የቻይና (ሻንሺ) -ኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ እና ንግድ ትብብር ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሄደ።


የቻይና (ሻንሺ) -ኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ እና ንግድ ትብብር ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሄደ ።
በጉባኤውም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እንዳለው መኮንን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምሥራቅ፣ እስያ እና ፓስፊክ ሀገራት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሣደር ደዋኖ ከድር፣ የኢንቨሥትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመሥገን፣ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት የቦር ድ አባላት እና የሁለቱ ሀገራት የቢዝነስ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።

የሁለቱ ሀገራት ንግድና ኢንቨሥትመንት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ሲሆን ኢትዮጵያም በቻይና ቤልት እና ሮድ ኢንሼቲቭ፣ በፎካክ እንዲሁም በብሪክስ ያላት ተሣትፎ እያደገ መምጣቱ በጉባኤው ላይ ተጠቁሟል።
ቻይና በኢትዮጵያ በመሠረተ ልማት ግንባታ እና በሌሎች የልማት ሥራዎች ትልቅ አሥተዋጽኦ የምታበረክት ሀገር መሆኗም ነው የተገለጸው።
ኢትዮጵያ ከምትከተለው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ አጀንዳ አንጻር እየወሠደቻቸው የማሻሻያ ሥራዎች ለኢንቨሥትመንት ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ በመሆኑ የቻይና ኩባንያዎች ትኩረት በተሠጣቸው የማምረቻ ኢንዱሥትሪ፣ በማዕድን፣ በአይሲቲ እና በሌሎችም መሥኮች በኢትዮጵያ ያላቸውን የኢንቨሥትመንት ድርሻ እንዲያሣድጉ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጥሪ አቅርቧል።


የሻንሺ ግዛት የንግድ ዲፓርትመንት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ፋን ዋንቹን በበኩላቸው ኢትዮጵያ ያላት ምቹ ጅኦግራፊያዊ መገኛ እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትልቅ የንግድና ኢንቨሥትመንት አጋጣሚ የሚፈጥር በመሆኑ ለሻንሺ ግዛት ኩባንያዎች ትልቅ እድል መሆኑን ገልጸዋል።


