ተ/ዋና ፀሀፊው የኒዉዝላንድ አምባሳደሩን ተቀብለው አነጋገሩየኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ተ/ዋና ፀሀፊ አቶ ውቤ መንግስቱ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የምክር ቤቱ የስራ ሀላፊዎች ጋር በመሆን መጋቢት 30 ቀን 2014 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የኒዉዝላንድ አምባሳደር ሚሰተር ሚካኤል አፕተንን በፅ/ቤታቸዉ ተቀብለዉ አነጋገሩ፡፡

ምክር ቤቱ በአዋጅ የተቋቋመ ሆኖ በስሩ የክልል ንገድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶችን ፣ የሁለት ከተማ የንገድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶችን እና አገር አቀፍ የዘrርፍ ማህበራት ምክር ቤቱን ጨምሮ የዘርፍ ማህበራትን በፈቃደኛ አባልነት በስሩ በማካተት የተመሰረተ የግሉ ዘርፍ ድምፅ ተቋም መሆኑን በመጥቀስ በዋነኝነት የአድቮኬሲና ምርምር፣ የአቅም ግንባታ አና የንግድና ኢንቨስትመንት ማስፋፋት ስራዎችን እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ያሏትን ዘርፈ-ብዙ የንግድና ኢንቨስትመንት ሀብቶች ከገለፁ በኋላ ምክር ቤቱ ከኢምባሲው ጋር ግንኙነቱን በማጠናከር የንግዱ ማህበረሰብ በተሻለ ሁኔታ ተጠቃሚ እነዲሆን በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ንግድ እና ኢንቨስትመንት የበለጠ ማስፋፋት እንደሚፈልጉ አስምረውበታል፡፡ በመጨረሻም ምክር ቤቱ በግንቦት ወር 2014 ዓ.ም በሚያዘጋጀው 12ኛው የኢትዮ- ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ላይ ኢምባሲውና የኒውዝላንድ ኩባንያዎች እንዲሳተፉ ጋብዘዋል፡፡

አምባሳደር ሚሰተር ሚካኤል አፕተን በበኩላቸው የኒውዝላንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በቁጥር ጥቂት እንደሆኑና ሁለቱ አገሮች የንግድና ኢንቨስትመንት እድሎቻቸው ላይ የበለጠ በመስራት በመካከላቸው ያለውን የቢዝነስ ትስስር የበለጠ ማጎልበት እንደሚገባ ተናግረዋለ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2019 377000 የኒውዝላንድ ዶላር የሚገመቱ እንደ ማሽኖች፣ ብረታብረትነና መሽነሪዎች የመሳሰሉ ምርቶችን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ደግሞ ወደ 6.9 ሚሊዬን የኒውዝላንድ ዶላር የሚገመቱ እንደ ቡና የመሳሰሉ የእርሻ ምርቶችን ኒውዝላንድ ያስገባች መሆኗን በመጥቀስ የንግድ ሚዛኑ ወደ ኢትዮጵያ ያደላ ነው ብለዋል፡፡ አገራቸው በቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር፣ በስልጠና አና የገንዘብ ድጋፍ የመሳሰሉትን ለኢትዮጵያ በማድረግ የሁለቱ አገሮች የንግድ ማህበረሰቦች በጋራ በሚጠቀሙበት አግባብ ወደፊት ከምክር ቤቱ ጋር በትብብር እንደሚሰሩ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ሁለቱ ወገኖች በንግድና ኢንቨስትመንት ማስፋፋት፣ በስልጠና፣ በልምድ ልውውጥና የእዉቀት ሽግግር፣ በገንዘብና ቴክኒክ ድጋፍ እና ሌሎችም በርካታ ጉዳዮች ዙሪያ በቀጣይ በትብብር በሚሰሩበት አግባብ ላይ ተወያይተዋል ::

ምክር ቤቱ ያዘጋጀውን ዘመናዊ የዲጂታል አገልግሎት በይፋ አስጀመረየኢትዮጵያ የንግድ እና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከአይርላንድ መንግስት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በትሬድ ማርክ ኢስት አፍሪካ (Trade Mark East Africa) የቴክኒክ እገዛ አማካኝነት ያዘጋጀውን ዘመናዊ የዲጂታል አገልግሎት መጋቢት 28 ቀን 2014ዓ.ም በራዲሰን ብሉ ሆቴል በደማቅ ሁኔታ በይፋ አስጀመረ፡፡

የኢትዮጵያ የንግድ እና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተ/ዋና ፀሀፊ አቶ ውቤ መንግስቱ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን ሲያስተላልፉ በምክር ቤቱ ቀደም ሲል በነበረው አሰራር በአብዛኛው የንግድ ማሳለጫ ስራዎች(trade facilitation operations) ማንዋል የነበሩ በመሆኑ ነጋዴዎች በምክር ቤቱ በአካል ተገኝተው ፎርሞችን ለመግዛትና ለመሙላት ይገደዱ ነበር ብለዋል፡፡ አሁን በተዘጋጀው ዘመናዊ የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ ግን የንግዱ ማህበረሰብ ከየትኛውም የዓለም ክፍል እና ቦታ ሆኖ አገልግሎቱን ማገኘትና መጠቀም እንደሚቻል ተ/ዋና ፀሀፊው አክለው ተናግረዋል።

የዲጂታል አገልግሎቱን በይፋ ያስጀመሩት የኢፌዲሪ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ አቶ እንዳለው መኮንን እንደተናገሩት ምክር ቤቱ አገልግሎት አሰጣጡን ከማኑዋል ወደ ዲጂታል በማሸጋገር አባላቱ እና የንግዱ ማህበረሰብ በተመቻቸው ጊዜና ቦታ አገልግሎት ማግኘት የሚችችሉበትን አዲስ የዲጂታል ፕሮጀክት በማዘጋጀቱ ትግበራ መጀመሩ ትልቅ አድናቆት ይገበዋል፤ ሚኒስቴር መሰሪያ ቤቱም በሚፈለግበት ሁሉ እገዛ ያደርጋል።

በትሬድ ማርክ ኢስት አፍሪካ የኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብነት በቀለ በበኩላቸው የንግዱን ምህዳር ምቹ ለማድረግ ትሬድ ማርክ ኢስት አፍሪካ በለጋሾች በኩል የኢትዮጵያን መንግስት ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከሚያስተባብራቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ የምክር ቤቱ የዲጂታል አገልግሎት ፕሮጀክት አንዱ መሆኑን በመጥቀስ፤ ጊዜ እና የግብይት ወጪዎችን ቆጣቢ የሆነውን የዚህን ፕሮጀክት አጠቃቀም ለንግዱ ማህበረሰብ ሙሉ በሙሉ ለማስተዋውቅ ወደፊት ቀጣዩ ደረጃ ወሳኝ ነው ብለዋል።

ምክር ቤቱ እስካሁን ሲሰጣቸው የነበሩትን አገልግሎቶች በኦንላይን ለመስጠት በዋነኛነት አባላትን ለመመዝገብ የሚያስችል የአባላቶች የመረጃ ቋት፣ የአቻ ለአቻ የቢዝነስ ትስስር (B2B) መፍጠር፣ ለአባላት አቅም ግንባታ ሥልጠናዎች፣ የግልግል ዳኝነት እና ኤክስፖርትን ለማስፋፋት እንዲሁም የንግድ ነክ መረጃን ያካተተውን አዲሱን የምክር ቤቱን የዲጂታል ሲስተም (Ethiopian Chamber Digital System) አስመልክቶ በ Africom Technologies & iDaptive Data Fusion System ባለሙያዎች ገለፃ ተድርጓል።

የመዝጊያ ንግግር የደረጉት የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ኢ/ር መለአኩ እዘዘው በበኩላቸው አዲሱን የዲጂታል ሲስተም አተገባበር ምክር ቤቱ አቅሙን ገንብቶ በራሱ ሙሉ በሙሉ እስከ ሚያስተዳድረው ድረስ ሲፍትዌሩን ያዘጋጀው ድርጅት በቀጣይ ለሁለት አመት የቴክኒክ እገዛ እንደሚያደርግና በኤሌክትሮኒክ የአንድ መስኮት አገልግሎትን(Electronic Single Window Service) አስመልክቶ ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋርም በመተባበር በመስራት የንግዱን ማህበረሰብ በበቃት እንደሚያገለግሉ ገለፀዋል፡፡ በመጨረሻም በእለቱ ትግበራውን በይፋ የጀመረውን የምክር ቤቱን የዲጂታል ሲስተም እውን እንዲሆን በገንዘብና በቴክኒክ የረዱትን የአይርላንድ መንግስት፣ የትሬድ ማርክ ኢስት አፍሪካ እና Africom Technologies & iDaptive Data Fusion System ድርጅትን አመስግነዋል፡፡

በዚህ የዲጂታል አገልግሎት ይፋ የማስጀመር ስነ-ስርዓት ላይ የኢፌዲሪ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መሰሪያ ቤትን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ስራ ሀላፊዎች እና የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

ECCSA- IBF meeting said to further strengthen the Existing RelationThe Ethiopian Chamber of Commerce and Sectoral Associations (ECCSA) - India Business Forum (IBF) bilateral breakfast meeting was organized in Partnership with the Embassy of India, Addis Ababa on March 17, 2022 at Hilton Addis Hotel.

The objectives of the meeting were to further promote existing bilateral ties in trade and investment, to create mutual advocacy and research networking platform, and establish a working group for more engagements.

Melaku Ezezew (Eng.), President of the Ethiopian Chamber of Commerce and Sectoral Associations (ECCSA) in his remarks, said the bilateral meeting is so important to boost the growing business links between Ethiopia and India.

countries for their mutual benefit. As part of our endeavors on moving forward private sector development, we are committed to partner deeply with friendly countries such as India and the counterpart India Business Forum (IBF), he added.

Ambassador Robert Shetkintong, Indian ambassador to Ethiopia, on his part, said that the event and the upcoming engagements will add more momentum in the efforts to strengthen Ethio-India long-lasting relations into a far vital area of cooperation in trade and investment. He further said that the meeting would also offer good opportunities to the private sectors to expand collaboration.

On the breakfast meeting, Ethiopian Chamber of Commerce and Sectoral Associations (ECCSA) Acting Secretary General Wubie Mengestu and his management members, India Business Forum (IBF), Indian Embassy, Addis Ababa Chamber of Commerce and Sectoral Associations (AACCSA) and Indian private companies representing technologies, Pharmaceuticals, dairy and food products, electro plastic, IT, manufacturing of equipment sectors have participated.

የኢትዮጵያ እና የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤቶች በጋራ ለመሥራት መከሩ፡፡የኢትዮጵያ እና የአዲስ አበባ የንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ም/ቤቶች በጋራ በመሥራት አቅማቸውን በማጠናከር የንግዱ ማኅበረሰብን እንዴት በተሻለ አሠራር እና ስትራቴጂ ማገልገል እንደሚቻል መከሩ ።

የኢትዮጵያ እና የአዲስ አበባ የንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ም/ቤቶች በግሉ ዘርፍ ዕድገት፣ በንግድ እና ኢንቨስትመንት፣ በገጽታ ግንባታ፣ የማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት እና በአቅም ግንባታ እንዲሁም በምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻያ፣ በሰራተኞች የርስ- በርስ ግንኙነት፣ በሕንጻ አጠቃቀም እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ሊያከናዉኗቸው በሚገቡ ጉዳዮች ላይ የካቲት 29 ቀን 2014 ዓ.ም በሰፊው ተወያዩ፡፡

በዚህ የሁለቱ ም/ቤቶች የማኔጅመንት አባላት በተሳተፉበት ገንቢ የውይይት መድረክ ላይ የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ም/ዋና ፀኃፊ አቶ ውቤ መንግስቱ እንደተናገሩት ሁለቱ ምክር ቤቶች በጋራ የሚሰሩ ስራዎችን በፍቅር እና በትብብር መንፈስ ተቀራርበው በመስራት የምክር ቤቶቹን መልካም ስምና ገፅታ መገንባት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

የተካሄደው የውይይት መድረክም በማኔጅመንቱና በሰራተኛው መካከል ብቻ የሚወሰን ሳይሆን የየምክር ቤቶቹ የዳሬክተሮች ቦርድ አባላት ተቀብለውት ወደ ስራ የሚገባ እንደሆነና በውይይቱ የተካፈሉ አመራሮችም በመግባባት እና በትብብር መንፈስ አብረው ሊሰሩ ይገባል ሲሉ አቶ ውቤ አሳስበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ዋና ፀሀፊ አቶ ሺበሺ ቤተማሪያም በበኩላቸው በማኔጅመንት አባላት የተጀመረውን መልካም ጅማሮ ለጋራ ዓላማ ጠንክሮ በመስራት ዳር ማድረስ ያስፈልጋል ያሉ ሲሆን አክለውም በሁለቱ ምክር ቤቶች ውስጥ ያለውን እምቅ አቅም በመጠቀም ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብለዋል፡፡

በጋራ በሚሰሩ አስተዳደራዊ፣ ኦፕሬሽናል፣ መልካም ግንኙነት፣ የገፅታ ግንባታ በመሳሰሉት አንኳር ተግባራት ላይ ትኩረት አድርገው የድርጊት መርሀ-ግብር አዘጋጅተው ለማኔጅመንቱ እና ለዳሬክተሮች ቦረድ አባላት የሚያቀርቡ ከሁለቱም ምክር ቤቶች የተውጣጡ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል፡፡

ኮሚቴዎችም በምክር ቤቶቹ መካከል በጋራ ሊሰሩ የሚችሉ አበይት ተግባራትን ፤ቀደም ሲል ከአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ም/ቤት በኩል የቀረበውን አጀንዳ መሰረት በማድረግ እና መጨመር ያለባቸውን የውይይት ሃሳቦች የማካተት፣ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ስራዎችን የመለየት፣ የድርጊት መርኃ ግብር የማዘጋጀት፣ የውሳኔ ሃሳብ የማቅረብ እና ውሳኔ የተሰጠባቸውን ጉዳዮች አፈጻጸም የመከታተል እና ሪፖርት የማቅረብ ኃላፊነቶች አሉባቸው፡፡

የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአቻ ለአቻ የቢዝነስ ትስስር (Business Networking) እንዲፈፅሙ አደረገ፡፡የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጂአይኤስቢ(GISB) የተሰኘ የአልጀርስ ኩባንያ ከፍተኛ ሀላፊዎችን እና በኢትዮጵያ በኬብል እና በፕላስቲክ ማምረቻ ዘርፍ የተሰማሩ አምስት የግል ኩባንያዎች የስራ ሃላፊዎችን መስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም በምክር ቤቱ የስልጠና አዳራሽ ተቀብሎ የአቻ ለአቻ የቢዝነስ ትስስር (Business Networking) እንዲፈፅሙ አደረገ፡፡

ሁለቱ ወገኖች ኩባንያዎቻቸዉ ስለሚያቀርቡት ምርትና አገልግሎት፣ ስለሀገሪቱ የንግድና ኢንቨስትመንት እድሎች እንዲሁም በቀጣይ በጋራ ስለሚሰሩባቸው ጉዳዮች መረጃ ተለዋውጠዋል፡፡

ጂአይኤስቢ(GISB) የተሰኘው ኩባንያ የኤሌትሪክ ኬብሎችንና ትራንስፎርመሮችን በማምረት በአልጀርስ ከፍተኛ ድርሻ ያለው እና በኢትዮጵያም በኢንቨስትመንት መሰክ ለመሰማራት ፍላጎት ያሳየ ኩባንያ መሆኑ ታውቋል፡፡


 

የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የነጩ ፖስታ ጎርፍ ለነጩ ቤተ መንግስት ሀገራዊ ንቅናቄን አስጀመረ፡፡

የነጩ ፖስታ ጎርፍ ለነጩ ቤተ መንግስት ሀገራዊ ንቅናቄ የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት፣ አመራሮችና ሰራተኞች በተገኙበት በምክር ቤቱ የ መሰብሰቢያ አዳራሽ ዛሬ መስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም ተጀመረ፡፡ በስነ ስርአቱ ላይ የተገኙት የምክር ቤቱ ፕሬዚደንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው እንደገለጹት ይህ “የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ሀገራዊ ንቅናቄ ዓላማ ን ከግቡ ለማድረስ የግሉዘርፍ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ዘመናትን የተሻገረ መሆኑን ያነሱት ፕሬዚደንቱ የአሜሪካ መንግስት በሰጠው አህጉራዊው ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት 'አጎአ' (AGOA) ተጠቃሚነታችን የሚጠበቀውን ያህል ባይሆንም ፤ በየጊዜው እየተስፋፉ ባሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሁም በኢኮኖሚ ማሻሻያ ርምጃዎች ምክንያት እየጎለበተ የመጣ ሲሆን ፤ አሰራሩ ከምንጊዜውም በተሸለ መልኩ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል የሚል ጠንካራ እምነት አለን ብለዋል፡፡

አያይዘውም በአገራችን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በተከሰቱ ግጭቶችን መነሻ የአሜሪካ መንግስት ለታዳጊ አገራት የሰጠው ይህ እድል ለኢትዮጵያ እንዲነፈጋት የሚወተውቱ አካላት ከድርጊታቸው መቆጠብ እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም በዚህ የነጩ ፖስታ ጎርፍ ለነጩ ቤተ መንግስት ሀገራዊ ንቅናቄ የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተሳትፎ ማድረጉ ወቅታዊና አስፈላጊ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

በመሆኑም መላው የንግዱ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ በሚደረገው በዚህ ሀገራዊና ጥረት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በዚህ ሀገራዊ ንቅናቄ መድረክ ከምክር ቤቱ ፕሬዚደንት በተጨማሪ ዋና ጸኃፊው አቶ የሱፍ አደምኑር እንዲሁም ሌሎች ሰራተኞችና አመራሮችም ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

እንደሚታወቀው በንቅናቄው ከአምስት ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ፊርማቸውን በማሰባሰብ የነጭ ፖስታ ጎርፍ ወደ አሜሪካው ነጩ ቤተ መንግስት የሚላክ ሲሆን፤ በመላ ሀገሪቱ ያሉ ዜጎች ፤ አለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን እውነታ እንዲረዳ፣ ከ ጣልቃ ገብነት እንዲታቀብ መልዕክት ለማስተላለፍ ታስቦ እየተካሄደ ያለ አገር አቀፍ ዘመቻ ነው፡፡

ዋና ፀሐፊ የባንግላድሽ አምባሳደር አነጋገሩ፡፡

የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ፀሀፊ አቶ የሱፍ አደምኑር በኢትዮጵያ የባንግላድሽ አምባሳደር ናዝሩል ኢስላምን መስከረም 4 ቀን 2014 ዓ.ም በፅ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡

አምባሳደር ናዝሩል ኢትዮጵያ እና ባንግላድሽ የረጅም ጊዜ ወዳጅነት ያላቸው አገሮች መሆናቸውን በመጥቀስ ኢትዮጵያ በተለይም የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በመሆኗ ዘርፈ-ብዙ ግንኙነት ከማድረግ ረገድ በጣም አስፈላጊ አገር መሆኗን ተናግረዋል፡፡ ንግድና ኢንቨስትመንትን አስመልክቶ በመንግስት በኩል በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ካልተጨመረበት የታቀዱ ስራዎች ግባቸውን አንደማይመቱም ብለዋል፡፡ አያይዘው የባንግላድሽ እና የኢትዮጵያን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከርና ለማሳደግ በሁለቱ አገሮች ንግድ ምክር ቤቶች መካከል የመግባቢያ ስምምነቶች ማድረግ እና ስራዎችን በትብብር መስራት እንሚገባ አክለዋል፡፡ የባንግላድሽ ባለሀብቶች በጨርቃጨርቅ፣ በግብርና እና በመድሀኒት ማምረት ዘርፎች መሰማራት እንደሚፈልጉም አምባሳደሩ ጠቁመዋል፡፡

የምክር ቤቱ ዋና ፀሀፊ አቶ የሱፍ በበኩላቸው ምክር ቤቱ የንግድና ኢንቨስትመንትን እንደሚያስፋፋ፣ የአቅም ግንባት ስልጠናዎችን እንደሚሰጥ፣ የምርምርና አድቮኬሲ ስራዎችን በመስራት እና የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የውይይት መድረኮችን በማካሄድ በየጊዜው የሚጋጥሙ የቢዝነስ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡ ለንግዱ ማህበረሰብ ልዩ ልዩ ጠቃሚ የቢዝነስ መረጃዎችን በማሰራጨት፣ በቢዝነስ እንቅስቃሴ ወቅትም የሚያጋጥሙ ግጭቶችን በምክር ቤቱ የዳኝነት ግልግል ማዕከል በኩል በመፍታት የንግድ እና ኢንቨስትመንቱን ከባቢ ምቹ ከማድረግ አኳያ ምክር ቤቱ በርካታ ተግባራትን እንደሚያከናውንም አብራርተዋል፡፡ በሁለቱ አገሮች በርካታ የንግድና ኢንቨስትመንት ሀብቶች መኖራቸውን ጠቅሰው የባንግላድሽ ባለሀብቶች ኢትዮጵያ መጥተው በማንኛውም ዘርፍ ቢሰማሩ ተጠቀሚ እንደሚሆኑም ተናግረዋል፡፡ ምክር ቤቱ በቀጣይ ከባንግላድሽ አቻው ጋር የመግባቢያ ስምምነቶችን በማድረግ የሁለቱን አገራት ንግድና ኢንቨስትመንት የሚያሳድጉ ተግባራትን በትብብር ለመስራት ዝግጁ እንደሆነም ዋና ፀሀፊው አክለው ገልፀዋል፡፡

ም/ዋና ፀሀፊው የካዛኪስታን አምባሳደርን አነጋገሩ

የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ዋና ፀሀፊ አቶ ውቤ መንግስቱ በኢትዮጵያ የካዛኪስታን አምባሳደር ባርሊቤይ ሳዲኮቭን ጳጉሜን 5 ቀን 2013 ዓ.ም ተቀብለው ሁለቱ አገራት የንግድና የኢኮኖሚ ግንኙነታቸውን በሚያጠናክሩበትና በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ አነጋገሩ፡፡

አምባሳደሩ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የንግድና ኢኮኖሚ ትስስር እና ትብብር አነስተኛ መሆኑን በማስታወስ በቀጣይ ግንኙነታቸውን ለማጠናከርና ለማሳደግ እንደሚፈለጉ ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም የንግዱ ማህበረሰብ እርስ በርስ ግንኙነት የሚፈጥሩበት እና ስለ ሁለቱ አገራት የንግድና ኢንቨስትመንት እምቅ ሀብቶችና እድሎች በቂ መረጃና የእውቀት ልውውጥ የሚያገኙበት መድረክ ማመቻቸት አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም ኢምባሲያቸው እ.ኤ.አ. መስከረም 20/ 2021 ዓ.ም. የቢዝነስ ሴሚናር እንደሚያዘጋጅና ምክር ቤቱም በዚህ ሴሚናር ተሳታፊ እንዲሆን ጋብዘዋል፡፡

የምክር ቤቱ ም/ዋና ፀሀፊ በበኩላቸው ሰለምክር ቤቱ አመሰራረት፣ አደረጃጀትና የሚያከናውናቸውን ዋና ዋና ተግባራት በመግለፅ በአገሪቱ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ምቹ ከማድረግ አኳያ የሚያጋጥሙ መሰናክሎችና ችግሮችን ለመፍታት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ በተዋረድ ከሚገኙ አጋር አካላት ጋር ምክር ቤቱ መድረኮችን በማዘጋጀት በየጊዜው ውይይት እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡ ኢምባሲው የሁለቱ አገራት የንግድ ማህበረሰብ የሚገናኙበትና በቂ የቢዝነስ መረጃ የሚለዋወጡበትን መንገድ ከማመቻቸት ረገድ እንዲሁም የሀገራቱን የንግድና የኢኮኖሚ ትብብር ለማሳደግ ያሳየውን ተነሳሽነት በማመስገን በቀጣይ በሚያዘጋጀው የቢዝነስ ሴሚናር ምክር ቤቱ አብሮ እንደሚሰራና አስፈላጊውን ትብብር ሁሉ እንደሚያደርግ ም/ዋና ፀሀፊው አክለው ገልፀዋል፡፡

ፕሬዚዴንቱ በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት ለማቅረብ ፈቃድ የተሰጠው የሳፋሪ ኮም ቴሌኮሚኒኬሽን ኢትዮጵያ ኃ.የተ. ልዑካን ቡድን ተቀብለው አነጋገሩ

የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ኢንጂነር መለአኩ እዘዘው ከዋና ፀሀፊ አቶ የሱፍ አደምኑር ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት ለማቅረብ ፈቃድ የተሰጠው የሳፋሪ ኮም ቴሌኮሚኒኬሽን ኢትዮጵያ ኃ.የተ. ድርጅት የውጪ ግንኙነት ሀላፊ ሚስተር ማቲው የተመራውን አራት አባላት የያዘ ልዑካን ቡድን ነሀሴ 18 ቀን 2013ዓም በፅ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡

ኢንጂነር መላኩ ሰለምክር ቤቱ አደረጃጀትና የሚያከናውናቸውን ዋና ዋና ተግባራት በመግለፅ የቢዝነሱን እንቅስቃሴ ምቹ ከማድረግ አንፃር በተለይም በአድቮኬሲው መስክ በመንግስትና በግሉ ዘርፍ መካከል መድረኮችን በማዘጋጀት በጥናት የተደገፉ በርካታ ውይይቶች የተካሄዱና ውጤት የተገኘባቸው መሆኑን ለልዑካን ቡድኑ አብራርተዋል፡፡

የቴሌኮም አገልግሎት በኢትዮጵያ ቁልፍ ከሆኑ ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑና ይህን የመሰለ አለም አቀፍ አውቅና ያለው አንጋፋ ድርጅት ዘመናዊ የዲጅታል አገልግሎት ለመስጠት ወደ አገር ቤት መምጣቱ የሚያስመሰግነውና ደስተኛ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚደንቱ አክለው ምክር ቤቱ ለድርጅቱ አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግና በቀጣይም በመገናኘት በትበብብር ለመስራት ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡

ሚስተር ማቲው በበኩላቸው እንደተናገሩት ድርጅታቸው እጅግ ዘመናዊና አለማቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ዲጅታል የቴሌኮም አገልግሎት በኢትዮጵያ ለመስጠት ቅድመ ሁኔታዎችን እያሟላ እና ቅድመ ተግባራትን እያከናወነ በሂደት ላይ ይገኛል፡፡ አያይዘውም አሁን በሂደት ላይ በተለይም የመስሪያ ዕቃዎችን ወደ ኢትዮጵያ ከማስገባት ረገድ ድርጅታቸው እያጋጠመው ያለውን መሸናክሎች አልፎ ውጤታማ እንዲሆን ምክር ቤቱ ያለውን ከፍተኛ አቅምና ተሞክሮ በመጠቀም እገዛ እንዲያደርግላቸውና በትብብር አብሯቸው እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎት ለማቅረብ ፈቃድ የተሰጠው ይህ ድርጅት በውስጡ የተለያዩ ኩባንያዎች በመያዝ የጋራ ጥምረት ሲሆን በጥምረቱም የኬንያው ሳፋሪኮም ፤ የዩናይትድ ኪንግደም ቮዳፎን እና ሲዲሲ ግሩፕ፣ የደቡብ አፍሪካ ቮዳኮም፣ የጃፓኑ ሱሚቶሞ እና ዲኤፍሲ የተካተቱ መሆናቸው ታውቋል።

ዋና ፀሀፊው የአሜሪካ ኤምባሲ ምክትል የኢኮኖሚ ኮንስለርን ተቀብለው አነጋገሩ

የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ፀሀፊ አቶ የሱፍ አደምኑር የአሜሪካ ኤምባሲ ምክትል የኢኮኖሚ ኮንስለር አሊ ናዲርን ዛሬ ሃምሌ 29 ቀን 2013ዓም በፅ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡

ምክትል የኢኮኖሚ ኮንስለር አሊ ናዲር በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ያሉትን የንግድና ኢንቨስትመንት እድሎች እንዲሁም የግሉ ዘርፍ ዕድሎችና ተግዳሮቶችን በጥልቀት መረዳት እንደሚፈልጉና በዚህ መነሻም ከምክር ቤቱ ጋር በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ፀሀፊ አቶ የሱፍ አደምኑር በበኩላቸው በምክርቤቱ አበይት ስራዎች ዙሪያ ገለጻ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ፤ ሁለቱ ሀገሮች የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ትስስር ያላቸው እንደሆነና በንግድና ኢንቨስትመንቱም ዘርፍ ግንኙነታቸውን የበለጠ ማጠናከርና ማሳደግ እንደሚገባቸው ገልፀዋል በአገሪቱ ያሉ አማራጮችን እንዲሁም የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ዙሪያ ገለጻ ሰጥተዋቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከ አሜሪካ ቻምበር በኢትዮጵያ ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙን ፤ በስምምነቱም መሰረት የአሜሪካ እና የኢትዮጵ ኩባንያዎች በጋራ የሚሰሩበት ሁኔታን ለማመቻቸት፣ በውጪ ቀጥታ በኢንቨስትመንትን ለመሳብ በጋራ ለመስራት እንዲሁም ኤግዚቢሽኖችን በጋራ ለማዘጋጀት የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ አሜሪካ ለታዳጊ አገራት የሰጠቸው ከታሪፍ እና ቀረጥ ነጻ ገበያ ዕድል(AGOA) የአግዋ ተጠቃሚነት እየተሸሻለ መምጣቱን አንስተው ይህ የገበያ ዕድልም መቀጠል ለግሉ ዘርፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በቅርቡ ለመጀመር ለታቀደው የካፒታል ገበያ እንዲሁም በመንግስት እና የግሉዘርፍ ትብብር ማእቀፍ የአሜሪካ ኩባንያዎች ተሳትፎ ቢያደርጉ ተጠቃሚ ይሆናሉ ሲሉ አክለዋል፡፡ ለዚህም ምክር ቤቱ ከኢምባሲው ጋር በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳለው እና በቅርቡ በአሜሪካ ለማካሄድ በታቀደው የኢትዮ አሜሪካን ኤግዚቢሽን ውጤታማነት እንዲሁም ምክር ቤቱ በያዛቸው ሌሎች ፕሮጀክቶች የኤምባሲውን እገዛ እንዲያደርግ አንስተዋል፡፡

ምክትል የኢኮኖሚ ኮንስለር አሊ ናዲርን በበኩላቸው እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ከምክር ቤቱ ጋር በትብብር ለመስራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡

ምክር ቤቱ ከኢፌዴሪ ጉምሩክ ኮሚሽን ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከኢፌዴሪ ጉምሩክ ኮሚሽን ጋር የስራ ግንኙነቱንና ትብብሩን በማጠናከር የጋራ ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ ለማከናወን የሚያስችለው የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ ሀምሌ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. በኮሚሽኑ የስብሰባ አዳራሽ ተፈራረመ፡፡

በዚህ የመግባቢያ ስምምነት ፊርማ ስነ-ስረዓት ላይ የኢፌዴሪ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ እንደተናገሩት ኮሚሽኑ አደረጃጀቱን በማጠናከር እና አሰራሩን በቴክኖሎጂ በማዘመን የገቢና የወጪ እቃዎች የጉምሩክ ስነ-ስርኣት እና የህግ ተገዥነት አፈፃፀምን ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ፣ ውጤታማ እና ወቅታዊነቱን የጠበቀ በማድረግ የላቀ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ኮሚሽኑ የደንበኛችን እንግልት ለመቀነስ እና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን የወረቀት አልባ የጉምሩክ አገልግሎትም ከመስከረም 2013 ዓ.ም. ጀምሯል፡፡ ኮሚሽኑ እያከናወነ ያለውን የሪፎርምና ሞደርናይዜሽን ስራዎች በዘላቂነት ውጤታማ ለማድረግ የሚቻለው ከመንግስት፣ መንግስታዊ ካልሆኑ እና ከግሉ ዘርፍ አካላት ጋር በቅንጅት እና በትብብር መፈፀም ሲቻል በመሆኑ በፈቃደንነት ላይ የተመሰረተ ትብብር የሚያስፈፅምበት የስምምነት ሰነዶችን በመፈራረም ተግባራዊ እያደረገ እንደሆነ ኮሚሽነሩ አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ኢ/ር መለአኩ እዘዘው በበኩላቸው ኮሚሽኑ የንግዱ ማህበረሰቡን እንደቀዳሚ ደንበኛ በመቁጠር ስራዎችን በዘመናዊና በተሳለጠ ሁኔታ ከምክር ቤቱ ጋር በትብብር እሰራለሁ በሚል መንፈስ ይህን አይነት መድረክ በማዘጋጀቱ አመሰግናለሁ ብለዋል፡፡ ፕሬዚደንቱ አያይዘው እነደገለፁት እንደዚህ አይነት የአሰራር ስምምነት ውጤታማ የሚሆነው ግልፅነት ያለው የጉምሩክ ስርዓት፣ የተሳለጠ የሎጂስቲክ አሰራርና አገልግሎትን ጊዜ እና ገንዘብ ቆጣቢ እና ቀልጣፋና ጥራት ባለው መንገድ ለንግዱ ማህበረሰብ በመስጠት ነው፡፡ የንግዱ ማህበረሰብ የጉምሩክ የአሰራረር ስርዓቶችን እንዲያውቅ፣ እንዲያከበር እና ተጠቃሚ እንዲሆን በማንቃት፣ ግንዛቤ በማስጨበጥና በማስተማር ረገድ እንዲሁም በትብብር የሚሰሩ መሰል በርካታ ስራዎችን ምክር ቤቱ ከኮሚሽኑ ጋር ተባብሮ ይሰራልም ብለዋል፡፡

የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠናን አስመልክቶ የአሰልጣኞች ስሌጠና ተካሄደ

ለተከታታይ አምስት ቀናት ሲሰጥ የቆየው እና የንግዱ ማኅበረሰብ ከአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና የሚያገኛቸውን ጥቅሞች በአግባቡ እንዲጠቀምባቸው እንዲሁም ሊከሰቱ የሚችሉ ክፍተቶችን ቀድሞ በመረዳት የአቅም ማጎልበት ስራዎችን ለማከናወን እንዲረዳ ታስቦ የተዘጋጀው የአሰልጣኞች ስልጠና ዛሬ ተጠናቀቀ፡፡በስልጠና መዝጊያ ፕሮግራሙ ላይ የታደሙት የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው እንደተናገሩት የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ለግሉ ዘርፍ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታም ሆነ የሚኖረውን እንድምታ ተረድቶ በአግባቡ መንቀሳቀስ እንዲቻል የግሉ ዘርፍ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል፡፡በመሆኑም በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና በጠቅላላ ስምምነቶች፣ በእቃዎች እና አገልግሎቶች ንግድ እንዲሁም ያለመግባባቶች መፍቻ ህጎች እና ስነስረሃቶች ፕሮቶኮሎች ላይ የተሰጠው ስልጠና ያሉብንን ክፍተቶች በመረዳት ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡አክለውም እንደዚህ አይነት ስልጠናዎች ወደፊትም በስፋት እንደሚቀጥሉ ገልጸው፤ በኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የግሉ ዘርፍ ወኪል እንደመሆኑ፤ ስልጠናውን የተከታተሉ አባላትም ሆኑ የሴክሬተሪያቱ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች እስከ ከተማ ምክር ቤቶች ድረስ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች በስፋት መዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡

በመጨረሻም ስልጠናውን ለሰጡት ፕሮፌሰር መላኩ ደስታ ላቅ ያለ ምስጋናቸውን አቅርበው የተዘጋጀላቸውን የምክር ቤቱ ማስታወሻ አበርክተውላቸዋል፡፡የምክር ቤቱ ዋና ጸኃፊ አቶ የሱፍ አደምኑር በበኩላቸው ከሰኔ 28- እስከ ሃምሌ 2 ቀን 2013 ዓ.ም ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ለምክር ቤቱ ስራዎችን የበለጠ ከማጠናከር እና ከማስፋት አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

ምክር ቤቱ ከኢፌዴሪ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በጋራ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የችግኝ ተከላ አከናወነ

የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከኢፌዴሪ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በጋራ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የችግኝ ተካለ አከናወኑ፡፡በዚህ ሰኔ 26 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም የሁለቱ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የምክር ቤቱ ዋና ጸኃፊ አቶ የሱፍ አደምኑር እንዲህ አይነት የአረንጓዴ አሻራ ዝግጅቶች ለወደፊቱም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው በዕለቱ ለተገኙ ሰራተኞች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡


ፕሬዚደንቱ የሳውዲ አረቢያን አምባሳደርን ተቀብለው አነጋገሩ

የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ኢንጂነር መለአኩ እዘዘው ከዋና ፀሀፊ አቶ የሱፍ አደምኑር ጋር በመሆን አምባሳደር ሳሚ ጃሚል አብዱላህን ዛሬ ሰኔ 17 ቀን 2013ዓም በፅ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡

አምባሳደር ሳሚ እንደተናገሩት የሳውዲ አረቢያ የንግድ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ በመምጣት ያሉትን የንግድና ኢንቨስትመንት እድሎች ማወቅና ከአቻዎቻቸው ጋር በትብብር መስራት ይፈልጋሉ፡፡ በመሆኑም ከምክር ቤቱ ጋር በመሆን ኤግዚቢሽን ማዘጋጀት እንፈልጋለን ብለዋል፡፡

ኢንጂነር መላኩ በበኩላቸው ሁለቱ ሀገሮች የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ትስስር ያላቸው እንደሆኑ በማስታወስ በንገድና ኢንቨስትመንቱም ዘርፍ ግንኙነታቸውን የበለጠ ማጠናከርና ማሳደግ እንደሚገባቸው ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለሳውዲ አረቢያ ኤክስፖርት ልታደርጋቸው የምትችላቸው እንደ ቁም ከብት፣ የዶሮ ስጋ፣ ሰሊጥ፣ ቡና እና ወዘተ እንዳሉም ገልፀዋል፡፡ ሁለቱ ወገኖች የሚያዘጋጁት ኤግዚቢሽን ሁለቱን የቢዝነስ ማህበረሰብ የሚያቀራርብና የጋራ ተጠቃሚ ያደረጋቸዋል ብለዋል፡፡

ሁለቱም ወገኖች በየበኩላቸው ፈፃሚ ኮሚቴ በማቋቋም አስፈላጊ መረጃ በመለዋወጥና የድርጊት መርሃ ግብር እና የመግባቢያ ሰነድ በጋራ በማዘጋጀት ለኤግዚቢሽኑ ተግባራዊነት እንደሚሰሩ ተስማምተዋል፡፡

ፕሬዚደንቱ የሩሲያ ፌደሬሽን ግብርና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ኦፊሴላዊ ተወካይ አምባሳደርን ተቀብለው አነጋገሩ

የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ኢንጂነር መለአኩ እዘዘው ከዋና ፀሀፊ አቶ የሱፍ አደምኑር ጋር በመሆን የሩሲያ ፌደሬሽን ግብርና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ኦፊሴላዊ ተወካይ ሚስተር ኢርጎ ቢሊክን ዛሬ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም በፅ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡

በውይይታቸውም፤ ሁለቱ አገራት በዋነኛነት የግብርና ነክ ቢዝነስን አስመልክቶ ያላቸውን ትብብር፣ የኢምፖርት-ኤክስፖርት ግንኙነታቸውን ከፍ በሚያደርጉበት፣ በግብርና የኢምፖር-ኤክስፖርት ምርቶች ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ተሳትፎ በሚያሳድጉበት ረገድ እንዲሁም ምክር ቤቱና ተወካዩ በጋራ ሊሰሩ በሚችሉባቸው የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሄደዋል፡፡

ኢንጂነር መለአኩ እንደተናገሩት ኢትዮጵያና ራሽያ በትብብር ቢሰሩ የጋራ ተጠቃሚ የሚሆኑበት በርካታ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ዕድሎች ያላቸው መሆኑን በመጥቀስ ሁለቱ አገራት የረጅም ጊዜ ግንኝነት ያላቸውን ያክል የኢምፖርት-ኤክስፖርት ግንኙነታቸው የሚጠበቀውን ያክል እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊ ለእርሻ ተስማሚ መሬት ያላትና ኤክስፖርት ልታደርጋቸው የምትችላቸው እንደ ሰሊጥ፣ጥጥ እና የመሳሰሉ በርካታ የግብርና ምርቶች ቢኖራትም በምርጥ ዘር፤ በዘመናዊ መስኖ እና በዘመናዊ የእርሻ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ግብርና ባለመጠቀሟ በቂ ምርት አታመርትም ለዚህም የራሽያን በምርምር የተደገፈ ተሞክሮ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንፈልጋለን ብለዋል፡፡

ሚስተር ኢርጎ በበኩላቸው በዋነኛነት በግብርና ቢዝነስ ላይ በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው በመግለፅ ራሽያ ምርትን ለማሳደግ በሚረዱ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ በሽታ መከላከያ እና በመሳሰሉ ላይ የሚሰሩ የምርምር ተቋማት እንዳሏት ተናግረዋል፡፡

የሁለቱን አገራት በግብርና ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎችንም በቪድዮ ኮንፈረንስ በማገኛት የእውቀት፣ ተሞክሮና ልምድ ልውውጥ ለማድረግ እንዳቀዱም ሚስተር ኢርጎ አክለው ገልጸዋል፡፡

ሁለቱ ወገኖች በቀጣይ በመገናኝት የጋራ ጉዳዮችን በትብብር እንደሚሰሩ ተስማምተዋል፡፡

ፕሬዚደንቱ የኩባ አምባሳደር አምባሳደርን ተቀብለው አነጋገሩ

የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው ከዋና ፀሀፊ አቶ የሱፍ አደምኑር ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር ሚስስ ቪልማ ቶማስ እና ሶስተኛ ፀሀፊ ሚስተር አልበርቶ ሄርናንዴዝን ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም ተቀብለው አነጋገሩ፡፡

ሚስስ ቪልማ ወደ ምክር ቤቱ የመጡበት አላማ ኢትዮጵያና ኩባ በንግድና ኢኮኖሚ ላይ ያላቸውን ግንኙነት በሚያጠናክሩበትና ከፍ በሚያደርጉበት መንገዶች ላይ ለመወያየት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ የሁለቱ ሀገሮች የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት በጣም ዝቅተኛ በሚባል ደረጃ ላይ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ አገራቸው በተለይ የህክምና ቁሳቁስ ፋርማሲቲከል፣ የክትባት መድሀኒት፣ ቻርኮል፣ ስኳር እና የመሳሰሉ ምርቶችን ኤክስፖርት እንምታደርግ እና የምግብ ምርቶችን ደግሞ ከውጪ እንደምታስገባ በማስታወስ የሁለቱ አገራት የንግድ ማህበረሰቦች ተገናኝተው ቢሰሩ እና ምርቶቻቸውን በቀጥታ መገበያየት ቢችሉ የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚደንቱ በበኩላቸው እንደተናገሩት ሁለቱ አገራት በፖለቲካው ዘርፍ ካላቸው የረጅም ጊዜ ግንኙነት አንጻር የንግድና ኢኮኖሚ ግንኙነታቸው ዝቅተኛ በመሆኑ ሁለቱም ወገኖች በትብብር ጠንክረው መስራት ይገባቸዋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት የንግድ ምክር ቤቶች ግንኙነታቸውን የበለጠ በማጠናከር ሀገራቱ ያላቸውን የቢዝነስ እድሎች፣ የኤክስፖርት እና ኢምፖርት ምርቶች መረጃዎች መለዋወጥ እንዲችሉ እንዲሁም የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅሞ የንግዱን ማህበረሰብ በማገናኝት የጋራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይፋ በተደረጉት ሶስት መመርያዎች ዓላማ እና አፈጻጸም ዙሪያ ለንግዱ ማኅበረሰብ ግንዛቤ እና ማብራሪያ ለመስጠት የውይይት ተካሄደ

የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከኢትዮጵያ የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማኅበር ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይፋ በተደረጉት ሶስት መመርያዎች ዓላማ እና አፈጻጸም ዙሪያ ለንግዱ ማኅበረሰብ ግንዛቤ እና ማብራሪያ ለመስጠት የውይይት መድረክ መጋቢት 23 ቀን 2013 ዓም በሂልተን አዲስ ሆቴል አዘጋጀ፡፡

የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ኢኒጂነር መላኩ እዘዘው በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት ምክር ቤቱ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አንዱ እና ዋንኛው ንግድና ኢንቨስትመንትን የተመለከቱ ፖሊሲዎችና ህጎች ሲወጡ የግሉን ዘርፍ ፍላጎቶች እና ጥቅሞች ባስጠበቀ መልኩ መሆኑን ማረጋገጥ እና በወጡት ፖሊሲዎች ፣ አዋጆች እና መመሪያዎች ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠር ነው፡፡

አያይዘውም ሰሞኑን ይፋ በተደረጉ ሶስት መመርያዎች ዓላማ እና አፈጻጸም ዙሪያ ለንግዱ ማኅበረሰብ ግንዛቤ እና ማብራሪያ ለመስጠት እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ የፋይናንስ እና ባንክ ዘርፍ ተግዳሮቶች ዙሪያ ውይይት ማካሄድ እንዲቻል የብሔራዊ ባንክ የስራ ኃላፊዎች ፈቃደኛ በመሆናቸው አመስግነዋል፡፡

ብሔራዊ ባንኩ ባንኮች ከሚሰጡት ብድር 27 በመቶ ለህዳሴ ቦንድ ግዢ እንዲያውሉት የሚያስገድደው መመሪያ በማንሳቱ የባንኮችን የጥሬ ገንዘብ ቅርቦት ከፍ እንዲል ማድረጉ፤ በኮቪድ 19 ምክንያት ለተጎዱ ደንበኞቻቸው ጊዜያዊ የብድር እፎይታ እና ተጨማሪ ብድር ለመስጠት እንዲያስችላቸው ለግል ባንኮች 15 ቢሊየን ብር እንዲሰጥ ማድረጉ፤ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰበት የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ባንኮች ለሥራ ማስኬጃ የሚሆን ብድር በአምስት በመቶ ወለድ እንዲሰጡ ብሔራዊ ባንክ ገንዘብ ማዘጋጀቱን ያስታወቀ ሲሆን ለንግድ ባንኮች የአንድ ዓመት ብድር በአምስት በመቶ ወለድ እንዲቀርብ በማድረግ፤ አዳዲስ የደህንነት ገፅታዎች እና ሌሎች መለያዎች የተካተቱባቸው የብር ኖቶች መታተማቸው መደበኛ ባልሆነ መንገድ እንዲሁም ከፋይናንስ ተቋማት ውጭ የሚዘዋወረውን ገንዘብ ለመሰብሰብ ሙስናን እና የኮንትሮባንድን ስራ ለመቀልበስ አገልግሎት የሚውል ስራ ተሰርቷል፣ እንዲሁም የባንክ አገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋፋት የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትን እንደ ባንክ ለማቋቋም የሚያስችል መመሪያና የመሳሰሉት ስራዎች የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት የሚያግዙ ከ60 በላይ መመሪያዎች እንዲወጡ፤ እንዲሻሻሉ እና እንዲከለሱ በማድረግ አጠቃላይ ኢኮኖሚው ሳይንገራገጭ እንዲቀጥል በማድረግ ለግሉ ዘርፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያስገኙ በባነኩ የተወሰዱ ርምጃዎች ናቸው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል አንዳንድ መመሪያዎች የንግድ እንቅስቃሴው በተፈለገው መንገድ እንዳይራመድ እንቅፋት መሆናቸውን በመጥቀስ የግሉ ዘርፍ እንደ ብሔራዊ ባንክ ካሉ ወሳኝ አካላት ጋር በመገናኘትና ተሳትፎ በማድረግ የግሉ ዘርፍ በንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ላይ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመፍታት እንደዚህ አይነት የምክክር መድረኮችን ማዘጋጀቱ ተገቢ እንደሆነ ፕሬዚደንቱ አክለው ግልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ አበባ፣አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ በበኩላቸው ብዙ የአበባ፣አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች የዲያስፖራ አካዉንት ተጠቃሚ ባለመሆናቸው እንዲሁም አብዛኛዎቹ ንግድ ላይ ሳሆን ኤክስፖርት ላይ አተኩረው የሚሰሩ በመሆኑ የዘርፉን ልዩ ባህሪ ከግንዛቤ በማስገባት እድገቱ የበለጠ የሚፋጠንበትን አንድምታ መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረው እንደተናገሩት እነዚህ አምራቾች ስራ በመፍጠር እና በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ በመሆን የውጪ ምንዛሬ ለአገሪቱ የሚያስገኙ ስለሆኑ ከፖሊሲ አቅጣጫም ሲታይ የተለየ ማዕቀፍ ሊዘጋጅላቸው እና እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡

በዕለቱ ስሞኑን ይፋ በተደረጉ መመሪያዎች ማለትም ትውልደ ኢትዮጵያውያን በውጭ ምንዛሪ የሚያስቀምጡትን ገንዘብ በምን ዓይነት አግባብ መጠቀም እንደሚኖርባቸው በሚያመለክተው፣ አንድ ድርጅት ወይም ተቋም ከባንክ ውጪ መያዝ የሚችለው የገንዘብ መጠን ለመወሰን የወጣ መመሪያ እና ማንኛውም የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ ቢዝነስና ተቋም የሚያገኘው ውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምን የሚወስነው መመሪያን አስመልክቶ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የኦፐሬሽን ዘርፍ ምክትል ገዥ፤ አቶ ፈቃዱ ድጋፉ እና በባንኩ የፋይናንስ ተቋማት ሱፐርቪዥን ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ ገለፃ ከተደረገ በኋላ መድረኩን ለውይይት ክፍት በማደረግ በርካታ ጥያቄዎች፣ አስተያየቶች፣ ማብራሪያዎች ተስተናግደዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማህበር እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ አመራሮች፣ የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች የስራ ሃላፊዎችና ተወካዮች እንዲሁም በቀጥታ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አገልግሎት ሰጪዎች ተሳትፎ አድርገዋል፡፡

አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች በሚል ርዕስ ላይ የምክክር መድክ ተዘጋጀ

የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከፓን አፍሪካ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ጋር በመተባበር የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች በሚል ርዕስ ላይ የካቲት 18 ቀን 2013 ዓ.ም በራማዳ ሆቴል፣ አዲስ አበባ የምክክር መድክ አዘጋጀ፡፡

የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ኢኒጂነር መላኩ እዘዘው እንደገለፁት የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነትን አስመልክቶ እንዲህ አይነት ጉባዔ ሲዘጋጅ የንግዱ ማህበረሰብ ከዚህ ስምምነት ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ ከስትራተጂክ አኳያ በማሰነብና በመወያየት መሬት ላይ አውርዶ ለመስራት ሁል ጊዜ ከሚቀነቀንለት ጥቅምና ዋጋ ማግኘት ባሻገር ጉዳት ሊያስከትሉ በሚችሉ ነገሮችም ላይ አስቀድሞ መመካከር ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ስትነፃፀር በርካታ ሀብቶች ያሏት ብትሆንም በኢኮኖሚውና በቢዝነሱ ላይ የሚጠበቀውን ያክል በአገርም ሆነ በውጪ አገሮች ያልተጠቀመቻቸውና ያልሰራቻቸው ብዙ የቤት ስራዎች ያሉባት ሀገር ናት፡፡ ምንም እንኳን አሁን ባሉ በርካታ ችግሮች ምክንያት የውጪ ባለሀብቶችን ወደ አህጉሪቱ እንዲገቡና እንዲያለሙ ቢደረግም አፍሪካዊ ባለሀብቶች ያገኙትን የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ተቀብለው የሀጉሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት ማስቀጠል ይገባቸዋል፡፡

ፕሬዚደንቱ ጨምረው ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነትን አስመልክቶ እየተከተለችው ያለውን ስትራቴጂ በግልፅ በማስቀመጥ እና በመወያየት ብሎም በቀጣይ ሀሳቡን ወደ ንግዱ ማህበረሰብ በማስረፅ ጥሩ ተወዳዳሪ ነጋዴ ማህበረሰብ በመፍጠር ከስምምነቱ ተጠቃሚ በሚኮንበት መንገድ ላይ መነጋገር ያስፈልጋል ብለዋል

የፓን አፍሪካ የንግድና ኢንዱስትሪ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ክቡር ገና በበኩላቸው አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት በርካታ ዕድሎችን በማምጣት ረገድ ለአፍሪካ የኢኮኖሚ እድገትና ልማት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ በአንፃሩ ከዚህ ስምምነት በአግባቡ ተጠቃሚ ለመሆን በርካታ ተወዳዳሪ ምርቶችን የማምረት፣ ጠንካራ መሰረተ-ልማት የመገንባት፣ ጠንካራ የፋናንስ ስርዕት እና ተቋማት እነዲኖሩ የማድረግ፣ አመቺ የቢስነስ ከባቢዎችን መፍጠር፣ የተሳለጠ የማጓጓዣና የሎጂስቲክ አገልግሎቶች፣ የተደረጀ መረጃ ልውውጥ፣ የመሳሰሉትን ማሟላት የግድ እንደሚገባ አክለው አብራርተዋል፡፡

በእለቱ የክልል የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች እና የዘርፍ ማህበራት ፕሬዚደንቶች፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እና የዘርፉ ባለሙያዎች በምክክር መድኩ ላይ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡

በግልግል ዳኝነትና የእርቅ አሰራር ስርዓት ለመደንገግ በወጣ አዋጅ ላይ ዓውደ ጥናት ተካሄደ

የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎሺፕ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የካቲት 16 ቀን 2013 ዓም በደብሊዉ ቲ ሲ(WTC) የስልጠና ማዕከል፣ አዳማ ከተማ በግልግል ዳኝነትና የእርቅ አሰራር ስርዓት ለመደንገግ በወጣ አዋጅ ላይ ዓውደ ጥናት አካሄደ፡፡

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ዋና ፀሀፊ አቶ የሱፍ አደምኑር የእለቱን ፕሮግራም ሲያስተዋውቁ፤ ምክር ቤቱ ቀደም ብሎ የግልግል ዳኝነት ማዕከል በማቋቋም በንገዱ ማህበረሰብ መካከል የሚከሰቱ አለመግባባቶችን ለመፍታት እየሞከረ ቢሆንም ግልፅ የሆነ አዋጅና ደንብ ባለመኖሩ ሂደቱን የተሟላ ከማድረግ አኳያ ውስንነት ነበረው ብለዋል፡፡ ዋና ፀሀፊ ጨምረው እንደተናገሩት እነዚህን ችግሮች ለማቃለል የሚያስችል አዋጅ አሁን በመዘጋጀቱ የተሟላ የግልግል ዳኝነት ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ይቻላል ፡፡

የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ኢኒጂነር መላኩ እዘዘው በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸው፤ ምክር ቤቱ አዋጁን በማርቀቅ እና በማዳበር ሂደት ከፍተኛ ተሳትፎ ሲያደርግ እንደቆየና የግሉ ዘርፍ አቋሞች እና አስተያየቶችም የህጉ አካል እንዲሆኑ የሚያስችል ጥናት በጽሁፍ አንዳቀረበ ገልፀዋል፡፡

የአውደ ጥናቱ ርዕስ የሆነው የግልግል ዳኝነትና የዕርቅ አሰራር ስርዓትን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ የታለሙለት ዋና ዓላማዎች ማለትም፤ የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የመሳሰሉት አለመግባባቶችን በግልግል ዳኝነት መፍታት፣ የተከራካሪ ወገኖችን ህጋዊ መብትና ጥቅምን መጠበቅ፤ ኢትዮጵያ ተቀብላ ያፀደቀቻቸዉን ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ስምምነቶች ተግባራዊ ነት የሚያግዝ እንዲሁም ለነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ማደግ አስተዋፅኦ የሚያደርግ እና በዉጭ ሀገር ለተሰጡ የግልግል ዳኝነት ፍርዶች እዉቅና የሚሰጥ መሆኑ ለግሉ ዘርፍ እድገት ብሎም ለአጠቃላይ የኢኮኖሚያዊ ስርዓት መጎልበት ሚናው ከፍ ያለ ነው ብለዋል፡፡

አዋጁ ምክር ቤቱ ሲሰጥ የቆየውን የግልግል ዳኝነት በተሻለ ግልጽነት እና አሰራሩን በማሻሻል ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

የጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎሺፕ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ክቡር ፓስተር ዳንኤል ገብረስላሴ በበኩላቸው ተቋማቸው ለሰው ልጆች ፍትህ በማምጣት ዙሪያ ለረጅም አመት ያህል እየሰራ ቢሆንም ጠንካራ ኢኮኖሚ ሳይገነባ በድህነት አዙሪት ውስጥ ሆኖ ክብር ያለው ህይወት መኖር አለመቻሉን በመገንዘብ ከኢትዮጵያ የንግድ እና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና ከሌሎች የባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ኢኮኖሚያዊ ፍትህን ለማስፈን የሚደረጉ በርካታ ስራዎች ላይ እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

በእለቱ በግልግል ደኝነት አዋጅ ላይ የተደረገው አውደ ጥናት የዚህ ትብብር አንዱ አካል ማሳያ እንደሆነም ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ ዳይሬክተሩ አክለው እንተናገሩት ኢትዮጵያ የተጠቀመችባቸውን አለም የደረሰችበትን ኢኮኖሚን የሚያሳድጉ ስታንዳርዶችን በመውሰድ እና ሊሻሻሉ የሚገቡ የተለያዩ ስራዎችን በመስራት አገሪቷ ለዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ፍትህ ክፍት እንደሆነች ማሳየት ይገባናል፡፡

በዘርፉ ምሁራን አዋጁን አስመልክቶ ገለፃ ከተደረገ በኋላ መድረኩን ለውይይት ክፍት በማደረግ በርካታ ጥያቄዎች፣ አስተያየቶች፣ ማብራሪያዎች ተስተናግደዋል፡፡ በዓውደ ጥናቱ ላይ ከተወካዮች ምክር ቤት፣ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቢ ህግ፣ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የተለያዩ ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት የተወጣጡ የሰራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች እነዲሁም የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች ተሳትፎ አድርገዋል፡፡

ዋና ፀሀፊው የካሜሮን ልዑካን ቡድንን ተቀብለው አነጋገሩ

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ዋና ፀሀፊ አቶ የሱፍ አደምኑር በሚሰተር አንቶዮኔ ነኮሎ፣ የዶዋላ ካሜሮን የቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ጀነራል ማኔጀር የተመራ አስር አባላት የያዘ የካሜሮን ልዑካን ቡድንን የካቲት 5 ቀን 2013 ዓ.ም. በምክር ቤቱ አዳራሽ ተቀብለው በንግድና ኢንቨስትመንት እድሎች፣ አማራጮች እና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ አነጋገሩ፡፡

ዋና ፀሀፊው ምክር ቤቱ በዋናነት ንግድና ኢንቨስትመንትን የማስፋፋት፣ የምርምርና አድቮኬሲ ስራዎችን የመስራት፣ በአቅም ግንባታ የቢዝነስ ነክ ስልጠናዎችን የመስጠት እንዲሁም የግልግል አገልግሎቶችን እንደሚያከናውን አብራርተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ የንግድና ኢንቨስትመንት እድሎች እና አማራጮች ያሏት መሆኗን በማስታወስ የካሜሮን ባለሀብቶች በግላቸውም ሆነ ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር በመሆን በሀገሪቷ ውስጥ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ቢሰማሩ ትርፋማ ይሆናሉ ብለዋል፡፡ ምክር ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግላቸውም አቶ የሱፍ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ ስላለው የኢንቨስትመንና የንግድና ምቹ የሥራ ዕድል እንዲሁም በቀጣይ በጋራ ሊሠሩ በሚችሉባቸው የቢዝነስ ዘርፎች ላይ የፓወር ፖይንት ገለፃ ተደርጎላቸዋል፡፡ ለአነሷቸው ጥያቄዎችም ምላሽ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ምክር ቤቱ ከሩሲያ ሴንት ፒተርስበርግ የኢንቨስተሮች እና ኢንተርፕርነርች ማህበር ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከሩሲያ ሴንት ፒተርስበርግ የውጪ አገር ኢኮኖሚ ልማት እና አለም አቀፍ የቢዝነስ ትብብር የኢንቨስተሮች እና ኢንተርፕርነሮች ማህበር ጋር የስራ ግንኙነቱን እና ትብብሩን በማጠናከር ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ ለማከናወን የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ ጥር 27 ቀን 2013 ዓ.ም. በምክር ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ ተፈራረመ፡፡

የስምምነቱ ዋና አላማ በሁለቱ ተቋማት እና በንግዱ ማህበረሰብ መካከል የሚኖሩ የንግድና የኢንቨስትመንት ማስፋፊያዎችና ትብብሮችን ለማጠናከር እና ለማሳደግ ብሎም የጋራ ተጠቃሚ ለመሆን እንዲቻል ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ነው፡፡

በተጨማሪም አነስተኛና መካከለኛ ኢነተርፕራይዞችን ጨምሮ ልዩ የቢዝነስ እንቅስቃሴዎችና ማህበራዊ ፕሮጆክቶችን ለማሳደግና ለመተግበር፤ የልምድ ልውውጦችን ለማድረግ፤ ጠቃሚ የገበያ፣የፋይናንስ፣የፈጠራና የመሳሰሉ መረጃዎችን ለመለዋወጥ፤ ስራ ፈጠራን የሚያስፋፉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር፣ የቢዝነስ ፎረሞችን ለማዘጋጀት፤ በግሉና በመንግስት ትብብር የሚመሰረቱ የኢንቨስትመንት ፕሮግራችን ለመተግበር፤ በቢዝነስና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ወቅት የሚከሰቱ ችግሮችን በጋራ ለማሶገድ እና መሰል ተግባራትን በጋራ ለማከናወን ተስማምተዋል፡፡

ስምምነቱን የፈረሙት ከምክር ቤቱ በኩል ዋና ፀሀፊ አቶ የሱፍ አደምኑር ሲሆኑ ከሩሲያ ሴንት ፒተርስበርግ የኢንቨስተሮች እና ኢንተርፕርነሮች ማህበር ደግሞ የማህበሩ ሊቀመንበር ሚስተር ሩስላን አናቶሊቪች ማርክ ናቸው፡፡

የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ 341/95ን ለማሻሻል በተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት እየተደረገ ነው

የግሉን ዘርፍ እንዲደራጅ ማድረጉ ዘርፉ በሰለጠነና ውጤታማ በሆነ መንገድ ከሚመለከታቸዉ አካላት በተለይም ከመንግሥትና የልማት አጋሮች ጋር የጠነከረ ግንኙነትና ተሳትፎ እንዲኖረው ያግዛል፡፡ በተለይ ጠንካራና አብዛኛው የንግዱን ኀብረተሰብ ያካተተ ምክር ቤት መኖር ለሁለንተናዊ እድገት ዋና አጋዥ በመሆኑም የሀገሪቱን ልማትና እድገት የማፋጠን ሚና ይኖረዋል፡፡

ሆኖም ተደጋግሞ እንደተባለው፤ በኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እምነት አሁን ያለው የግሉ ዘርፍ አባልነት አሻሚ ፤ አደረጃጀቱ የተበታተነ፣ያልተቀናጀና የታለመለትን አላማ ለማሳካት ያላስቻለው ደካማ መሆኑ ከተግባር ተሞክሮ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በዚህ ረገድ ተደራራቢ እና የተከፋፈለ ድርጅታዊ መዋቅር መኖር፣ከላይ እንደተገለፀው በዚህ አዋጅ ሳይሆን በሌሎች ሕግች ተደግፈው በመደራጀት የሚንቀሳቀሱ የንግድና አምራች ማኀበር አባላት በመኖራቸው፣ እንዲሁም አንዳንድ ወገኖች ደግሞ ያለሕጋዊ ድጋፍ ተደራጅተው ለመንቀሳቀስ በመቻላቸው፣ ብዛት ያላቸው የንግድና አምራች ክፍል አባሎች ደግሞ ህጉ በሰጣቸው መብት መሠረት ከንግድና የዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤቶች መዋቅር ውጭ ለመሆን በመምረጣቸው ፤ በአዋጅ ቁጥር 341/1995 የተደራጁት የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ጠንካራ ሆነው አጥጋቢ እንቅስቃሴ አድርገዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡

ፕሬዚደንቱ ከፖላንድ ልዑካን ቡድን ጋር ውይይት አደረጉ

የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ኢንጂነር መለአኩ እዘዘው ከምክር ቤቱ ዋና ፀሀፊ አቶ የሱፍ አደምኑር ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የፖላንድ ኢምባሲ አምባሳደር ፕረዘሚስላው ቦባንክ እና በኢምባሲው የፖለቲካና ኢኮኖሚ ዘርፍ ቀዳሚ ፀሀፊ ሚስተር ማሴይጅ ችራኖውስኪን ታህሳስ 7 ቀን 2013 ዓ.ም. በጽ/ቤታቸው ተቀብለው በሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ትብብር እና በንግዱ ማኅበረሰቦች መካከል የሚኖረውን የቢዝነስ ትሥሥር በሚየሳድጉበትና በሚያጠናክሩበት ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደሩ፣ ኢትዮጵያ ስላላት የኢኮኖሚ ሁኔታ እና የቢዝነስ እድሎች መረጃዎችን ማወቅ እና የሁለቱ አገሮች ኢኮኖሚያዊ ትብብር እና ትስስር በሚያድግበትና በሚጠናከርበት አግባብ ላይ መወያየት እንደሚፈልጉ አስረድተዋል፡፡ ፖላንድ ከኢትዮጵያ እንደ ቅባት እህሎች፣ ቆዳና የቆዳ ዉጤቶች የመሳሰሉ የግብርና ውጤቶችን የምትጠቀም ቢሆንም ኢትዮጵያ ካሏት በርካታ ሀብቶች አንፃር በፖላንድ ገበያ ላይ በበቂ ሁኔታ አልተዋወቀችም ብለዋል፡፡ ሀገራቸው በግብርና እና በግብርና ማቀነባበሪያ ማሽነሪዎች፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በፈጠራ ቴክኖሎጂዎች እና በሌሎችም ዘርፎች ያደገች ሀገር እንድሆነች ጠቅሰው ለኢትዮጵያ አቻ የቢዝነስ ኩባንዎች የእውቀት ሽግግር ማድረግ እንደሚቻልም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚደንቱ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ሰፋፊ የእርሻ መሬት እና በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች እንዲሁም ኤክስፖርት ልታደርጋቸው የምትችላቸው እንደ ቡና፣ ሰሊጥ፣ የቁም ከብቶች እና ማእድናት ያሉ የግብርና ምርቶች ያሏት ሀገር ብትሆንም የሚጠበቀውን የምርት ብዛት፣ ጥራትና ጥቅም እያገኘች አለመሆነኗን በመጥቀስ በተለይም እንደ ግብርና መካናይዜሽን ያሉ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግሮችን እና ተሞክሮዎችን ከፖላንድ በማግኘት መማር ትፈልጋለች ብለዋል፡፡

ፕሬዚደንቱ አክለው እንደተናገሩት ፎረሞችን፣ ኤግዚቢሽኖችን፣ የቢዝነስ ትስስሮችን በመፍጠር የንግዱን ማህበረሰቦች በማገናኘት እና የሁለቱን አገሮች ምርቶችና የቢዝነስ እድሎች በሚገባ በማስተዋወቅ የኢኮኖሚ ትበብር፣ ትስስር እና የጋራ ተጠቃሚነትን ማሰዳግ ይገባል፡፡

ሁለቱ ወገኖች በቀጣይም በመገኛኘት የንግዱ ማህበረሰብ ግንኙነት እና የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ ትብብር በሚያሳድጉበት ረገድ የጋራ ስራዎችን እንደሚሰሩ ተስማምተዋል፡፡

ኢትዮ- አሜሪካ 2021 የንግድ ትርዒት ሊካሄድ ነው

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እና ኢትዮ ፕሮሞሽን በዋሽንግተን ዲሲ የንግድ ትርዒት በጋራ ለማዘጋጀት የሚያስችላቸውን የጋራ መግባቢያ ሰነድ ዛሬ ታህሳስ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ተፈራረሙ። ስምምነቱን የፈረሙት ከምክር ቤቱ በኩል ዋና ፀሀፊ የሱፍ አደምኑር ሲሆኑ የኢትዮ ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አበበ ፈለቀ ናቸው፡፡

በፊርማው ስነ ስረዓት ላይ የምክር ቤቱ ዋና ፀሀፊ እንዳሉት ኤግዚቢሽኖችን፣ አቻለአቻ የቢዝነስ ስብሰባዎች እና የተለያዩ የኔትወርኪነግ ግንኙነቶችን በማዘጋጀት እንዲሁም ከውጭ የሚመጡ ባለሀብቶችን በመቀበል ፣ የሀገር ውስጥ የቢዝነስ ተልኦኮዎችን ወደ ውጪ አገሮች ይዞ በመሄድ እና መሰል ተግባራትን በማከናወን ምክር ቤቱ ከተቋቋመበት ዋነኛ አላማዎች አንዱ የሆነውን የንግድና ኢንቨስትመንት ለማስፋፋት ጥረት ያደርጋል፡፡

ከዚህ ቀደም ምክር ቤቱ በራሱም ሆነ ከተለያዩ አካላት ጋር በመቀናጀት በየአመቱ ንግድ ትርኢቶችን ሲያዘጋጅ የነበረ መሆኑን አስታውሰው በእለቱ የሚደረገው የመግባቢያ ስምምነት ደግሞ በቀጣይ አሜሪካ የሚካሄደውን ኤግዚቢሽን ከኢትዮ ፕሮሞሽን ጋር በትብብር ለማዘጋጀት እና ሚሽን ይዞ በመሄድ እዚያ ያለውን ገበያ በተሸለ ሁኔታ ለማወቅ እንዲሁም አሜሪካ የሰጠችንን ከቀረጥ ነፃ የማስገባት እድል (Africa Growth and Opportunity Act - AGOA) የበለጠ ለመጠቀም ያስችላል ብለዋል፡፡

ኢትዮ ፕሮሞሽን ከምክር ቤቱ ጋር ለመስራት መወሰኑን አመስግነው ኤግዚቢሽኑን በተሳካ ሁኔታ ለማዘጋጅትና ለማካሄድ ምክር ቤቱ የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ዋና ፀሀፊው አክለው ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ የምትልካቸው ምርቶች እየጨመሩ እንደሆነና የታሰበው ኤግዚቢሥንም የበለጠ በማስገባት ረገድ በመጀመሪያዎቹ ተርታ እንደምትመደብ አቶ አበበ በበኩላቸው እንደተናገሩት ምክር ቤቱ በርካታ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ያሉት እና እንደዚህ አይነት ኩነቶችን በማዘጋጀት አባላቱን ተጠቀሚ በማድረግ ልምድ ያለው ተቋም መሆኑን ጠቅሰው አብረው መስራታቸው ለድርጅታቸውም ሆነ ለምክር ቤቱ የጋራ ጥቅም ያስገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እና ኢትዮ ፕሮሞሽን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ከሰኔ 18-19፣ 2013 ለሁለት ቀናት የሚያካሂዱት የንግድ ትርዒትና ባዛር በዋሽንግተን ዲሲ ጌይሎርድ ናሽናል ሪዞርትና ኮንቬንሽን ማዕከል የሚካሄድ ይሆናል ሲል ኢትዮ ፕሮሞሽን ገልጾልናል።

በዚሁ የንግድ ትርዒት ላይ አስመጪና ላኪዎች፣ አገልግሎት ሰጭዎች ፣ አምራቾች ፣ የፋይናንስ ተቋማት እና ሌሎች የንግድ ድርጅቶች እንደሚሳተፉ የሚጠበቅ መሆኑንም ኢትዮ ፕሮሞሽን ለምክር ቤታችን የላከው መግለጫ ይጠቁማል፡፡ የንግድ ትርኢቱ፤ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች የአፍሪካ ምርቶች ከቀረጥ ነጻ ወደ አሜሪካ እንዲገቡ የሚፈቅደው ህግ ሙሉ ተጠቃሚ ማድረግን፣ ለአሜሪካ የንግድ ተቋማት እና የንግድ ማህበረሰብ መሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ስላሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ግንዛቤ ማስጨበጥንና ለኢትዮጵያ ምርቶች እና አገልግሎቶች የአሜሪካን ገበያ ተደራሽነት የመፍጠር አላማዎችን የሰነቀ ነው። ከዚህ ሌላ የዝግጀቱ ታዳሚዎች የኢንቨስትመንት አማራጮችን የሚያገኙባቸውና እውቀትና ልምዳቸውን የሚለዋወጡባቸው ወርክሾፖችና የውይይት መድረኮችም ተመቻችተዋል። የኢትዮጵያን ባህል፣ ኪነጥበብና ታሪክ የሚያስተዋውቁ መሰናዶዎችም ከዝግጀቱ አካል ናቸው ተብሏል።

ይሄ የንግድ ትርዒት የኢትዮጵያን የንግድ ማህበረሰብ እጅግ ሰፊ ከሆነውና አሜሪካ ነዋሪ ከሆነው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ ጋር የሚያገናኝ ትልቅ መድረክ ሲሆን፤ የትውልደ ኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ኢትዮጵያ ውስጥ ስላሉ የፋይናንስ፣ የሪል ስቴት እና የሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች ግንዛቤ የሚጨብጡባቸው መድረኮችም ይዘጋጃሉ።

ፕሬዚደንቱ የክሪክ አምባሰደርን አነጋገሩ

የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ኢንጂነር መለአኩ እዘዘው ከምክር ቤቱ ዋና ጸኃፊ አቶ የሱፍ አደምኑር ጋር ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ ሆኖ በኢትዮጵያ፤ ጂቡቲ ፤ ደቡብ ሱዳን እና በአፍሪካ ህብረት የግሪክ አምባሳደር እና ቋሚ መልዕክተኛ አና ፋረሁንን ሕዳር 22 ቀን 2013ዓም ተቀብለው አነጋገሩ፡፡

አምባሳደር አና ፋረሁ ወደ ምክር ቤቱ የመጡበትን በማስረዳት ቀደም ሲል እንደ አ.ኤ.አ. ማርች 2019 በምክር ቤቱና በሄለኒክ ኢንተርፕራይዞች ፌደሬሽን መካከል የኢኮኖሚ ትብብር ለማስፋፋት እና የንግድ ግንኙነትን ለማጠናከር የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት በማስታወስ ለንግዱ ማህበረሰቦች የሁለቱን ሀገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ሀብቶች እንዲያዉቁ በማድረግ በመካከላቸው አጋርነት መፍጠር እና ግንኙነታቸውን ማጠናከር እንዲሁም የሀገራቱን ኢኮኖሚ ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ግሪክ በርካታ የግብርና ምርቶችን የምታመርት በመሆኑ ባለሀብቶቿ ኢትዮጵያ መጥተው በተለይም በግብርና ዘርፍ ከተሰማሩ የኢትዮጵያ ባለሀብቶች ጋር መገናኘትና በአጋርነት ኢንቨስት ማድረግ እንዲሁም የእውቀት ሽግግርም ማድረግ እንደሚፈልጉ አክለዋል፡፡ የግሪክ ባለሀብቶች በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዙሪያ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ሰፊ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸው፤ የተካሄደው ውይይትም በቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

ኢንጂነር መላኩ በበኩላቸው በምክር ቤቱ እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች እንዲሁም በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዕድሎች እና የግሪክ ባለሀብቶች ተሳትፎ ላቅ ያለ ደረጃ በሚደርስበት ጉዳዮች ዙሪያ ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡ ሁለቱም አገሮች የየራሳቸው የሆኑ የቢዝነስ እድሎችና አማራጮች ያሏቸው መሆናቸውን ገልፀው እነዚህን መረጃዎች በበቂ ሁኔታ ለንግዱ ማህበረሰብ በማድረስ በሁለቱ የንግዱ ማህበረሰቦች መካካል ያለውን ግንኙነት ማሳደግ እና የንግድና ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት ይገባልም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሰፋፊ መሬቶች ያላት ብትሆንም ዘመናዊ ግብርና እና ምርጥ ዘር የሌላት በመሆኗ በቂ ምርት አለማምረቷን ባላትም የግብርና ምርቶች እሴት ጨምራ እና በጥንቃቄ አሽጋ ለገበያ ማቅረብ አለመቻሏ፣ በርካታ የቱሪስት መስህቦች እንዲሁም ሌሎች ሀብቶች ቢኖራትም ከየዘርፉ የሚገባትን ጥቅም እያገኘች እንዳልሆነ ካስረዱ በኋላ ክሪክ በእነዚህ ዘርፎች ላይ ያላትን ተሞክሮ እና እዉቀት ለኢትዮጵያ እንድታካፍል ጠይቀዋል፡፡

በውይይታቸው ምክር ቤቱና ኤምባሲው የሁለቱን አገራት የንግድ ማህበረሰቦች ግንኙነት በሚያጠናከሩበትና የንግድና ኢንቨስትመንትን በሚያስፋፉበት ሁኔታ እንዲሁም ወደፊት በጋራ ሊሰሩ በሚችሉባቸው በርካታ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል፡፡

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በረቂቅ ንግድ ህጉ ዙረያ ዓውደ ጥናት እያካሄደ ነው

የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ህዳር 3 ቀን 2013 ዓም ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል በረቂቅ ንግድ ህጉ ዙረያ ወርክ ሾፕ(ዓውደ ጥናት) እያካሄ ደነው ፡፡

በዚህ ዓውደ ጥናት ላይም የኢፌዴሪ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ደኤታ ክቡር አቶ እሸቴ አስፋው፤ ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ክቡር አቶ ተስፋዬ ዳባ እንዲሁም የጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎሺፕ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ፓስተር ዳንሄል ገብረስላሴ ጨምሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተወጣጡ የሰራ ኃላፊዎች ተሳትፎ እያደረጉ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ኢኒጂነር መላኩ እዘዘው በዕለቱ ባሰሙት ንግግር ዘመናዊ፣ ከዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ ነባራዊ የዕድገትና የኢኮኖሚ ፖሊሲ አንፃር የተቃኘ፣ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው የንግድ ሥርዓት መኖር፤ በንግዱ ማህበረሰብና በአጠቃላይ በአገራዊ ዕድገት ውስጥ የሚጫወተው ሚና የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም፤ በሀገራችን ወጥነት ያለው የንግድ ህግ መኖር ለማንኛቸውም የንግድ እና ተያያዥ ስራ መስክ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ተብሎ በመታመኑ የንግድ ሕግ መድብል በኤፌዴሪ ጠቅላይ አቃቢ ህግ አማካኝነት ለረዥም ጊዜ በወሰደ እና ምክር ቤታችንን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ሰፊ ተሳትፎ ሲዘጋጅ ቆይቶ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀ ሲሆን ለተወካዮች ምክር ቤትም ተመርቷል፡፡ የዛሬው ዓውደ ጥናት ዓላማም በረቂቅ ህጉ የግሉን ዘርፍ በስፋት በማወያየት ግብሃት እንዲሰጥበት ለማስቻል ታስቦ የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎሺፕ ኢትዮጵያ በተገኘ ድጋፍ ያዘጋጀው መድረክ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ

በኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኔትወርኪንግ ማዕከል( Center for Investment Networking in Ethiopian (CINE)) መካከል በኢንቨስትመንት እና ንግድ ማስፋፋት ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የሁለትዮሽ የመግባቢያ ስምምነት ጥቅምት 16 ቀን 2012ዓ.ም ተፈረመ፡፡

በተጨማሪም በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኔትወርኪንግ ማዕከል( Center for Investment Networking in Ethiopian (CINE)) እና ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መካከል ተመሳሳይ የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሟል፡፡

ስምምነቱን የፈረሙት በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኔትወርኪንግ ማዕከል በኩል የማዕከሉ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ለማ ደገፋ ሲሆኑ በኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በኩልም የምክር ቤቱ ዋና ጸኃፊ አቶ የሱፍ አደምኑር ናቸው፡፡ በኢንቨስትመንት ኮሚሽን በኩልም ኮሚሺነር ሌሊሴ ነሚ ፈርመዋል፡፡

በፊርማ ስነስረዓቱ ላይም የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እንዲሁም ኢንጂነር መላኩ እዘዘውን ጨምሮ ከሶስቱም ተቋማት የተወከሉ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

በቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት የተቋቋመው በኢትዮጵ የኢንቨስትመንት ኔትወርኪንግ ማዕከል(CINE) በዋንኛነት ፤ የአገሪቱን የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለማሳደግ የሚረዱ የንግድ እና ኢንቨስትመነት ማስተዋወቅ፣ የውጪ ባለሀብቶች በአገራችን ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያበረታቱ ፎረሞችን የማዘጋጀት፣ የቢዝነስ ኔትወርኪንግ ስራዎችን በማበረታታት የአገራችን ባለሀብቶች ከውጪ አቻዎቻቸው ጋር በጋራ(JV) የሚሰሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት ዓላማው አድርጎ የተመሰረተ ነው፡፡

ከዚህም ባሻገር የአገራችን ባለሀብቶች በየዘርፎቻቸው የዕውቀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ምርትን እና ምርታማነትን ሊያሳድጉ በሚችሉባቸው ዘርፎች የስልጠና እና ተያያዥ ድጋፎችን ለማድረግ ታስቦ የተቋቋመ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትም በዋነኝነት ከተለያዩ ሀገራት ጋር በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ የአቻ ለአቻ የንግድ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት የኢትዮጵያ ነጋዴዎች እንደተሰማሩበት ወይም መሰማራት እንደሚፈልጉበት የዘርፍ አይነት የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ የማመቻቸት፤ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ የማገዝ እና ለንግድና ኢንቨስትመንት ማነቆ የሆኑ ችግሮች ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ የግሉ ዘርፍ የሚያድግበትና የሚጠናከርበትን ሁኔታ ማጎልበት ብሎም የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ አማካኝነት የንግዱ ማኀበረሰብን አንገብጋቢ ጉዳዮችንና ችግሮችን የሚፈቱበት ሁኔታን ማመቻቸት ናቸው ፡፡

ከዚህም ባሻገር የግሉን ዘርፍ ጥቅም ለማስከበር መንግስትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚያካሂዷቸው አካባቢያዊና አለም አቀፍዊ የንግድና ኢንቨስትመንት ስምምነቶች፣ ድርድሮችና ፕሮግራሞች ላይ የነቃ ተሳትፎ ያደርጋል፣ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሞ በጋራ በመስራት ለአገር ምርቶችና አገልግሎቶች አዳዲስ የገበያ ዕድሎችን ያፈላልጋል፣የንግድ ነክ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት የንግዱ ማኀበረሰብ በፖሊሲዎችና በአሰራሮች ላይ በቂ ዕውቀት እንዲኖረው እንዲሁም ማኀበራዊ ኃላፊነቱን አውቆ ሥነ ምግባርን በጠበቀ ሁኔታ እንዲሰራ ያበረታታል፡፡

በመሆኑም የሁለቱ ተቋማት በጋራ ለመስራት መወሰናቸው ለአገራችን የወጪ ዘርፍ ዕድገት ብሎም ለውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መጎልበት ላቅ ያለ ድርሻ እንደሚኖረው በወቅቱ የተገለጸ ሲሆን ከሶስቱም ወገን የተወጣጣ የቴክኒክ ኮሚቴ ለማቋቋምም ከስምምነት ተደርሷል ፡፡

ፕሬዚደንቱ ከባንግላዲሽ አምባሳደር ጋር ተወያዩ

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት መልአኩ እዘዘው (ኢንጂነር) ከምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ የሱፍ አደምኑር ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የባንግላዲሽ አምባሳደር ሚስተር ታሪክ ሀሰንን ነሀሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም. በፅ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ ፡፡

አምባሳደሩ ወደ ምክር ቤቱ የመጡበት ዓላማ ስለ ግሉ ዘርፍ ተገቢውን መረጃ ለማግኘት እና በባንግላዲሽ እና በኢትዮጵያ የንግድ ማኅበረሰቦች መካከል ያለው የቢዝነስ ግንኙነት በሚጎለብትበት ሁኔታ ላይ ለመወያየት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ መናሀሪያ ማዕከልና በኢኮኖሚዋ በፍጥነት እያደገች ያለች አገር በመሆኗ ኢምባሲያቸው መልካም ግንኙነትን ማሳደግ እንደሚፈልግ እና የሁለቱን አገራት ንግድና ኢንቨስትመንት በማስፋፋት ተባብረው እንደሚሰሩ ጨምረው ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአብዛኛው የባንግላዲሽን ምርቶች የምታስገባው በቀጥታ ሳይሆን እንደ ጅቡቲና ሶማሌ ላንድ ባሉ ሌሎች አገሮች አማካኝነት መሆኑን የተናገሩት ሚስተር ታሪክ በተለይም እንደ ህክምና መድሀኒት የመሳሰሉ ምርቶችን በቀጥታ ከአገራቸው ብታስመጣ ከሌሎች አገሮች ከምትገዛቸው እጅግ ባነሰ ዋጋ በመግዛት ተጠቃሚ እንደምትሆን ጠቁመዋል፡፡

የአምባሳደሩን መልካም ሀሳብ የተቀበሉት የምክር ቤቱ ፕሬዚደንት በበኩላቸው ባንግላዲሽ በጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የተሻለ ልምድ ያላት ሀገር መሆንዋን አስታወስው ኢትዮጵያም ከመልካም ተሞክሮዋም መማር እንደምትችልና በዚህ ዘርፍ የሚሰማሩ የውጪ ኢንቨስተሮችንም እየጋበዘች እንደምትገኝ አብራርተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአብዛኛው ወደ ውጪ የምትልካቸው የቡና፣ የሰሊጥ፣ የአትክልት፣ የስጋ፣ የቁም ከብቶችና የመሳሰሉት በርካታ የግብርና ምርቶች እንዳሏትም ገልፀዋል፡፡ ከኢትዮጵያ የንግድ ምክር ቤት ዋነኛ ተግባራት መካከል አንዱ የንግዱ ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ ማፈላለግ ነው ያሉት ፕሬዚደንቱ የሁለቱም ሀገራት ምክር ቤቶች መልካም ግንኙነታቸውን በማጠናከር በየሀገራቱ ያሉትን የቢዝንስ አማራጮች፣ የተፈጥሮ ሀብቶቻቸውን እና ልዩ ልዩ የንግድና የኢንቨስትመንት መረጃዎችን ለንግዱ ማህበረሰብ በወቅቱ ማድረስ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

ሁለቱም ወገኖች ወደፊት የጋር ተግባራትን በማከናወን የሁለቱ አገራት የንግድ ማህበረሰቦች የቢዝነስ ግንኙነቶች እንዲጠናከር እና እርስ በርስ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በሚሰሩበት ሁኔታ ላይ በስፋት ተወያይተዋል::

በመመሪያ ቁጥር 64/20/12 ተጠቃሚ የምትሆኑ ግብር ከፋዮች የተሰጠው ጊዜ ከሚያዝያ 28 እስከ ግንቦት 27 ቀን 2012ዓ.ም ብቻ መሆኑን አውቃችሁ ተጠቃሚ እንዲትሆኑ ለማስታወስ እንወዳለን፡፡

የፌደራል ግብር ከፋይ ሆናችሁ የሚኒስትሮች ም/ቤት በወሰነው መሠረት የእዳ ምዕረቱ የሚመለከታችሁ ግብር ከፋዮች በሙሉ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃትና ኢኮኖሚውን በመደጎም ግብር ከፋዮች ወደ ንግድ እንቅስቃሴ ገብተው የምርትና አገልግሎት አቅርቦት እንዲሳለጥ፣ ድርጅቶች ሰራተኞቻቸውን በስራ ላይ እንዲያቆዩ እና ግብር ከፋዮች ቫይረሱን ለመከላከል ለሚደረገው እንቅስቃሴ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ የሚኒስተሮች ም/ቤት የግብር ዕዳ ስረዛ የመክፍያ ጊዜ ማራዘምና የሚከፍሉትን ለማበረታታት መመሪያ ቁጥር 64/20/12 ማውጣቱ ይታወሳል፡፡

በዚህ መሰረትም የገቢዎች ሚኒስቴር ከሚያዝያ 28 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ግብር ከፋዮች ተጠቃሚ እንዲሆኑና በሁሉም ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ተግባራዊ መሆን መጀመሩን መግለጫ ማውጣቱ ይታወቃል፡፡

በመሆኑም በመመሪያው ተጠቃሚ የሚትሆኑ ግብር ከፋዮች ከተጠቀሰው ቀን ማለትም ከግንቦት 27/12 ዓ.ም በኋላ የምትመጡ ግብር ከፋዮች የእዳ ምዕረቱ ተጠቃሚ እንደማትሆኑና በመደበኛ አሰራር እንደምትጠየቁ የገቢዎች ሚኒስቴር የገለጸ ሲሆን በቀሩት 3 ቀናት ውስጥ ማለትም እስከ ግንቦት 27/12 ዓ.ም ተጠቃሚ እንድትሆኑ ለማስታወስ እንወዳለን፡፡

የኢትዮጵያ የንግድ እና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት

ምክር ቤቱ ከትሬድ ማርክ ኢስት አፍሪካ ተቋም ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ

የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና ትሬድ ማርክ ኢስት አፍሪካ በጋራ ለመስራት ግንቦት 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በምክር ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ፡፡

የምክር ቤቱ ዋና ፀሀፊ አቶ የሱፍ አደምኑር እንደገለፁት ቀደም ሲል ምክር ቤቱ እና ትሬድ ማርክ ኢስት አፍሪካ በተለይም ንግድን ከማሳለጥ ረገድ የነበረውን የአገር ውስጥ ምርት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት (Origin of Certificate) አሰጣጥን ከማንዋል አሰራር ወደ ዲጂታል ለመለወጥ፣ የመረጃ ቋትን በማሳደግ የአባላትን መረጃ ብቁ ማድረግ እና የምክር ቤቱን አጠቃላይ የኢንፎረሜሽን ሲስተም የማሻሻል የፕሮጀክት ሀሳቦች ላይ አብረው ለመስራት ሲወያዩ ቆይተው ለዉሳኔ በመድረስ ወደ ዛሬው የመፈራረም ሰነስርዓት ተደርሷል፡፡

ፕሮጀክቱ አራት መቶ ሺ የአሜሪካን ዶላር የሚሸፍን ሆኖ በሚቀጥሉት 3 አመታት የሚፈፀም መሆኑን የጠቀሱት ዋና ፀሀፊው ድርጅቱ ያደረገው ድጋፍ ምክር ቤቱን አሁን ካለበት ወደ ተሻለ አሰራር ሂደት የሚወስደው ነው ብለዋል፡፡ ስለ ድጋፉ በምክር ቤቱ ስም በማመስገን በቀጣይም በተመሳሳይ ስራዎች ላይ ከድርጅቱ ጋር በጋራ ብዙ ስራ መስራት እንደሚቻል አቶ የሱፍ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

የትሬድ ማርክ ኢስት አፍሪካ በኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ታደሰ ተፈራ በበኩላቸው እንደተናገሩት ድርጅታቸው በምስራቅ አፍሪካ ላይ ለመስራት ከ10 ዓመት በፊት ስራ የጀመረ መሆኑን በመጥቀስ፤ የተቋቋመውም ንግድን በመደገፍ የንግድ ስራዎች እንዲቀላጠፉ በማድረግ አገሮች ብልጽግና እንዲያመጡ ለመደገፍ እንደሆነ እና በኢትዮጵያም ላይ ለመስራት ከዛሬ ሁለት አመት በፊት ከመንግስት ጋር ተፈራርሟል ብለዋል፡፡ ድርጅቱ ላለፉት 10 አመታት የሰራው ስራ በገለልተኛ አካል ተገምግሞ የንግድ ወጪን (Trade Cost) በ10% በመቀነስ እና አገሮች የውጪ ንግዳቸውን እስከ 25% እንዲያሳድጉ በማድረግ የሰራ መሆኑ በመረጋገጡ ይህን ዉጤትም ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት እየተሰራ ነው፡፡

ድርጅቱ ንግድን በማሳለጥ፣ በትራንስፖርት፣ በኢንፍራስትራክቸር፣ በሎጂስቲክ፣ በቀጠና አገሮች ትስስር፣ በንግድ ተወዳዳሪነት እና በነጋዴ ሴቶች ድጋፍ እና በመሳሰሉት ዘርፎች ላይ እንደሚሰራም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ ከምክር ቤቱ እና ከድርጅቱ የተውጣጡ የበላይ ሃላፊዎች የተገኙ ሲሆን ሁለቱ ተቋማት በቀጣይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ዋና ጸሐፊ የቤልጂየም አምባሳደርን በጽ/ቤታቸው አነጋገሩ

የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ የሱፍ አደምኑር በኢትዮጵያ የቤልጂየም አምባሳደር ፍራንኮይዝ ዱሞንትን እና ባልደረባቸውን የንግድና ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ኤሪክ ሳንትኪንን የካቲት 18 ቀን 2012 ዓ.ም. በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ፤ በሁለቱ ሀገራት የንግዱ ማኅበረሰቦች መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትሥሥር በሚያጠናክሩበት ሁኔታም ተወያይተዋል፡፡

በአዲስ አበባ የንግድ ጉብኝት የሚያደርጉ የቤልጂየም ኩባንያዎችን ይዘው የመምጣት ፍላጎት እንዳላቸው የገለጹት አምባሳደሩ በተለይ በጨርቃጨርቅ፣ በዕፅዋት ግብርና፣ ታዳሽ ኃይል፣ ብረት፣ ፋርማሴውቲካልስ ማኑፋክቸሪንግና ሎጂስቲክስ በመሳሰሉት ዙሪያ በሁለቱ በቤልጂየምና በኢትዮጵያ ኩባንያዎች መካከል ዘርፈ ብዙ የአቻ ለአቻ ውይይት መድረኮችን ከምክር ቤቱ ጋር በጋራ ለማዘጋጀት ማሰባቸውን ተናግረዋል፡፡

የአነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የትላልቅ ኢንዱስትሪዎች መሠረት በመሆናቸው በተለይ ኢንተርፕራይዞቹ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በሚተሳሰሩበት ላይም በትብብር መሥራት እንደሚቻል ጠቅሰዋል፡፡

የአምባሳደሩን ፍላጎት የተቀበሉት የምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ የምክር ቤቱን ተግባርና ኃላፊነት አስረድተዋቸዋል፡፡ አይይዘውም በኢትዮጵያ በኩል ሊኖር ስለሚችለው ፍላጎትና አቅምም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ እያደገ ያለውን ኢኮኖሚዋን ማስቀጠል እንደምትፈልግና ምክር ቤቱ ከቤልጂየም ኤምባሲ ጋር የሚያደርገው ቀጣይ ትብብር በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነም ጨምረው አብራርተዋል፡፡

በመጨረሻም በቀጣይ የታሰበውን መድረክ ማዘጋጀት በሚችሉበት ዝርዝር ነጥቦች ላይ ተወያይተዋል፡፡

ምክር/ቤቱ በዋሽንግተን ዲሲ የአለም ዓቀፍ የገንዘብ ተቋም ከፍተኛ ኢኮኖሚስት እና የገቢዎች አስተዳደር ክፍል ም/ሀላፊ ተቀብሎ አነጋገረ

የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት መልአኩ እዘዘው(ኢንጅነር) ከምክር ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ጋር በጋራ በዋሽንግተን ዲሲ የአለም ዓቀፍ የገንዘብ ተቋም ከፍተኛ ኢኮኖሚስት ሚስስ ረብቃ ስፓርክማን እና የገቢዎች አስተዳደር ክፍል ም/ሀላፊ ሚስተር አንድሪው ኦኬሎን የካቲት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. በፅ/ቤታቸው ተቀብለው በሀገሪቱ ውስጥ ስላለው የጉሙሩክ፤ ቀረጥና የግብር አሰባሰብ ስርዓት ላይ አነጋገሩ፡፡

ከገቢዎች ሚኒስቴር እና ጉሙሩክ ኮሚሽን የተሻለ ስልት በመከተል ተገቢውን የጉሙሩክ ቀረጥ እና ግብር መጠን መሰብሰብ እንዲችሉ ቲክኒካዊ ድጋፍ እንደሚሰጡ የተናገሩት የአለም ዓቀፍ የገንዘብ ተቋም ከፍተኛ ኢኮኖሚስት ሚስስ ረብቃ ስፓርክማን ፡፡ ወደ ምክር ቤቱም የመጡት ከንግዱ ማህበረሰብ ላይ የጉሙሩክ ቀረጥና ግብር የሚሰበሰብትን ሁኔታና የአሰራር ሂደቱን ለመረዳት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ኢንጅነር መልአኩ በበኩላቸው ምክር ቤቱ ከአገር አቀፍ ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ ለተዋቀሩት የገቢዎችና የግምሩክ መስሪያቤቶች ባለድረሻ አካል እንደሆነ እና አዋጆችና ህጎች ሲረቀቁ ተገቢውን ግብአት በመስጠት ረገድ ተሳትፎ እንደሚያደርግ አንስተዋል፡፡

የአንድ መስኮት ኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት አሰጣጥንም አስምልክቶ ከሚመለከታቸው ጋር በላቀ መነሳሳት አብረው እየሰሩ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ሆኖም ግን ቀረጥና ግብርን አስመልክተው በተደጋጋሚ በሚወጡ አዋጆች፣ ህጎችና መመሪያዎች ዙሪያ የንግዱ ማህበረሰብ በየጊዜው የግንዛቤ ማስጨበጫና አጫጭር ስልጠናዎች ሊያገኝ ይገባልም ብለዋል፡፡

በፌደራል ደረጃ የተቋቋመው የቀረጥ አሰባሰብ ቅሬታ ተቀባይ ኮሚሽን በንግዱ ማህበረሰብ በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆን በክልሎችም ደረጃ ቢቋቋም መልካም እንደሆነ ሀሳብ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚደንቱ ከስሪ ላንካ አምባሳደር ጋር ተወያዩ

የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት መልአኩ እዘዘው (ኢንጂነር) ከምክር ቤቱ ዋና እና ምክትል ዋና ጸሐፊ ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የስሪ ላንካ አምባሳደር ሱጌሽዋራ ጉናራትናን እና ባልደረባቸውን የቀድሞውን አምባሳደር ሱሚዝ ዳሳናያኬን የካቲት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ተቀብለው አነጋገሩ፤ በሁለቱ ሀገራት የንግዱ ማኅበረሰቦች መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትሥሥር በሚያጠናክሩበት ሁኔታም ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደር ጉናራትና እንደተናገሩት ባለፈው ህዳር ወር የተካሄደውን የኢትዮጵያ-ስሪ ላንካ ቢዝነስ ፎረም ተከትሎ በስሪ ላንካ በማሽነሪ ምርት ዕውቅና ያተረፈውን ቀዳሚ የኮንስትራክሽን ኩባንያን ጨምሮ በርካታ የሀገራቸው ኩባንያዎች በመጪው መጋቢት ወር መጨረሻ ገደማ ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር ለመወያየት ያደረባቸውን ፍላጎት ለፕሬዚደንቱ አስረድተዋል፡፡

የአምባሳደሩን ጥያቄ የተቀበሉት የምክር ቤቱ ፕሬዚደንት ሀገራቸው በማደግ ላይ ያለች ሀገር እንደመሆኗ የውጭ ኢንቨስትመንትን በእጅጉ እንደምታበረታታ ገልጸው በተለይ አሁን ያለውን የተዛባ የገቢና ወጪ ምርት ሚዛን ለማስተካከልም ሆነ የውጭ ምንዛሪን እጥረት ለማስተካከል እንዲረዳ በማሽነሪ ምርት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት በእጅጉ ትፈልጋለች፡፡

በሀገራት መካከል የሚደረግ ማንኛውም አጋርነትና ትብብር በእርስ በርስ መጠቃቀም ላይ የተመሠረተ መሆን ስለሚገባው እንዲህ ዓይነቱ ኢንቨስትመንት ለሀገራቸው ዕድገት ጠቃሚ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

የስሪ ላንካ ኩባንያዎች የኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ስሪ ላንካ እንዲመጡ እንደሚፈልጉም አምባሳደሩ ገልጸው በጉዳዩ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

በርካታ የስሪ ላንካ ኩባንያዎች በሀዋሳ የኢንዱስትሪ መንደር በተለይም በአልባሳት ምርት ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙና የንግድ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ማስፋፋት እንደሚፈልጉም አምባሳደሩ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

አይ.ቲ.ኤም.ኢ. አፍሪካ 2020 ንግድ ትርዒት በይፋ ተከፈተ


ለሦስት ተከታታይ ቀናት ክፍት ሆኖ የሚቆየው ዓለም አቀፍ የጨርቃ ጨርቅ ምህንድስናና ማሽነሪ ንግድ ትርዒት (አይ.ቲ.ኤም.ኢ-አፍሪካ 2020) የካቲት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. የኢትዮጵያና የህንድ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የመጡ የቢዝነስ ተወካዮችና የኩባንያ ባለቤቶች በታደሙበት በአዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽ በደማቅ ሁኔታ ተከፈተ፡፡

ይህ ተከታታይነት ያለውና ታላቅ መድረክ ‹‹በጨርቃጨርቅ ቴክኖሎጂ አፍሪካን ማበልጸግ›› በሚል ርዕስ በህንድ የአይ.ቲ.ኤም.ኢ. ሶሳይቲ እና በኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን በአፍሪካ ብሎም ከአፍሪካ ባሻገር ላለው ዓለም በጨርቃጨርቅ ኢንቨስትመንትና በቴክኖሎጂ ፈጠራ አዲስ ለውጥ መፍጠር ላይ ያለመ ነው፡፡ በተጨማሪም የአፍሪካ የጨርቃጨርቅ ቴክኖሎጂ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ አሻራውን እንዲጥል የታሰበም ነው፡፡

በአነስተኛ ምርትና ጥራት እንዲሁም በደካማ የማኔጅመንት መዋቅርና በክህሎትና ሥልጠና ውስንነት ሳቢያ የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ በዓለም ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ የመሆን አቅም እንዳላጎለበተ የተናገሩት ፕሬዚደንቱ መድረኩ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ዕውቅ የቢዝነስ መሪዎችንና ኩባንያዎችን ያሰባሰበ እንደመሆኑ ለአፍሪካ ባለሀብቶች የተሻለ ልምድና ተሞክሮ የሚፈጠር ነው ሲሉ እምነታቸውን ገልጸዋል።

የህንድ አይ.ቲ.ኤም.ኢ. ሶሳይቲ ሊቀመንበር አቶ ሃሪ ሻንካር በመግቢያ ንግግራቸው ላይ አፍሪካ የህንድ ዋነኛዋና ቀጣይዋ የንግድ ሸሪክ እንደመሆኗ በተከታታይ በሚዘጋጀው በዚህ ንግድ ትርዒት የጨርቃጨርቅ ምህንድስናና ኢንዱስትሪን አፍሪካ ውስጥ የማጎልበት ፍላጎት በእጅጉ አላቸው፡፡

የምክር ቤቱ ፕሬዚደንት ኢንጂነር መልአኩ እዘዘው በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው የሁለቱ ሀገራት የንግዱ ማኅበረሰብ ግንኙነት የንግድ ግንኙነታቸውን ከማጠናከር ባሻገር የሀገራቱን የሁለት ምዕተ ዓመት የንግድ ግንኙነት የሚዘክር ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ተካ ገብረየሱስ በበኩላቸው መድረኩ በኢትዮጵያ ላይ መዘጋጀቱ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ አህጉር ለግሉ ዘርፍ ጭምር ተስፋ ሰጪ የጨርቃጨርቅ ቴክኖሎጂ ዕድገት የሚያመጣ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት የዓለም አቀፍ ንግድ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሚስ ዶሮዚ ቴምቦ የኢኮኖሚ ዕድገት ማለት ለአፍሪካ ልጆች የኑሮ ፈተናን የማሸነፍ ጉዳይ እንደመሆኑ በጨርቃጨርቅም ሆነ በሌሎች የልማት ዘርፎች ላይ የሚደረገው ትብብርና አብሮ መሥራት እጅግ ወሳኝ ነው ሲሉ አስምረውበታል፡፡በቀጣይ ሁለት ቀናቶች የድርጅቱ ልዑካን ቡድን በዚሁ ጉዳይ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚወያይም ታውቋል፡፡


እ.ኤ.አ. ከ2017-18 ባለው ጊዜ ውስጥ የህንድና የኢትዮጵያ ንግድ ምጣኔ 1.27 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሲሆን ህንድ ወደ ኢትዮጵያ የላከችው 1.22 ቢሊዮን ዶላር ከኢትዮጵያ ያስገባቸው ደግሞ 45 ሚሊዮን ዶላር እንደሚደርስ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያመለክት በመድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡

ከኢንቨስትመንት አንፃርም በደረጃ ህንድ የኢትዮጵያ 2ኛ የኢንቨስትመንት አጋር ስትሆን የተረጋገጠው የኢንቨስትመንት መጠንም 4ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሆነ ታውቋል፡፡

ከ15 የአፍሪካ፣ ኢሲያና አውሮፓ ሀገሮች የተውጣጡ ከ100 በላይ ኩባንያዎች በንግድ ትርዒቱ ላይ የተሳተፉ ሲሆን በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት የአቻ ለአቻ ውይይቶች፣ የፋይናንስ ጉዳዮች፣ ባህላዊ መድረኮችና የቴክኖሎጂ ሴሚናር እንደሚካሄድ የተገለጸ ሲሆን የተሳታፊዎችን ዕድል የሚያሰፋ እንደሆነም ተነግሯል፡፡ከምክር ቤቱ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት እና ከጽ/ቤት የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን የዓለም የንግድ ድርጅት ም/ዋና ዳይሬክተር አነጋገሩ

የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት መልአኩ እዘዘው (ኢንጅነር) ከምክር ቤቱ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት እና ከጽ/ቤት የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን የዓለም የንግድ ድርጅት ም/ዋና ዳይሬክተር ሚስተር አለን ዎልፍ የሚመራውን ልዑካን ቡድን የካቲት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. በምክር ቤቱ ቦርድ መሰብሰቢያ አዳራሽ ተቀብለው ኢትዮጵያ በአለም ንግድ ድርጅት አባል በምትሆንበት ሂደት ዙሪያና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ አነጋገሩ፡፡

ኢትዮጵያ ላለፉት ስምንት ዓመታት ተንጠልጥሎ የነበረው የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ድርድር ጥያቄ በማንቀሳሰቀስ በርካታ ስራዎች እያከናወነች መሆኗን ያደነቁት ም/ዋና ዳይሬክተሩ ድርጅቱ በመላው ዓለም የሚካሄዱ የንግድ መስተጋብሮችን የሚመራ ዓለም አቀፍ ህግን የሚተገብር እንደሆነና በሃገራት መካከል የሚካሄዱ የንግድ እንቅስቃሴዎች ደንቦች የሚመለከት እና አባል ሀገራት የንግድ ስምምነቶች ላይ ድርድር የሚያካሂዱበት እና በንግድ አማካይነት የሚከሰቱ ግጭቶች መገላገያ መድረክም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ ከአለም አቀፍ ባንክ፣ ኤይ ኤም ኤፍ፣ አለም አቀፍ የንግድ ማእከል እና የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የመሳሰሉት ድርጅቶች ወደ አባልነት ለሚደረገው ድርድር ሂደት ንግድ ነክ ትብብርን እና የአቅም ግንባታና ስልጠናን አስመልክቶ የቴክኒክ እገዛ እንደሚያደርግም ተናገረዋል፡፡

የምክር ቤቱ ፕሬዚደንት በበኩላቸው እንደ ንግዱ ማህበረሰብ ተወካይነት ኢትዮጵያ የአለም ዓቀፍ ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እያደረገችው ላለው ሂደት ደጋፊና ተባባሪ ነን ይህም ደግሞ የአለም አቀፋ ውህደት ለንግሉ ዘርፍ ብሎም ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት አስፈላጊ እንደ ሆነ ተናግረዋል፡፡ በአሁን ወቅት በሀገሪቱ ልግሉ ዘርፍ የጎላ ትኩረት እየተሰጠው በመሆኑ የግሉን ዘርፍ እንደ ዋነኛ የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ በመቁጠር መንግስት የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድግ ላይ ይገኛል፣ ይህ ደግሞ በአለም አቀፍ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ያደርጋል፤ ድርጅቱንም በአባልነት ለመቀላቀል የሚደረገውን ጉዞ ያቀላል፡፡

ኢትዮጵያ በጨርቃጨርቅ፣ በቆዳ፣ በቁም ከብት በመሳሰሉት የግብርና ዘርፎችና በአግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፍም ተነፃፃሪ ጥቅሞች ያላት አገር እንደ ሆነች እና የድርጅቱ አባል ለመሆንም ከፍተኛ ጥረት እያደረገች መሆነኗን በማስረዳት ታዳጊ አገር በመሆኗ በተለይም ገና በማቆጥቆጥ ላይ ላሉ ኢንዱስትሪዎች፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራዞች የሰው ሀይል በአለም አቀፍ የስልጠና ስርዓት የተቃኘ የቴክኖሎጂና የእውቀት አቅም ግንባታ ለማግኘት ከድርጅቱ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል፡፡

አገሪቷ በድርጅቱ አባል ለመሆን በምታደርገው እንቅስቃሴና ድርድር ሂደት ውስጥ ምክር ቤቱ ከመንግስት ጋር በመሆን የተቻለውን ሁሉ እየሰራ እንደሆነና የምክር ቤቱ ዋና ፀሀፊም የቴክኒክ ኮሚቴ አባል እንደሆነ ጨምረው የገለፁት ፕሬዚደንቱ የድርጅቱ ሴክሬተሪያት ይህን ተመልክቶ የግሉ ዘርፍ ተሳታፊ የሚሆንበትና የሀገሪቷን ኢኮኖሚ በማሳደግ ቀዳሚ ሚና የሚጫወትበትን ምህዳር እንዲያመቻችም ጠይቀዋል፡፡

በቀጣይ ሁለት ቀናቶች የድርጅቱ ልዑካን ቡድን በዚሁ ጉዳይ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚወያይም ታውቋል፡፡

ምክር ቤቱ ከካናዳ-አፍሪካ ቢዝነስ ምክር ቤት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና የካናዳ-አፍሪካ ቢዝነስ ምክር ቤት በኢትዮጵያና በካናዳ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ንግድና ኢንቨስትመንት መልካም ዕድል ለማሳደግ የሚያስችላቸውን የትብብር የመግባቢያ ሰነድ የካቲት 1 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሃያት ሬጀንሲ ተፈራረሙ፡፡

ስምምነቱ የሁለቱ ምክር ቤቶች አባል የንግዱ ማኅበረሰብ መረጃ እንዲለዋወጡና በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ እንዲመክሩ የጋራ መድረክ ለመፍጠር የሚያስችል ነው፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባል የንግዱ ማኅበረሰብ በካናዳ-አፍሪካ ቢዝነስ ምክር ቤት ውስጥ የአባልነት መብት እንዲያገኝና በካናዳ የንግድና ኢንቨስትመንት ገበያ ውስጥ ለመሳተፍ የሚያስችለውን መልካም ዕድል የሚፈጥርለት መሆኑም ታውቋል፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱ ክብርት ናሲሴ ጫሊ በካናዳ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር፣ የዕለቱ የክብር እንግዳ የተከበሩ ሜሪ ኢንግ በካናዳ የአነስተኛ ቢዝነስ ኤክስፖርት ማስፋፊያ እና ዓለም አቀፍ ንግድ ሚኒስትር፣ እንዲሁም ከ16 ኩባንያዎችና ማኅበራት የተወከሉ የካናዳ የንግድ ልዑካንና የኢትዮጵያ አቻዎቻቸው በተገኙበት በኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት መልአኩ እዘዘው (ኢንጂነር) እና በካናዳ-አፍሪካ ቢዝነስ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ጋሬት ብሉር መካከል ተከናውኗል፡፡

የካናዳ-አፍሪካ ቢዝነስ ምክር ቤት በንግዱ ማኅበረሰብ መካከል ትሥሥር በመፍጠርና የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር በማድረግ በካናዳና በአፍሪካ መካከል ያለውን ንግድና ኢንቨስትመንት ለማሳለጥ የሚሰራ ምክር ቤት እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ም/ቤቱ የኬንያ ብራንድ ኬኢ የወጪ ንግድ ማስፋፊያ እና ብራንዲንግ ኤጀንሲ ልዑካን ተቀብሎ አነጋገረ

ኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ የሱፍ አደም ኑር ከምክትላቸው አቶ ውቤ መንግሥቱ ጋር በመሆን ሦስት አባላትን የያዘውንና በኤጀንሲው የወጪ ንግድ ልማትና ማስፋፊያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኦስቲንግ ማቼሶ የተማራውን በምህፃረ ቃሉ ብራንድ ኬኢ የተባለውን የኬንያ የወጪ ንግድ ማስፋፊያ እና ብራንዲንግ ኤጀንሲ ልዑካን ቡድን ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በዋና ጸሀፊው ቢሮ ተቀብለው አነጋገሩ፡፡

የልዑካን ቡድኑ ጉብኝት ዋና ዓላማ በኬንያና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ይበልጥ ለማሳለጥ የሚያስችል አቅም በሀገራቱ የንግድ ማኅበረሰብ መካከል ለመፍጠር እንዲረዳ ፕሮግራም ለማዘጋጀት በማሰብ እንደሆነም አቶ ማቼሶ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኬንያ የወጪ ንግድ እያሽቆለቆለ በመምጣቱና በኬንያም የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ዕድገት ዘገምተኛ በመሆኑ ባለፉት ሦስት ዓመታት የሀገራቱ የንግድ ምጣኔ አነስተኛ መሆኑን የጠቆሙት የብራንድ ኬኢ ተወካይ እንደተናገሩት ፕሮግራሙ የንግድ ግንኙነቱን በማፋጠን የሥራ ዕድልን ለመፍጠርም ሆነ የሁለቱን ሀገራት ማህበራዊ ደህንነት ለማሻሻል የሚያስችል እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያና ኬንያ እ.ኤ.አ. በ2012 የሁለትዮሽ የንግድ ስምምነት መፈራረማቸውና ይህንኑ ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም በሰፊው ተወያይተዋል፡፡

በሞያሌ በኩል የሚገናኘው የናይሮቢ ሞያሌና የሞያሌ አዲስ አበባ የአስፋልት መንገድ መጠናቀቁን ያስታወሱት ተወያዮቹ መልካም አጋጣሚውን በመጠቀም በሀገራቱ መካከል ያለውን ንግድ ለማሰደግ ምክር ቤቱና ብራንድ ኬኢ በቅንጅት መሥራት ባለባቸው ጉዳዮች ላይም ተወያይተዋል፡፡

ኬንያ ከኢትዮጵያ የአበባ ምርቶችን፣ አትክልቶችን፣ በቆሎና የጥራጥሬ እህሎችን በጥሬው እንደምታስገባና ጥቂት የማኑፋክቸሪንግ ምርቶችንና የፍጆታ ዕቃዎችን ወደ ኢትዮጵያ እንደምትልክ ገልጸው የሁለቱ ተቋማት ትብብር የተቀነባበሩ ምርቶችን ለመላክ የሚያስችል ዕድልን እንደሚፈጥርም ተወያዮቹ አብራርተዋል፡፡

የተቋማቱን ትብብር ውጤታማ ለማድረግ የተለየ መድረክ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት የብራንድ ኬኢ ተወካይ ማቼሶ በመጪው ሚያዝያ ወር ዐውደ ርዕይ በአዲስ አበባ የማካሄድ ዕቅድ እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡ ዐውደ ርዕዩ ላይ ባዛር፣ የአቻ ለአቻ ውይይቶችና የቢዝስ መድረኮች ሊኖሩ እንደሚችሉም በውይይታቸው ላይ ተገልጿል፡፡

መድረኩ የሁለቱ ሀገራት የንግድ ማኅበረሰብ የቢዝነስ መረጃ እንዲለዋወጡና እግረ መንገዳቸውንም የገቢና ወጪ ንግድ ንግኙነት ውል ለመዋዋል ያስችላቸዋልም ተብሏል፡፡

መድረኩ ለሀገራቱ የግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሾች ዘላቂ አጋርነት የጎላ ሚና እንደሚኖረው ተገለጸ

የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት መልአኩ እዘዘው (ኢንጂነር) አሁን በሚታየው የሉላዊው የኢኮኖሚ አዝማሚያ በአጋርነትና በትብብር የመሥራቱ ጉዳይ አማራጭ ሳይሆን መሠረታዊ ግዴታ ነው አሉ፤ ምክር ቤቱ ከኳታር ልማት ባንክ ጋር ጥር 18 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሃያት ሬጀንሲ በአጋርነት ባዘጋጁት የቢዝነስ ለቢዝነስ የውይይት መድረክ ላይ የተናገሩት ነበር፡፡

የቢዝነስ ለቢዝነስ መድረኩ የሁለቱ ሀገራት ኩባንያዎች የጋራ ተጠቃሚነትን በሚፈጥሩ የንግድ አማራጮችና ዕድሎች ላይ ውይይት እንዲያደርጉ ያለመ ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2008 ዓ.ም. 22.3 የአሚሪካ ዶላር የነበረው የኢትዮጵያና የኳታር የንግድ መጠን በ2018 5.8 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ላይ መውረዱን ያስታወሱት ኢንጂነር መልአኩ የኳታር ኢነቨስተሮች በኢትዮጵያ መዋዕለንዋያቸውን የሚያፈሱበት ወቅት መሆን እንዳለበት ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

የተከበሩ አቶ ተካ ገብረየሱስ የፌዴራል ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ደዔታ በይፋዊ የመክፈቻ ንግግራቸው ይህ የኳታር የንግድ ልዑካን ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት የግሉን ዘርፍ ትብብርና ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችል መድረክ እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት እ.ኤ.አ. በ2030 የሀገሪቱን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌትነት ዕውን የሚያደርግ ሀገርበቀል አዲስ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረጉን የገለጹት ሚኒስትር ደዔታው ጊዜው የኳታርንና የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ትብብር ይበልጥ የምናጠናክርበት ወቅት መሆኑን አጽንኦት በመሥጠት ገልጸዋል፡፡

አቶ ሃማድ ሳሌም መጀጊር በኳታር ልማት ባንክ የወጪ ንግድ ልማትና ማስፋፋት ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ይበልጥ ማሳደግ እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል፡፡ የሀገራቱን የኢኮኖሚ ግንኙነት ለማጠናከር በመካከላቸው ያለውን ግብይትና የንግድ ልውውጥ ማሳደግ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን የኳታር ልማት ባንክ እንደሚያምንም ገልጸዋል፡፡

ኳታር ከኢትዮጵያና ከሱዳን ጋር በመተባበር በግብርና፣ ኮንስትራክሽን፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ሪል ኢስቴት እና ትራንስፖርት ኢንቨስትመን ላይ ተሰማርታ በመስራት ላይ እንደምትገኝም ተገልጿል፡፡

በመጨረሻም በፕላስቲክ፣ ኤሌክትሪክ፣ ቶቦዎች፣ የህክምና፣ ኮንስትራክሽን፣ የፕላስቲክ ከረጢቶች፣ ወረቀትና አሉሙኒየም ምርቶች ላይ የተሰማሩ የኳታር ኩባንያዎች ከኢትዮጵያውያን አቻዎቻቸው ጋር የቢዝነስ ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችላቸውን የአቻ ለአቻ ውይይት አድርገዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ከቱኒዚያ፣ ስሪ ላንካ፣ ቻይና፣ ፊሊፒንስ፣ አሜሪካ፣ ኮሪያ፣ ሳዑዲ አረቢያ ኩባንያዎች ጋር የተለያዩ የቢዝነስ ፎረሞች፣ ኤክስፖዎችና የአቻ ለአቻ የውይይት መድረኮች በመዲናችን መካሄዳቸው ይታወቃል፡፡

ኢኖቬቲቭ ግራንት ፈንድ ፕሮጀክት ላይ የውይይት መድረክ ተካሄደ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከኢኒሸቲቭ አፍርካ እና ከፓን አፍርካ የንግድና ኢንደስትሪ ምክር ቤት ጋር በመተባበር የግሉ ዘርፍ ከታች ወደ ላይ በሚደረግ የፖሊሲ ለውጥ ተሳታፊ እንዲሆን ማብቃት /Empowering Marginal Economic Actors through Policy Reform from the Bottom-up Project/ በሚል ኢኖቬቲቭ ግራንት ፈንድ ፕሮጀክት ላይ በሞሞና ሆቴል የውይይት መድረክ ጥር 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ተካሄደ፡፡

የውይይት መድረኩን የከፈቱት የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት መልአኩ እዘዘው(ኢንጅነር) እንደተናገሩት ምክር ቤቱ የጋራ ድምጽ መድረክ በመሆን የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚ ዉስጥ የመሪነት ሚናዉን እንዲጫወት ንግድና ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት፣ ዉጤታማ የአድቮኬሲና የአቅም ግንባታ ስራ በመስራት የሃገሪቱን ኢኮኖሚ የሚመራ የግል ዘርፍ እዉን እንዲሆን ለማድረግ ተልዕኮ አንግቦ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡

ምክር ቤቱ ከመንግሥት ጋር በመሆን የተለያዩ ሀገራዊ ፖሊሲዎች፣ መመሪያዎችና ደንቦች ከግሉ ዘርፍ ፍላጎት፣ መብትና ጥቅም ጋር የማይጋጩ መሆን አለመሆናቸውን በመገምገም፣ ጥናታዊ ዘገባዎችን በማዘጋጀትና የመፍትሄ ሃሳብ በማቅረብ ህጎች በሚቀየሩበት አለያም ሊሻሻሉ በሚችሉበት ሁኔታ ላይም የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሆነም ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ምክር ቤቱ ከፍተኛ የሆነ የፋይናንስ እና የሠው ሃይልን የሚጠይቁ በርካታ ተግባራት ሲፈፅም በነበረበት ወቅት ለረጅም ጊዜ አጋር የሆነው የስዊድን ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (SIDA) በቅርቡ የተጠናቀቀውን የPSD-Hub ፕሮጀክት ሲደግፍ የቆየ መሆኑን ጠቅሰው አሁን ደግሞ የግሉ ዘርፍ ከታች ወደ ላይ በሚደረግ የፖሊሲ ለውጥ ተሳታፊ እንዲሆን ማብቃት የሚል አዲስ ፕሮጀክት ይዞ መምጣቱን የተናገሩት ፕሬዚደንቱ የእለቱ አውደ ጥናት በፕሮጀክቱ ዙሪያ በስፋትና በጥልቀት በመወያየት ጠቃሚ ግብዓት ለመስጠት ነው ብለዋል፡፡

የፓን አፍርካ የንግድና ኢንደስትሪ ምክር ዋና ዳይሬክተር አቶ ክቡር ገና እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ ለአነስተኛ የግል ኢኮኖሚ አንቀሳቀሾች፣ በመንግስትና በግሉ ዘርፍ መካከል ለሚደረጉ የፖሊሲ ጉዳይ ውይይቶች እና ለግል ዘርፉ የንግድ ምክር ቤቶችና ማህበራት የአቅም ማጎልበቻ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ የሶስት አመት ቆይታ ቢኖረውም በዘላቂነት የግል ዘርፉ ደጋፊ እንዲሆን ለማድረግ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባም አቶ ክቡር አክለው ተናግረዋል፡፡

የኢኒሸቲቭ አፍርካ ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ የኋላሸት ገ/ሚካኤል በበኩላቸው ተቋማቸው ከተመሰረተ ጊዜ አንስቶ ከለጋሾች የሚሰበሰበውን የገንዘብ ድጋፍ አመርቂና ውጤታማ በሆነ መንገድ በማስተዳደር 150 ከሚሆኑ የድጋፍ ተጠቃሚዎች ጋር ሲሰራ በመቆየቱ ጥሩ ልምድ ያከበተ መሆኑን በመግለጽ የድጋፍ ገንዘቡን ለተጠቃሚዎች ከማስተላለፉ ባሻገር ድጋፉ ያገኘውን ማህበር አቅም በማጎልበት ውጤታማነቱን እንዲያሳድግ እገዛ የማድረግ ስራም እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የግሉ ዘርፍ ከታች ወደ ላይ በሚደረግ የፖሊሲ ለውጥ ተሳታፊ እንዲሆን ማብቃት፣ የኢኖቬቲቭ ግራንት ፈንድ ፕሮጀክትን ቀጣይ ስለማድረግ፣ የስራ ፈጠራ እድሎችን ለማሳደግ ቢዝነስን ማንቀሳቀስ፣ ለኢኖቬቲቭ ግራንት ፈንድ የሚሆኑ የምክረ-ሀሳቦች/እቅዶች አይነቶች እና የፕሮጀክቱ ቀጣይ እርምጃዎች በሚሉ ርዕሶች ላይ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

የኢኖቬቲቭ ግራንት ፈንድ ፕሮጀክት ለንግዱ ማህበረሰብ ማህበራትና ዘርፎች መነሻ የገንዘብ ድጋፍን የማመቻቸት፣ የአነስተኛና ጥቃቅን ድርጅቶችን የማሳለጥ፣ የኢንዱስትሪ፣ የምሁራናና የሌሎች ባለድረሻ አካላትን የትብብር መድረክ ማመቻቸት እና የግሉ ዘርፍ የአቅም ግንባታ ጉዳዮችና ለኢኮኖሚ እድገት አስተዋፅኦ የሚያደርጉ የመፍትሄ ሀሳቦችን ለማመንጨት የሚረዳ የግንኙነት መረብ እንዲኖር የማመቻቸት ተግባራትን እንደሚያከናውን በገለፃው ላይ ተብራርቷል፡፡

ይህ ኢኖቬቲቭ ግራንት ፈንድ ፕሮጀክት ከስዊድን ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ /SIDA/ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት እየተረዳ ኢኒሸቲቭ አፍርካ ፣ ሴንተር ፎር ኢንተርናሽናል ፕራይቬት ኢንተርፕራይዝስ /CIPE/ እና ፓን አፍርካን የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት /PACCI/ የተሰኙ ተቋማቶች በጋር የሚተገብሩት ለ3 አመታት የሚቆይ እቅድ እንደሆነ ታውቋል፡፡

ምክር ቤቱ ከቲኤምኢኤ ጋር የንግድ ሥራ አመቺነትን ለማቀላጠፍ በሚያስችለው የትብብር ማዕቀፍ ላይ ተወያየ

የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ የሱፍ አደምኑር ትሬድማርክ ኢስት አፍሪካ የተባለን ድርጅት ወክለው የመጡ አራት አባላትን የያዘውንና በሚካኤል ሚቴይ የድርጅቱ አይሲቲ ለንግድና ትራንስፖርት ፋሲሊቴሽን ዳይሬክተር የተመራውን ልዑካን ቡድን ጥር 7 ቀን 2012 ዓ.ም. በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡

የጉብኝቱ ዓላማ ከምክር ቤቱ ጋር የንግዱን ማኅበረሰብ የንግድ ሥራ አመቺነትን (trade facilitation) አሠራር መዘርጋት የሚያስችል የድጋፍ ትብብር ለማድረግ ነው፡፡ ድርጅቱ በተለይ ለምሥራቅ አፍሪካ የግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሾች የአይሲቲ ሥርዓትና ሥርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዳውን መሠረተ ልማት በመዘርጋት፣ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በመሥጠትና አገልግሎቶችን ቀላል፤ ተገማች፤ ቀልጣፋና ፈጣን የሚያደርጉ አሠራሮችን የተመለከቱ ድጋፎችን በማድረግ በዓለም አቀፉ የንግድ ምህዳር ውስጥ የመጠቀም ዕድላቸውን ለማሳደግ በእጅጉ እየሠራ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ የሱፍ አደምኑር ሀሳቡ እንዳስደሰታቸው ገልጸው በዚህ ረገድ ምክር ቤቱ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ጠቁመዋል፡፡ እንደ ዋና ጸሐፊው ገለጻ የምክር ቤቱን አገልግሎት ቀልጣፋ ለማድረግ ይረዳ ዘንድ የምክር ቤቱን የኤሌክትሮኒክ አንድ መስኮት እና የአምራች ሀገር የምስክር ወረቀት (certificate of origin) አሠራርን ማዘመን፣ የመረጃ አሰጣጥና የሥልጠና አገልግሎትን ማመቻቸትና የድረ-ገጽ ማበልጸግን የመሳሰሉ አገልግሎቶች ትብብር ማድረግ ከሚፈልጉባቸው ነጥቦች ዋነኞቹ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

የግሉ ዘርፍ ተወካይ እንደመሆኑ ምክር ቤቱ ዋነኛው የቢዝነስ መረጃ ምንጭ መሆን ይፈልጋል የሚሉት የሱፍ በንግግራቸው ለንግዱ ማኅበረሰብ ፈጣንና ቀልጣፋ የገበያ መረጃና ሌሎች ተዛማጅ አገልግሎቶችን ለመስጠት የምክር ቤቱን የኤሌክትሮኒክ አንድ መስኮት አገልግሎት የማዘመን አስፈላጊነትን አስምረውበታል፡፡ ለምክር ቤቱ ሠራተኞችና አባል ምክር ቤቶችም ስልጠናዎችን ማመቻቸትን በተመለከተ የቲኤምኢኤ የድጋፍ ትብብር ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም የትብብር ማዕቀፍ መንደፉ አስፈላጊ በመሆኑ የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ወደ ሥራ መግባት እንደሚቻልም መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡

ተቀማጭነቱን ኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ያደረገው ቲኤምኢኤ በየንግድ ሥራ አመቺነት በዓለም ግንባር ቀደም ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ስኬታማ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑም ታውቋል፡፡

መዲናችን የመጀመሪያውን የጎዳና ላይ ትርዒት ልታስተናግድ ነው

‹‹ዋን አፍሪካ ካርኒቫል›› በሚል መሪ ቃል በአፍሪካ የመጀመሪያውን የጎዳና ላይ ትርዒት (ካርኒቫል ፌስቲቫል) በአዲስ አበባ ለማካሄድ ዕቅድ እንዳለ የአይ. ጂ. ኢንተርቴይንመንት ባለቤትና የዝግጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ይስሀቅ ጌቱ ገለጹ፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ ይህን የተናገሩት ጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት መልአኩ እዘዘው (ኢንጂነር) ጋር በፕሬዚደንቱ ጽ/ቤት በዝግጅቱ ዙሪያ በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡

በዕለቱ ከኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ከቱሪዝም ኢትዮጵያና ከግል ድርጅቶች የተውጣጡ ሰባት አባላትን የያዘ ልዑካን ቡድን ከፕሬዚደንቱ ጋር በዝግጅቱ ዓላማና ከምክር ቤቱ ጋር በጋራ በሚሰሩ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርጓል፡፡ የዝግጅቱ ዓላማ የአፍሪካን ባህል፣ ታሪክ፣ ንግድና ኢንቨስትመንት ትሥሥር በማበረታታት በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ለማስተዋወቅ እንደሆነ የዝግጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ይስሀቅ ገልጸዋል፡፡

ቀደም ሲል አፍሪካን የሚመጥን የጋራ መድረክ ኖሮ አያውቅም የሚሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ 15 ቀናት ያህል እንደሚቆይ በሚጠበቀው ዝግጅት የመጀመሪያ ቀን የጎዳና ላይ ትርዒት እንደሚካሄድና በቀሩት ቀናት 54ቱም የአፍሪካ ሀገሮች ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበትና የሚሸጡበት ኤግዚቢሽንና ባዛር እንዲሁም አፍሪካዊ ባህሎችና ታሪኮች የሚተዋወቁበት ዝግጅት በግዮን ሆቴል ለህዝብ እንደሚታይ አብራርተዋል፡፡

ሀገራችን ዘርፈ ብዙ የሆኑ እምቅ ሀብቶቿን ወደ ገንዘብ ያልቀየረች ሀገር መሆኗን በአጽንዖት የተናገሩት የምክር ቤቱ ፕሬዚደንት ኢንጂነር መልአኩ እንደተናገሩት እንደ ቡናና ሰሊጥ ያሉ ጥሬ ምርቶችን በቅናሽ ዋጋ ወደ ውጭ እየላክን በምትኩ የኛኑ ምርት እሴት ተጨምሮበት ከእጥፍ በላይ በሆነ ዋጋ መልሰን እንሸምታለን ካሉ በኋላ እንዲህ ዓይነቱ ዝግጅት ሀብታችንን በአግባቡ ለመጠቀም ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

ዝግጅቱ ለሀገራችን ብሎም ለአህጉራችን አዲስ የቢዝነስ እይታ እንደመሆኑ በጋራ መሥራቱ ጅማሮው እንዲያምር ስለሚያደርግ ምክር ቤቱ በዚህ ረገድ የድርሻውን እንደሚወጣም ተናግረዋል፡፡ በቆይታው በየዕለቱ ከ10 ሺ በላይ ጎብኚዎች እንደሚገኙ የሚገመት ሲሆን ዝግጅቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል ተብሎለታል፡፡ የፊታችን የካቲት 21 ቀን 2012 ይጀመራል ተብሎም ቀጠሮ ተይዞለታል፡፡

አይ. ጂ. ኢንተርቴይንመንት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከአ/አ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ከቱሪዝም ኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር በመተባበር እንደሚያዘጋጀውም ታውቋል፡፡

የኤሌክትሮኒክስ አንድ መስኮት አገልግሎት አሠራሮችን ያቀላጥፋል ተባለ


የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን ጨምሮ 16 መስሪያ ቤቶች የኢትዮጵያ ኤሌክትሮኒክስ አንድ መስኮት አገልግሎትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን፤ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በተገኙበት ታህሳስ 25/2012 ዓ.ም ስራውን በይፋ አስጀምረዋል፡፡ አገልግሎቱ በአገሪቱ በተለያዩ መስሪያ ቤቶች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ቀላል፤ ተገማች፤ ቀልጣፋና ፈጣን ያደርገዋልም ተብሏል፡፡

አሰራሮችን ወረቀት አልባ በማድረግ አለም አቀፍ የንግድ ስርዓትና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጠዉ ይህ ስርዓት አገራዊ ገቢን በማሳደግ፤ወጪን የሚቆጥብና የአገልግሎት አሰጣጥ ግዜን የሚቀንስ ከመሆኑም በላይ አሰራሩ ሙስናን በመቀነስ የደንበኞች እርካታን ይጨምራል፤ አለም አቀፍ ንግድን በማበረታታት ግልፅነትን ያሰፍናል፤ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን ጨምሮ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የንግድና ኢንዱስቴር ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር፣የትራንስፖርት ሚኒስቴር፣የመዓድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣የኢትዮጵ ብሄራዊ ባንክ፤ የጉምሩክ ኮሚሽን፤የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፤ የኢትዮጵያ መረጃና መረብ ደህንነት ኤጄንሲ ጨምሮ በአጠቃላይ በመጀመሪያዉ ዙር 16 የግልና የመንግስት ተቋማት ስራውን ለማስጀመር የሚስችል ስምምነትተፈራርመው ወደስራ ገብተዋል፡፡

ምክር ቤቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አዘጋጀ


የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ዘርፍ ያሉ የኢንቨስትመንት አቅሞች፣ ዕድሎች እና ተግዳሮቶችን አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ታህሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. በኢሊሌ ሆቴል አካሄደ፡፡

ምክር ቤቱ ከሚሰራቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል አንዱ የንግድና ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት ስራ መሆኑን በመጥቀስ የኢንቨስትመንት ማስፋፋፊያ ስራውን ለመስራት ያሉትን ምቹ ሁኔታ፣ አማራጮች እና ድጋፎች የአገር ውስጥ ባለሀብቱን ግንዛቤ ማሳደግ ነው፡፡

ከዚህ በፊት በአዋሳና በኮምቦልቻ ተመሳሳይ የግንዛቤ መፍጠሪያ ስልጠናዎች በምክር ቤቱ መሰጠቱን ያስታወሱት የምክር ቤቱ ም/ዋና ፀሀፊ አቶ ውቤ መንግስቱ መድረኩ በጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ዘርፍ ያሉትን የኢንቨስትመንት አማረጮች እና ተግዳሮቶች በማሳወቅ እና ለእነዚህም ችግሮች መፍትሄ በሚሰጡባቸው መንገዶች ላይ በመወያየት ተሳታፊዎች ለራሳቸው ተጠቅመው ለሌሎችም እነዲጠቀበት የማድረግ ስራ ለመስራት እንዲቻል ነው ብለዋል፡፡በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ በኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ዘርፍ ያሉ የኢንቨስትመንት አቅሞች፣ ዕድሎች እና ተግዳሮቶች እንዲሁም በቅርቡ በኢትዮጵያ የሚካሄደውንእና በጨርቃጨርቅ ማሽነሪዎች እና ተያያዥ ሁነቶች ላይ የሚያተኩረውን የ ITME Africa 2020 ኤክስፖን አስመልክቶ ገለፃዎች የተደረጉ ሲሆን፤ ይህን ተከትሎ በተሳታፊዎች በተነሱ በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ ውይይት ተካሂዷል ፡፡


ምክር ቤቱ ከፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈራረመ

የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና የኢፌዲሪ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በትብብር ለመስራት ታህሳስ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. በምክር ቤቱ አዳርሽ የጋራ ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ ለማከናወን የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡ ስምምነቱ የተፈረመው በምክር ቤቱ ዋና ፀሀፊ አቶ የሱፍ አደምኑር እና በኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ አለበል ደሴ ነበር፡፡

የመግባቢያ ሰነዱ ስምምነት ዋና ዓላማ ሁለቱ ተቋማት የንግዱ ማህበረሰብ የሚያጋጥሙትን ፈታኝ ችግሮች በመለየት እና በጥናትና ምርምር በማስደገፍ ለፖሊሲ አውጪ የመንግስት አካላት የመፍትሄ ሀሳብ ለማቅረብ በሚያስችል ሁኔታ በትብብር ለመስራት ነው፡፡

በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ አቶ የሱፍ አደምኑር እንደተናገሩት ምክር ቤቱ ከሚሰራቸው ንግድና ኢንቨስትመንት የማስፋፋት፣ የአቅም ግንባታና ስልጠና የመሳሰሉት አበይት ተግባራት መካከል የንግዱን ማህረሰብ መብትና ጥቅም ከማስከበር እና ምቹ የንግድ ከባቢ ለመፍጠር ከመስራት አንፃር የንግድና ኢንቨስትመንትን የሚመለከቱ ፖሊሲዎች፣ ህጎች፣ ደንቦችና የአሰራር ስርዓቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በጥናት በመለየት አማራጭ የመፍትሄ ሀሳቦች የሚያቀርቡበት እስከ ጠቅላይ ሚንስትሩ የሚደርስ የውይይት መድረክ ከመንግስት ጋር ያዘጋጃል፡፡ ምክር ቤቱ ለመንግስት የሚሆኑ ግብዓቶችን ከማዘጋጀት አንፃር በሚያካሂደቸው ጥናቶች፣ ከኢንስቲትዩቱ ጋር በመተባበር የሚሰራበትን መንገድ ለማመቻቸት ስምምነቱ ያስችለዋል፡፡

ምክር ቤቱ ለንግዱ ማህበረሰብ የሚሰጣቸውን ስልጠናዎች እና የንግድና ኢንቨስትመንት፣ የገበያና አጠቃላይ ጠቃሚ መረጃዎችን በተጠናከረ መልኩ ለመስራት ብሎም የዳታ አሰባሰብና አተናተን አሰራር ስርዓትን ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ለማድረስ ኢንስቲትዩቱ ካለው ልምድ አኳያ አብሮ መስራቱ አስፈላጊ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ከመንግስት ጋር በሚያደርገው ውይይት ከፖሊሲ ጥናቶች ጋር ተያይዞ ይህን ከመሰለ የመንግስት ኢንስቲትዩት ጋር አብሮ መስራቱ ተአማኝነቱን ስለሚጨምር በተደረገው ስምምነት ደስተኛ እንደሆኑ የተናገሩት አቶ የሱፍ ምክር ቤቱ ከተቋሙ ጋር በጋራ የተሻለ ስራ እንደሚሰራ ተስፋቸውን ገልፀዋል፡፡

አቶ አለበል ደሴ በበኩላቸው ተቋማቸው በነፃ ኢኮኖሚው ውስጥ ስለማክሮ ኢኮኖሚና ስለ አገር እድገት ተከታታይ የሆኑ በተለይ ለፖሊሲ ጠቃሚ የሆኑ ሳይንሳዊ ጥናቶችና ምርምሮችን በማካሄድና መንግስትን በማማከር የሚሰራ መሆኑን በመጥቀስ የግል ዘርፉንም አስመልክቶ ከዚህ በፊት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ፣ የፋይናንስ፣ ከኢንቨስትመንት ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶች ላይ ጥናቶችን በማካሄድ የፖሊሲ የመፍትሄ ሀሳቦችን ለመንግስት ያቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ምክር ቤቱ በቀጣይ የግሉን ዘርፍ ችግሮች በጥናት አስደግፎ የፖሊሲ ሀሳብ በማቅረብ ረገድ በጋራ ለመስራት ፍላጎቱን ማሳየቱ ለተቋሙ እንደ መልካም አጋጣሚ ይቆጠራል በማለት ስምምነቱ እንዳስደሰታቸውም ገልፀዋል፡፡ አቶ አለበል ጨምረው በስምምነቱ መሰረት በጋራ እቅድ በማዘጋጀት ወደ ተግባር መግባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱን ተግባራዊ ከማድረግ ረገድ የጥናትና ምርምር፣የምክር አገልግሎት፣ የአጭርና መካካለኛ ስልጠናዎች፣የግንዛቤ ማስጨበጫ አገልግሎት፣ የልምድ ልውውጥ ስራዎች በጋራ ከሚሰሩ ዋና ዋና ተግባራት መካከል እንደሚገኙባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

ምክር ቤቱ በኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ላይ ከንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ተወያየ

የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አዲስ በወጣው የኢክሳይዝ ታክስ አዋጅ ቁጥር ........./2012 ዙሪያ ከተለያዩ ኩባንያዎች ከተውጣጡ የንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ታህሣሥ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. በምክር ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት አደረገ፡፡

ውይይቱን የመሩት የምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ አቶ የሱፍ አደምኑር ከም/ዋና ፀሀፊው አቶ ውቤ መንግስቱ ጋር በመሆን እንደተናገሩት የውይይቱ መሠረታዊ ዓላማ በአዋጁ ላይ የንግዱን ማኅበረሰብ አስተያየት በማድመጥ የአቋም መግለጫውን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉዳዩ ለሚመለከተው የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለማቅረብ ነው፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች ከጨርቃ ጨርቅ አምራቾች ማህበር፣ ከታሸገ ውሃ እና ለስላሳ መጠጦች አምራቾች ኢንዱስትሪ ማህበር፣ ከበላይነህ ክንዴ ኦቶሞቲቭና በላይ አብ ሞተርስ፣ ከሆራይዘን ጎማ እንዲሁም ከጄቲአይ የትንባሆ ሞኖፖል እና ሌሎችም ኩባንያዎች የተውጣጡ ሲሆን አዋጁ በንግዱ እንቅስቃሴ ላይ በሚያሳደረው አሉታዊና አዎንታዊ ተፅዕኖዎች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት አድርገዋል፡፡

በተለይ፣ በአዋጁ መግቢያ ላይ እንደተቀመጠው ቀደም ሲል በነበረው አዋጅ ላይ ከተዘረዘሩት መሠረታዊ ነጥቦች አንዱ በተመረጡ ዕቃዎች ላይ የማምረቻ ወጪ የኤክሳይዝ ታክስ መጣል ሲሆን በአዲሱ አዋጅ ላይ በማምረቻ ወጪ ላይ ሲሰላ የነበረው የኤክሳይዝ ታክስ በፋብሪካ የመሸጫ ዋጋ እንዲተካ መደረጉ በገቢያቸውም ሆነ ባጠቃላይ እንቅስቃሴያቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል ብለዋል፡፡

እንደ ተወያዮቹ አስተያየት ከሆነ በአዲሱ አዋጅ የተቀመጠው የኤክሳይዝ ታክስ በመቶኛ ሲሰላ ከበፊቱ ያነሰ ቢሆንም በፋብሪካ የመሸጫ ዋጋ ላይ የተጣለ በመሆኑ የታክስ መጠኑን በእጅጉ ከፍ ያደርገዋል፡፡

የኤክሳይዝ ታክስ መጣል የሚገባው በቅንጦት ዕቃዎችና ለጤና ጎጂ በሆኑ ዕቃዎች ላይ ሆኖ ሳለ ከምግብነት በሚመደቡ የታሸጉ ውሃዎች ላይ መጣሉም አግባብ አለመሆኑ በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡

አዲሱ አዋጅ በተለይ በሀገር ውስጥ በሚያመርቱ አምራቾች ላይ የተጣለው ተጨማሪ የታክስ መጠን የሀገር ውስጥ አምራቾችን ከማበረታታት ይልቅ ገቢ ምርት ላይ እንዲሰማሩ እንደሚያደርግም ተወያዮቹ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

በአንዳንድ ምርቶች ላይ የተጣለው ከፍተኛ ታክስ ደግሞ ለኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት በር ስለሚከፍት ከታክስ ለመሰብሰብ የታቀደውን ዓላማ ላያሳካ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸውም ተወያዮች በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ዋና ፀሐፊው የተወካዮቹን የአቋም መግለጫ የተጠቃለለ ሰነድ ለሚመለከተው አካል እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል፡፡

 

ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸዉን ለማሳደግ ተስማሙ

የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ዓይናለም አባይነህ (ዶ/ር) የኢትዮጵያና የደቡብ ኮሪያ ሪፐብሊክ የንግዱ ማኅበረሰብ አንቀሳቃሾች የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነታቸውን ቀጣይነት ያለው ውጤት ሊያመጣ በሚችል ደረጃ ለማሳደግ በላቀ ደረጃ ሊሰሩ እንደሚገባ አሳሰቡ፡፡

ዶ/ር ዓይናለም ይህን የተናገሩት ህዳር 19 ቀን 2012 ዓ.ም. የፌዴራል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከምክር ቤቱና የደቡብ ኮሪያ ቢዝነስ ኩባንያ ከሆነው ቡሳን-ኡልሳን ኢኖቢዝ ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባዘጋጀው የኢትዮጵያ-ኮሪያ ቢዝነስ ፎረም ላይ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ነው፡፡ የቦርድ አባሉን ንግግር ተከትሎ የፌዴራል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ ዶ/ር አክሊሉ ኃ/ሚካኤል፣ በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር የተከበሩ ሊም ሁን ሚ እና በኢትዮጵያ የቡሳን ከተማ የክብር ቆንስላ ጄኔራል ኪም ሳንግ ጂን የመክፈቻ ንግግር አድረገዋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት የግሉ ዘርፍ ተወካዮችም ወደተሻለ የንግድ ትሥሥር ሊያደርሳቸው በሚችሉ ጉዳዮች ላይ የአቻ ለአቻ ውይይት አድርገዋል፡፡

ዶር ዓይናለም በንግግራቸው የሀገር ውስጥ የግል አንቀሳቃሾችን እያደገ ካለው የኮሪያ ንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ጋር ይበልጥ የሚያስተዋውቃቸው በመሆኑ መድረኩ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን አጽንዖት በመስጠት ገልጸዋል፡፡ መድረኩ በንግድ ማኅበረሰቡ መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር መልካም አጋጣሚ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ዶር ዓይናለም አያያዘውም የሁለቱን ሀገራት የንግዱን ማኅበረሰብ የማስተሳሰሩ ጉዳይ የምክር ቤቱና የኢኖቢዝ ኩባንያ ጥቅል የቤት ሥራ ሊሆን እንደሚገባም እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታው ዶ/ር አክሊሉ ኃ/ሚካኤል ባደረጉት ይፋዊ የመክፈቻ ንግግር ኢትዮጵያ ከሠሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት 2ኛዋ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንደመሆኗ ለኮሪያ ኩባንያዎች ክፍት ናት ሲሉ በሀገሪቱ ያለውን የኢንቨስትመንት መልካም ዕድል አስረድተዋል፡፡

ሀገራቸው ሰፊ የሀገር ውስጥና የውጭ ገበያ፣ እጅግ ከፍተኛና በተመጣጣኝ ከፍያ የሚሰራ አምራች ኃይል ያላት እንደመሆኗ የኮሪያ ኩባንያዎች ይህን መልካም አጋጣሚ መጠቀም እንደሚችሉ አብራርተዋል፡፡ የሁለቱ ሀገሮች የግሉ ዘርፍ አጋርነትም በመንግሥታቸው አጽንዖት ይሰጠዋል ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ሁን ኢትዮጵያና ኮሪያ ልዩና ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው በኮሪያ ጦርነት ወቅት የተሰዉትን ኢትዮጵያውያን በማስታወስ የገለጹ ሲሆን ሀገራቱ ይህን የረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፉም ይበልጥ ለማጠናከር እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የኮሪያ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር የጋራ ጥቅማቸውን በሚያስጠብቅ መልኩ መሥራት እንደሚፈልጉም እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያንና የደቡብ ኮሪያን የንግድ ግንኙት አስመልክቶ በተደረገው ማብራሪያ ኢትዮጵያ እንደ ቡና፣ የቅባት እህሎች ቆዳ ወደ ኮሪያ ስትልክ እንደ መድኃኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የኤሌክትሪክ ዕቃዎችና ጎማ እንደምታስገባ ተገልጿል፡፡ ደቡብ ኮሪያ የእስያ ገበያ መተላለፊያ ላይ ያለች እንደመሆኗ እንደ ቡና፣ ሰሊጥ፣ አበባ፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳና የቁም ከብት የመሳሰሉትን ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን የኢትዮጵያ ምርቶች በከፍተኛ ቁጥር ወደ ኮርያ ለማስገባት እየሰሩ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ .ኤ.አ. የ2018 መግለጫ እንደሚያመለክተው የሁለቱ ሀገራት ያለፉት አሥርት ዓመታት የንግድ ልውውጥ መጠን 1.8 የአሜሪካ ዶላር ሲሆን ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ መጠን 226 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የገቢ ንግዷ ደግሞ 1.6 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር መሆኑም ታውቋል፡፡

በመድረኩ ላይ 100 ያህል የኢትዮጵያ ኩባንያዎች በማዳበሪያ ምርት፣ ሰሊጥና ቡና ማቀነባበሪያ፣ አውቶሞቢል፣ ኬሚካል ምርት፣ ኮንስትራክሽንና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች፣ ሪል ኢስቴትና የኢንዱስትሪ መንደር ማልማት ላይ ከተሰማሩ ከ12 በላይ የኮሪያ ባለሀብቶች ጋር በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ ሊያደርሳቸው የሚያስችል ውይይት አድርገዋል፡፡

ሁለቱ ሀገሮች በቅርቡ ከሁለት ሳምንታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ተመሳሳይ ቢዝነስ ፎረም ማካሄዳቸውም ይታወቃል፡፡

አመታዊ የዘርፈ ብዙ ባለድረሻ አካላት የጋራ ውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው


የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያዘጋጀው አመታዊ የውሃ አቅርቦት፣ ሳኒቴሽንና ሀይጅን እና የውሃ ሀብት አስተዳደር የዘርፈ ብዙ ባለድረሻ አካላት የጋራ ውይይት መድረክ ከህዳር 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በሂልተን ሆቴል እየተካሄደ ነው፡፡

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኢነጂ. ስለሺ በቀለ በእንኳን ደህና መጣችሁና በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት የዘርፈ ብዙ ባለድረሻ አካላት የጋራ ውይይት መድረክ እ.ኤ.አ. ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በውሃ ዘርፍ ላይ የሚሰሩ አካላት በየአመቱ ውይይት የሚያካሂዱበት መድረክ ሲሆን ዘንድሮ አስረኛ አመቱን እና የውሃ ሀብት አስተዳደርን በማካተት ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ሚኒስትሩ አክለው የዘንድሮው አመታዊ የውይይት ጉባኤ በዋናነት በውሃ ዘርፍ ላይ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ያሉበትን ሁኔታ እና ፈታኝ ሁኔታዎች እንዲሁም የወደፊት ስትራቴጂካዊ እቅዶች በመንደፍ የሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እና ዘላቂ የልማት ግቦችን እውን ለማድረግ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች በመለየት