በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና (TVET) ሥትራቴጂ ዙሪያ ውይይት ተካሄደ።



በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና (TVET) ሥትራቴጂ ዙሪያ ውይይት ተካሄደ።
በአዲስ አበባ ግረንድ ፓላስ ሆቴል የተካሄደው ውይይት የተዘጋጀው በኢፌዴሪ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እንዲሁም በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት እና GIZ-STEP 4 ድጋፍ ነው።
በውይይቱም የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ተሻለ በሬቻ፣ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ አቶ ጸደቀ ድጋፌን ጨምሮ ከጂአይዜድ STEP-4 ፣ ከግሉ ዘርፍ ባለድርሻ አካላትና ትላልቅ ኩባንያዎች የተውጣጡ ተወካዮች ተሣትፈዋል።
በኢትዮጵያ ያለው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ውጤትን መሠረት ያደረገ፣ ከኢንዱስትሪው ጋር የተጣጣመ፣ ፍላጎትን መሠረት ያደረገና ውጤት ተኮር መሆን እንዳለበት ነው በውይይቱ የተነሣው።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ተሻለ በሬቻ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘመኑ የሚፈልገውን እውቀት እና ክህሎት የያዙ ሠልጣኞችን ለማፍራትና ለኢንዱስትሪው ውጤታማነት አጋዥ የሚሆን ኃይል ለማፍራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ አቶ ጸደቀ ድጋፌ በበኩላቸው ፍላጎትን መሠረት ያደረገ፣ የመጭውን የቴክኒና ሙያ ሁኔታ ያገናዘበ፣ የግሉን ዘርፍ አሣታፊ ያደረገ እና ጥራትን መሠረት ያደረገ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሠው ምክር ቤቱም ዘርፉን የሚደግፍ ክፍል በማቋቋም ለመሥራት ጥረት እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።



የግሉ ዘርፍም ከሥርዓተ ትምህርት (Curriculum) ቀረጻ ጅምሮ በኢንዱስትሪ ትሥሥር፣ በሌሎችም አግባቦች የነቃ ተሣትፎ ማድረግ እንዳለበት ነው የተገለጸው።
ከሥልጠና ውጤታማነት ጋር በተያያዘ በተለይም በድህረ- ሥልጠና ሂደት ሠልጣኞች ያሉበትን ሁኔታ መዳሰስ አስፈላጊ ሲሆን ይህንን መነሻ በማድረግ በየጊዜው ውጤታማ ሥራ ለማከናወን ያግዛል ተብሏል።
በአዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ መሠረት እየተዘጋጀ ያለው ሥትራቴጂ በተለይም ለTVET አስተዳደር ውጤታማነት የግሉ ዘርፍ ተሣትፎ ወሣኝነት ተነሥቷል።
በገበያው ተፈላጊ እውቀት እና ክህሎት ያለው ባለሙያ ለማፍራት ከ10 ዓመት የልማት እቅድ፣ ከሀገር በቀል ኢኮኖሚ ልማት እንዲሁም ከዲጂታላይዜሽንና ኢኖቬሽን፣ በተቋማት እና ኢንዱስትሪ ትሥሥር፣ በጥራት እና በሠርቲፊኬሽን አሠራር የተቃኘ ሥትራቴጂ ሊኖር እንደሚገባም ተገልጿል።


