሰፋነው የምንሄደው ቁልፍ ተግባራችን ይሆናል።
በመጨረሻም፣ ይህ ተሳትፎ እንዲሳካ እገዛ ላደረጉልን ለኢፌዴሪ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ፣ በጣሊያን የኢትዮጵያ ኢምባሲ፣ በኢትዮጵያ የጣሊያን ኢምባሲ እና ሌሎች ባለድርሻዎች በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና በራሴ ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
የተከበሩ ሰብስብ አባፊራ አባጆቢር
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት

