የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና ከፓን አፍሪካ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት በጋራ ለመስራት ተወያዩ፡፡
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ሰብስብ አባፊራ ከፓን አፍሪካ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ክቡር ገና ጋር የሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ግንኙነቶች በሚጠናከሩበት ሁኔታ ላይ ተወያዩ፡፡
በውይይታቸው ወቅት የኢትዮጵያ የንግድን ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት አቶ ሰብስብ አባፊራ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና እንደመሆንዋ ብዙ የአፍሪካ ስብሰባዎች ይካሄዳሉ በመሆኑም ከፓን አፍሪካ የንግድና የኢንዱስትሪ ጋር የሚኖረን ግንኙነት ከትብብር ያለፈ ነው፣ ብዙ ስራዎችን አብረን እንሰራለንም ብለዋል፡፡
አያይዘውም የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ወርቃማ ጊዜያትን ያሳለፈበት ወቅቶችን አሁንም እንዲደገም እንፈልጋለን ፤ እኛ እንደ ምክር ቤት ብዙ ሪፎርሞችን እየሰራን ነው፣ ብዙ አገልግሎቶችንም በቅልጥፍና መስጠት አለብን ብለን አቅደን ስራዎች እየከወን በመሆኑ ይህ የሁለቱ ምክር ቤቶች ትብብር መልካም አጋጣሚ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ምክር ቤቱ የግል ዘርፉን ተሳትፎ እንዲጎለብት ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት የምክር ቤቱ ፕሬዚደንት ከፓን አፍሪካ ንግድና ኢንዱስትሪ ጋርም ብዙ ተሞክሮና ልምዶች ይገኛሉ ፣ ይህም ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ የግሉ ዘርፍ እድገት አስተዋፅኦው የጎላ በመሆኑ ትብብራችን ይቀጥላል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የፓን አፍሪካ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ክቡር ገና በበኩላቸው የምክር ቤቱን አሁን ትኩረት አድርጎ የሚሰራባቸውን ፕሮግራሞችን በተለይም የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ፣ የዲጅታላይዜሽን እና በሌሎች ጉዳዮችን የግሉን ዘርፍ ግንዛቤ ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አክለውም የፕሮስፐሪቲ አፍሪካ ኮንፈረንስ በሚቀጥለው መስከረም በአዲስ አበባ የሚካሄድ በመሆኑ ይህንን እድል የግሉን ዘርፍ የምናስተዋውቅበት በመሆኑ ከሁለቱ ም/ቤቶች በሚቋቁም የጋራ ኮሚቴ በትብብር መሰራት አለበት ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት ዋና ፀኃፊ ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ በበኩላቸው የፓን አፍሪካ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት አብሮን በጋራ ለመስራት መፈለጉ አመስግነው ፣ ፓን አፍሪካን በእቅድ ከያዛቸው ስድስት ፕሮግራሞች ብዙዎቹ በተለይም ዲጂታላይዜሽንና የሴቶች ሊደርሽፕ ማሳደግ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትም በእቅድ አካቶ እየሰራባቸው ያሉና በትኩረት የሚተገብራቸው መሆኑን ጠቁመው ወደ ፊት ጠንካራ የስራ ትብብሮችና ተሞክሮዎች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል፡፡

