አምራቾች የብሔራዊ የደረጃ ምልክት መጠቀም እንደሚገባቸው ተገለፀ::

አምራቾች የብሔራዊ የደረጃ ምልክት መጠቀም እንደሚገባቸው ተገለፀ፤
የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት የስኪምና የደረጃ ምልክት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ኦሊያድ ሌንጮ እንደገለፁት በምግብና ምግብ ውጤቶች፣ በኬሚካል ኬሚካል ውጤቶች፣ በኮንስትራክሽንና ሲቪል ኢንጂነሪንግ፣ በኤሌክትሪክ ምርትና ውጤቶች እንዲሁም መሰል ዘርፎች ላይ 3መቶ 47 አምራቾች የብሔራዊ የደረጃ ምልክት ፍቃድ ተሰጥቷቸው በምርቶቻቸው ላይ እየተጠቀሙ ይገኛሉ ብለዋል።
የህፃናት መቀንጨርን ለመከላከልና ነፍሰጡር እናቶች አስፈላጊ የተመጣጠነ ስነ-ምግብ ብሎም የህብረተሰቡን ጤና ለማጎልበት ምግብና የምግብ ውጤቶች አስፈላጊውን ጠቃሚ የምግብ ንጥረ ነገር የያዙ ምርቶች መመረታቸውን ለማረጋገጥ አምራቾች በምርቶቻቸው ላይ ብሔራዊ የበለፀገ ምግብ ምልክት መጠቀም ግድ እንደሚላቸው አስገንዝበው በተለይም የስንዴ ዱቄት፣ የምግብ ጨው እና የምግብ ዘይት ምርቶች ይህንን ሳያሟሉ ወደ ገብያ መቅረብ እንደማይችሉ ገልጸዋል።
የሸማቹን ጤናና ደህንነት ለመጠበቅና በከፈለው ልክ ተገቢ ምርት እንዲጠቀም ለማስቻል፣ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶችን በቀላሉ ለመለየት የሚያስችል ስርዓት በመተግበር ፍትሀዊ የንግድ ምህዳር ለማስፈንና ከሀገር አልፎ በአህጉርና በአለም አቀፍ ተወዳዳሪ ብሎም ተመራጭ አምራቾችን ለማፍራት የብሔራዊ ደረጃ መጠቀም ለድርድር የሚቀርብ እዳልሆነ መሪ ሥራ አስፃሚው አብራርተዋል።
በሀገራችን በርካታ አምራቾች እንደሚገኙ የገለፁት መሪ ስራ አስፈፃሚው ሁሉም አምራቾች አስገዳጅ ደረጃ ለወጣላቸው ምርቶቻቸው የብሔራዊ ደረጃ ምልክት መጠቀም ተገቢ እንደሆነ አስታዉሰው ኢንስቲትዩቱም የደረጃ ምልክት አጠቃቀም ላይ ባደረገው ቅኝት አንዳንድ አምራቾች ከኢንስቲትዩቱ ፍቃድ ውጪ ምልክት እየተጠቀሙ እንደሚገኙ ገልጸው ይህ ፍጹም ተቀባይነት የሌለወና በህግ የሚያስጠይቅ መሆኑን አሳዉቀዋል።
አስገዳጅ ደረጃ የወጣላቸው ምርቶች ወደ ገበያ ከመውጣታቸው በፊት ብሔራዊ የደረጃ ምልክት መለጠፍ እንደሚገባቸው በአዋጅ ቁጥር 1343/2016 አንቀፅ 25(3) የተደነገገ ሲሆን ከኢንስቲትዩቱ ፍቃድ ውጪ የደረጃ ምልክት መጠቀም የወጣውን አዋጅ ተላልፎ የተገኘ በመሆኑ በአንቀፅ 38(5) የተከለከለ ድርጊት ስር ወንጀል መሆኑን ተናግረው በአንቀፅ 39(4) በተጠቀሰው መሰረት ከ1 ዓመት እስከ 5 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲሁም እስከ 5 መቶ ሺ ብር ቅጣት እንደሚያስቀጣ አሳስበዋል።
ከኢንስቲትዩቱ ፍቃድ ውጪ የብሔራዊ የደረጃ ምልክት የሚጠቀሙ አምራቾች ከድርጊታቸው በአስቸኳይ ታቅበው ህጋዊ በሆነ መንገድ የምልክት ፍቃድ እንዲወስዱ በአፅንኦት ገልፀው ህጋዊ፣ ብቃት ያለውና በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ አምራቾችን እውን በማድረግ የማያቋርጥ ሁለንተናዊ ሀገራዊ እድገትን ለማረጋገጥ በጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ገልፀዋል።ኢ.ደ.ኢ.

