የተጠናቀቀው 15ኛው የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ስኬታማ ነበር:- ሰብስብ አባፊራ



የተጠናቀቀው 15ኛው የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ስኬታማ እንደነበር የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሰብስብ አባፊራ ገለጹ፡፡
ንግድ ትርኢቱ እንዲሳካ ስፖንሰር ላደረጉ፣ በትብብር ለሰሩ እና ለተሳተፉ ተቋማትና ባለድርሻ አካላትም የእውቅናና የዋንጫ ሽልማት አበርክተዋል፡፡
የንግድ ትርኢቱ የሀገር ውስጥ ምርቶችን ከማስተዋወቅ ባሻገር በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ የተፈጠሩ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎችን ያስተዋወቅንበት ጭምርነው ሲሉ ገልጸዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡
በየዓመቱ የኢትዮጵያን ይግዙ! በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ! በሚል መሪ ሀሳብ የተካሄደው ዝግጅቱ በግብርናና ማምረቻ፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በአይሲቲ፣ በፋይናንስና ቴክኖሎጂ፣ በሎጂስቲክስ እና በሌሎችም ዘርፎች ምርቶችና አገልግሎቶች ለእይታ የቀረቡበት መድረክ ከመሆኑ አንፃር የኢትዮጵያን የንግድና ኢንቨስትመንት መዳረሻነት የበለጠ በማሳደግ ረገድ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።
በንግድ ትርዒቱ ከዓለም ዓቀፍ የንግድ ተቋማት እና የአገር ውስጥ ኢንተርፕራይዞች ምርቶች እና አገልግሎቶችን ማቅረባቸውን አንስተዋል፡፡


የተለያዩ ሃገራት ኩባንያዎች በሃገራችን የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ በስፋት እንዲሳተፉ በማስቻል ረገድ ውጤታማ እንደነበርና ለገበያ ትስስር፣ ቴክኖሎጂ ለውውጥ፣ እንዲሁም በጋራ ለመስራት አጋጣሚ መፍጠሩን አንስተዋል፡፡
የንግድ ትርኢቱ እንዲሳካ በትብብር ለሰራው ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ለስፖንሰሮች፣ ተባባሪ አካላትና ተሳታፊዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በተያያዘም ዝግጅቱ ለሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለውና ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የንግድ ትርኢቱ ተሳታፊዎች ለኢትዮጵያ ቻምበር ገልጸዋል፡፡
በሀገር ውስጥ ከአነስተኛ እና መካከለኛ እስከ ግዙፍ ኩባንያዎች እንዲሁም ከውጭ ከበርካታ ሀገራት የመጡ ተሳታፊዎች ምርትና አገልግሎታቸውን አቅርበዋል፡፡
ከምርትና አገልግሎት አቅርቦት ባሻገር የፓናል እና የቢዝነስ ለቢዝነስ ውይይት በተካሄደበት የንግድ ትርኢት በርካታ ጎብኝዎች ተገኝተዋል፡፡
የዝግጅቱ ተሳታፊዎችም የንግድ ትርኢቱ ኩባንያዎች የንግድ ትስስር እንዲፈጥሩ፣ የገበያ እድላቸውን እንዲያሰፉ እና የቴክኖሎጂ እና የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ እድል መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡
መሰል ዝግጅቶች ሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ከውጭ ተቋማት ጋር እንዲተዋወቁና የገበያ እድል እንዲፈጠር የሚያደርጉ በመሆናቸው ተሳታፊዎች እድሉን ላመቻቸው ለኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ለስፖንሰሮች እንደየደረጃቸው፣ ለተባባሪ አካላትና ተሳታፊዎች እንዲሁም በዝግጅቱ የነቃ ተሳትፎ ለነበራቸው ተሳታፊዎች የእውቅና ሽልማት እና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል ፡፡

