ኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት (AfCFTA) ድርድርን ማጠናቀቋን ተከትሎ መስከረም 29 ቀን 2018 ዓ.ም በሸቀጦች ዘርፍ የንግድ ትግበራ በይፋ ትጀምራለች።


ኢትዮጵያ በቀዳሚነት የፈረመችው የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት (AfCFTA) ድርድርን ማጠናቀቋን ተከትሎ መስከረም 29 ቀን 2018 ዓ.ም በሸቀጦች ዘርፍ የንግድ ትግበራ በይፋ ትጀምራለች።
በማስጀመሪያ ንግዱ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎ ሥጋ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በየብስ ትራንፖርት ቡና፣ የጥራጥሬ ምርቶችና የቅባት እህሎች ወደ ኬንያ፣ ሶማሊያ እና ወደ ደቡብ አፍሪካ ይላካል፡፡
ለዛሬ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት (AfCFTA) ዙሪያ የተዘጋጀ መጣጥፍ እናስነብባችሁ።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና በአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት እ.አ.አ በ2018 በኪጋሊ ሩዋንዳ በተፈረመዉ ማቋቋሚያ ስምምነት የተመሰረተ ነፃ የንግድ ቀጣና ነዉ፡፡
ነፃ የንግድ ቀጣና ማለት በሀገራት ስምምነት መሰረት የሚቋቋም የንግድ ክልል ሆኖ በፈራሚ ሀገራቱ መካከል የሚደረጉ የንግድ ልዉዉጦችን ለመጨመርና ለማሳለጥ ቀረጥ (tariff) እና ሌሎች ቀረጥ ያልሆኑ የንግድ መሰናክሎችን (non-tariff barriers to trade) የሚያስወግድ ወይም የሚቀንስ ነዉ፡፡
በዚህም መሰረት የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናዉ ስምምነቱን ፈርመዉ ባፀደቁት ሀገራት መካከል ያለዉን ምርቶችና አገልግሎቶች ንግድ፣ ኢንቨስትመንትና የሰዎች ነፃ እንቅስቃሴ በማሳለጥ አንድ ዉህድ አህጉራዊ ገበያን ለመፍጠር የተመሰረት ነዉ፡፡
በተጨማሪም አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናዉ የአባል ሀገራት አህጉራዊና አለምአቀፋዊ የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት የማሳደግ፣ የምርትን መሰረት የማስፋፋት፣ አካባቢያዊ የዕሴት ሰንሰለትን የማጠናከር፤ የግብርና ልማት፣ የምግብ ዋስትናና የኢንዱስትሪ ልማትን የመደገፍ፤ አህጉራዊ ትስስርን የማጠናከር እንዲሁም ለአህጉራዊ የጉምሩክ ህብረት (customs union) መመስረት መሰረት የመጣል ዓላማዎች አሉት፡፡
ነፃ የንግድ ቀጣናዉ በዋናነት በአባል ሀገራቱ ዘላቂ እና አካታች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት፣ የፆታ እኩልነትና መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ያለመ ነዉ፡፡
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና መመስረቻ ስምምነትን እስካሁኑ ጊዜ ከ55ቱ የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት 54ቱ (ከኤርትራ በስተቀር) የፈረሙት ሲሆን፤ ከፈረሙትም 48ቱ ስምምነቱን ስላፀደቁት የንግድ ቀጣናዉ አባል ሆነዋል፡፡
ከአባል ሀገራቱ መካከልም ሀገራችን ኢትዮጵያ ትገኝበታለች፡፡ የአባላቱ ቁጥርም ከዚህ በላይ ጨምሮ ሁሉንም የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት የሚያካትት እንዲሆን ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ዋና ፅህፈት ቤት በአክራ ጋና ይገኛል፡፡
በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና በመመስረት በአህጉሪቱ ሀገራት መካከል ያለዉን የኢኮኖሚ ትስስር ማጠናከር እ.አ.አ በ1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት) ሲመሰረት ጀምሮ የነበረ ዕቅድ ሲሆን፤ ይህን ለማሳካት በሀገራቱ የተለያዩ ስምምነቶች ተፈርመዋል (ለምሳሌ የ1991 የአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ማቋቋሚያ ስምምነት)፤ ሌሎች እርምጃዎችም ተወስደዋል፡፡ በዚህም መሰረት በአህጉሪቱ የተለያዩ አካባቢያዊ ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰቦች (regional economic communities) ተመስርተዋል፡፡
ይህም የሆነዉ በዋናነት የአካባቢያዊ ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰቦች (ለምሳሌ የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ (COMESA)) መቋቋም ሁሉንም የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት የሚያካትት አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ለማቋቋም ይረዳል በሚል ፅኑ እምነት ነዉ፡፡
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና መመስረት የአፍሪካ ህብረት እ.አ.አ በ2013 ያወጣዉየ“አጀንዳ 2063” ዕቅድ አካል ሲሆን፤ በዋናነትም በዕቅዱ ላይ የተቀመጠዉን “የተሳሰረች፣ የበለፀገችና ሰላማዊ አፍሪካ”ን የመፍጠር ፓን-አፍሪካዊ ግብ ለማሳካት ይረዳል፡፡
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ከላይ የተገለፁትን ዓላማዎች ለማሳካት በአባል ሀገራቱ የተለያዩ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸዉ ይገልፃል፤ ስራዎቹ እንዲሰሩ የሚያስፈልጉትን የህግና ተቋሟዊ ማዕቀፎችንም ዘርግቷል፡፡
ከነዚህም ስራዎች ውስጥ በአባል ሀገራቱ መካከል በሚደረጉ ድርድሮችና ስምምነቶች ቀረጦችንና ሌሎች ቀረጥ ያልሆኑ ለእቃዎች ንግድ ማነቆ የሆኑትን መሰናክሎች ደረጃ በደረጃ ማስወገድና የአገልግሎቶች ንግድ ደረጃ በደረጃ ነፃ ማድረግን ይገኙበታል፡፡
በኢንቨስትመንት፣ አእምሮአዊ ንብረት መብቶች፣ በውድድር ፖሊሲና በሁሉም ንግድ-ነክ ጉዳዮች ላይ መተባበርም ሌላኛዉ ስራ ነዉ፡፡
በተጨማሪ በጉምሩክ ጉዳዮችና በንግድ ማሳለጫ እርምጃዎች ላይ መተባበር፤መብቶቻቸውንና ግዴታዎቻቸውን በሚመለከት የአለመግባባቶችን መፍቻ መንገድ ማቋቋም፣ ቀጣናዉን ተግባራዊ ለማድረግና ለማስፈፀም ተቋማዊ ማእቀፍ መመስረትና ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ ሌሎች ሀገራቱ ለመስራት የተስማሙባቸዉ ጉዳዮች ናቸዉ።
ሀገራችን ኢትዮጵያም የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና አባል እንደመሆንዋ በእነዚህ ስራዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ ተጠቃሚነትዋን ማሳደግ ይኖርባታል፡፡
ለዚህም መሳካት በተለይ የሀገሪቱን የግል ዘርፍ የሚገጥሙትን የተለያዩ ችግሮች በየጊዜዉ በመፍታት ዐቅሙንና ተወዳዳሪነቱን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ ይህም የመንግስትና የግል ዘርፉ ዘላቂ ዉይይትና ትብብር ይጠይቃል፡፡

