የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የ2017 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ::

የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የ2017 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።
የምክር ቤት ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዘዳንት አቶ አንተነህ አዲሱ እንዳሉት ያደጉ አገራት አሁን ላሉበት ደረጃ የደረሱት የግሉ ዘርፍ ተገቢውን ሚና እንዲጫወት ምቹ ሁኔታ በመፍጠራቸውና የግሉ ዘርፍም ድምፁ በተገቢ ሁኔታ እንዲሰማ በአንድነት በመቆማቸው ነው ብለዋል።
የአገራችንና የክልላችን የግል ዘርፍ በተናጠል ከመንቀሳቀስ በየደረጃው ባሉት ምክር ቤቶችና ማህበራት በመታቀፍ ሊንቀሳቀሱ ይገባል ያሉት ፕሬዘዳንቱ የንግድና ዘርፍ ማህበሩ የሚመሰረተው በነጋዴው ፈቃደኝነት ላይ ተመስርቶ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የኢኮኖሚ ዋልታ የሆነው ነጋዴው የህብረተሰብ ክፍል ህጋዊ በሆነ መንገድ ብቻ ሸማቹን እያገለገለ መብትና ጥቅሙ ሲጣስበት ጠበቃ የሚቆምለት ተወካይ የንግድና ዘርፍ ማህበር በመሆኑ ሚናው ከፍተኛ ነው ሲሉ አቶ አንተነህ አክለው ገልጸዋል።



የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዘዳንት ወ/ሮ አምሳለ ነጋሽ በበኩላቸው የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት መቋቋሙ ዓላማው በንግዱ ማህበረሰብና መንግስት መካከል ድልድይ ሆኖ እንዲያገለግል ለማስቻል ነው ብለዋል።
በመድረኩ የምክር ቤቱ የ2017 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃጸም ሪፖርት፣ የ2018 በጀት ዓመት የምክር ቤቱ እቅድና የኦዲት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።
በጉባኤው የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የገበያ ልማት ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ አሰገደች ወልደየስ፣ የቤንች ሸኮ ዞን ንግድና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ጉብላ፣ የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ንግድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ታቻን ጨምሮ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ከፍተኛ አመራሮችና የምክር ቤት አባላት ተገኝተዋል።(የቤንች ሸካ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን)

