የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ ጋር የከተማዉን ንግድ ምክር ቤት ለማጠናከር ተወያዩ።

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ ጋር የከተማዉን ንግድ ምክር ቤት ለማጠናከር ተወያዩ።
በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት በተከበሩ አቶ ሰብስብ አባፊራ የተመራ የምክር ቤቱ የዳይሬክተሮች ቦርድ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከአቶ አብዱላሂ አደም ዩሱፍ ጋር ያደረገዉ ዉይይት የድሬዳዋ ከተማ ንግድና ዘርፍ ማህበራትን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነዉ።
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰብስብ አባፊራ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፤ የድሬዳዋ ከተማ ንግድ ምክር ቤት በአገሪቱ ከተመሰረቱት አምስት ቀደምት ቅርንጫፎች አንዱ ነው። ድሬዳዋ ከአዲስ አበባ ከተማ ቀጥሎ ሰፊ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድባት ከተማ ሆና ሳለች፣ የንግድ ምክር ቤቱ አሁን በሚገኝበት ደረጃ መዳከሙ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም፣ የከተማ አስተዳደሩ የንግድ ምክር ቤቱን ሚና በአግባቡ ካለመረዳት የተነሳ ተገቢውን ድጋፍ ሳያደርግ መቆየቱ ትክክል አለመሆኑን በመጠቆም፣ በቀጣይ የከተማዋን የንግድ እንቅስቃሴ የሚያነቃቁና ንግድ ምክር ቤቱን የሚያጠናክሩ ስራዎች ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዉ፣ አሁን ያሉት ከንቲባ ስለንግድ ምክር ቤት በቂ ግንዛቤ ስላላቸዉ ለድሬዳዋ ንግድ ምክር ቤት ማንሰራራት መልካም አጋጣሚ እንደሆነም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ የንግድ ምክር ቤቶች የአገርን ንግድና ኢንቨስትመንትን በማስፋፋትና ህገ ወጥ ንግድን በመከላከል ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸዉን አበርክቶ በማብራራት በየደረጃዉ ያሉ የመንግስት መዋቅሮች ንግድ ምክር ቤቶችን በመደገፍ የሚጠበቅባቸዉን ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ አለባቸዉ ብለዋል።
የድሬዳዋ ከተማ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አዲል ኢሲሃቅ በበኩላቸዉ የከተማዋ የንግድ ም/ቤት እንዲዳከም ያደረገዉ ተገቢ የሆነ ድጋፍ አለማድረግ መሆኑን ጠቁመዉ፣ አሁን በአዲስ መልክ የተደራጀዉ አስተዳደር የምክር ቤቱን ሚና በመረዳት እንዲደግፈዉ ጠይቀዋል።

የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ አቶ አብዱላሂ አደም የማንኛዉ ድርጅት ጥንካሬ የሚመሰረተዉ በአባላቱ ጥንካሬ ላይ እንደሆነ በመጠቆም ም/ቤቱን ለማጠናከር የንግዱ ማህበረሰብ የምክር ቤቱን አላማና የሚያበረክትለትን ጠቀሜታ እንዲረዳ ማድረግ ነዉ ብለዋል። ይህንን ለማድረግ ግን ጠንካራ ምክር ቤት መኖር አለበት።
ከዚህ አንፃር የከተማ አስተዳደሩ በንግድ ቢሮ በኩል መድረክ በማመቻቸት የምክር ቤቱ አባል እንዲሆኑና የሚጠበቅባቸዉን የአባልነት ግዴታ እንዲወጡ የማድረግ ስራ እንሰራለን ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ማንኛዉንም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነዉ ያሉት ከንቲባዉ ይህንን ድጋፍ ለማድረግ ግን በንግድ ም/ቤቱ በኩል ዝግጁነና ተነሳሽነት መኖር አለበት ብለዋል።

