ክቡር ፍስሐ ይታገሱ( ዶ/ር) ፤ እርስዎ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ሆነው በመሾምዎ እንኳን ደስ ያልዎት ለማለት እወዳለሁ- የተከበሩ ሰብስብ አባፊራ

ክቡር ፍስሐ ይታገሱ( ዶ/ር) ፤
እርስዎ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ሆነው በመሾምዎ በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ በመላው የንግዱ ማኅበረሰብ እንዲሁም በራሴ ስም እንኳን ደስ ያልዎት ለማለት እወዳለሁ።
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፤ የኢንዱስትሪ ልማትን ከአገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት፣ ከሥራ ዕድል ፈጠራና ከዘላቂ ብልጽግና ጋር በማያያዝ የግሉን ዘርፍ ጥቅምና ተሳትፎ ለማጠናከር ይሠራል። በዚህ ረገድ፣ የሀገር ውስጥ ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ፣ በኢንዱስትሪውና በንግዱ ዘርፍ መካከል ያለውን ትስስር ለማጠናከርና የኢትዮጵያን ምርቶች ወደ አዳዲስ ገበያዎች ለማስፋፋት ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤትዎ ጋር በቅርበት ለመስራት ያለንን ዝግጁነት ለማረጋገጥ እወዳለሁ።
በተለይም ለአምራቾች የሚሰጡ የቴክኒክና የሎጂስቲክስ ድጋፎችን ማጠናከር፣ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢንዱስትሪ መንደሮችና የረጅም ጊዜ ብድር ተደራሽነት ማሻሻል ለዘርፉ ዕድገት ወሳኝ ናቸው። እነዚህ ጥረቶች የሀገር ውስጥ ምርቶች በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ገበያዎች ያላቸውን ተቀባይነትና እምነት ከማሳደግም በላይ የኢንዱስትሪውን ምርታማነትና ውጤታማነት ያጎለብታሉ።
በሌላም በኩል ፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄንና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ስትራቴጂዎች ማጠናከር፣ የኢትዮጵያ ምርቶችን በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ማድረግ ለአምራቾች አዳዲስ ዕድሎችን ከመፍጠር ባሻገር የአገራችንን የኤክስፖርት አቅም ለማሳደግ ያግዛል።
ከዚህ አንፃር ፤ ምክር ቤታችን የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ተግዳሮቶች በጋራ ለመፍታት፣ ምቹ የንግድ አካባቢን ለመፍጠርና በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል ያለውን የፖሊሲ ውይይትና ትብብር ለማጠናከር ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤትዎ ጋር በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን በድጋሚ አረጋግጣለሁ።
በመጨረሻም ፤በአመራር ዘመንዎ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ዕድገት እንዲፋጠን፣ የግሉ ዘርፍ አስተዋጽኦ እንዲጎለብትና አገራችን በአፍሪካ ቀዳሚ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል እንድትሆን የሚያግዙ ውጤታማ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ እመኛለሁ።
ኢትዮጵያ ታምርት! መልካም የስራ ዘመን ይሁንሎት።
የተከበሩ ሰብስብ አባፊራ አባጆቢር
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት
