የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትና የኢትዮጵያ አበባ ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ላኪዎች ማህበር ጋር ውይይት

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትና የኢትዮጵያ አበባ ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ላኪዎች ማህበር የግሉ ዘርፉ በአገር ኢኮኖሚ ውስጥ ሊጫወት በሚገባው ሚና እና ሊኖረው በሚገባ ድርሻ ዙሪያ ተወያዩ፡፡
በኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ዋና ፀሐፊ ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) የተመራ የም/ቤቱ የማኔጅመንት አባላት ቡድን አባላቱ ከሆኑት የዘርፍ ማህበራት አንዱ ከሆነው የኢትዮጵያ አበባ አትክልት ፍራፍሬ አምራች ላኪዎች ማበር ማኔጅመንት አባላት ጋር የግሉን ዘርፍ ሚና ከፍ ለማድረግ በቅንጅት መስራት በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡
የኢ/ን/ዘ/መ/ም/ቤት ዋና ፀሐፊ ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ በአሁኑ ወቀት የግሉ ዘርፍ ለአገር አጠቃላይ ኢኮኖሚ ዕድገት እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ ከሚጠበቅበት አኳያ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን በማንሳት ይህንን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ እና ተገቢውን ቦታና ድርሻ እንዲኖረው ለማድረግ የግሉ ዘርፍ ከመንግስት ጋር ተቀራርቦ የሚሰራ የግሉ ዘርፍ ድምፅ በሚገባ እንዲሰማና ምቹ የስራ ከባቢ አግኝቶ ሚናውን እንዲጫወት በአግባቡ የሚወክለው ጠንካራ ተቋም እንደሚያስፈልገው በማንሳት፤ ለዚህ ዓላማ ከተቋቋመ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ከወትሮው በተሻለ ሁኔታ ለመስራት እራሱን በአዲስ መልክ አደራጅቶና መዋቅራዊ ለውጥ አድርጎ ወደ ስራ መግባቱን አንስተዋል፡፡
ያደጉ አገራት አሁን ላሉበት ደረጃ የደረሱት የግሉ ዘርፍ ተገቢውን ሚና እንዲጫወት ምቹ ሁኔታ በመፍጠራቸውና የግሉ ዘርፍም ድምፁ በተገቢ ሁኔታ እንዲሰማ በአንድነት በመቆማቸው ነው ያሉት ዶ/ር ቀነኒሳ፣ የአገራችን የግል ዘርፍም በተናጠል ከመንቀሳቀስ በየደረጃው ባሉት ምክር ቤቶችና ማህበራት በመታቀፍ ሊንቀሳቀሱ ይገባል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አበባ ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ላኪዎች ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ በበኩላቸው አሁን ላይ የግሉ ዘርፍ ትክክለኛ ድምፅ ሊሆን የሚችለውና የግሉን ዘርፍ ከመንግስት ጋር ሊያገናኝ የሚችለው አገር አቀፍ ተቋም የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ም/ቤ መሆኑን በማንሳት፣ በተለይም ለግሉ ዘርፍ ምቹ የስራ ካባቢን ለመፍጠርና በግሉ ዘርፍ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ በሚችሉ ፖሊስዎች ላይ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር የምክክር መድረኮችን በማመቻቸት የግሉ ዘርፍ ድምፅ በአግባቡ እንዲሰማ ከማድረግ አንፃር አሁን ላይ አበረታች ለውጥ መታየቱንና በመንግስት ዘንድ ያለው የም/ቤቱ ተደማጭነትም እየጨመረ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡
ማህበራቸውም እንደ አንድ የም/ቤቱ አባል የአባላቱን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ ከም/ቤቱ ጋር ተቀናጅቶ ለመስራት ከወትሮው በተሸለ ሁኔታ ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ሁለቱ ተቋማት በጋራ የሚሰሯቸውን ተግባራት ለይቶ በማውጣት የትግበራ መርሐ ግብር የሚያዘጋጅ የጋራ ታስክ ፎርስም አቋቁመዋል፡፡


