የዓለም አቀፍ ጥራት ኤክስፖ በጥራት መንደር ከህዳር 11 እስከ ህዳር 14/208 ዓ.ም በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ዶክተር ካሳሁን ጎፌ ተከፍቶ እየተካሄደ ነው፡፡

የዓለም አቀፍ ጥራት ኤክስፖ በጥራት መንደር ከህዳር 11 እስከ ህዳር 14/208 ዓ.ም በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ዶክተር ካሳሁን ጎፌ ተከፍቶ እየተካሄደ ነው፡፡
ይህ ዝግጅት የጥራት እውቅና ሰርቲፊኬት ያላቸው ተቋማት ብቻ የሚሳተፉበት መሆኑን የፕሮግራሙ አዘጋጅ የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ገልጿል፡፡
በዝግጅቱ ላይ ከተለያዩ ሀገሪቱ አካባቢዎች የጥራት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት ያላቸው ተቋማት ብቻ እየተሳተፉ ሲሆን የሚካሄደውም “ጥራት፡-በተለየ እሳቤና ፈጠራ” በሚል መሪ ሐሳብ ነው፡፡
በጥራት መንደር የሚገኙ ተቋማት የትኞቹ ናቸው? አምስት ተቋማት ሲኖሩ አራቱ የጥራት መሰረተ ልማት ተቋማት ናቸው::
1. የቴክኖሎጂ ባለስልጣን
2. የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት
3. የስነ ልክ ኢንስቲትዩት
4. የደረጃዎች ኢንስቲትዩት
5. የአክሬዲቴሽን ኢንስቲትዩት ናቸው፡፡
የቴክኖሎጂ ባለስልጣን ተጠሪነቱ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሲሆን ቀሪዎቹ ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት የጥራት መሰረተ ልማት ተቋማት በሚል የሚታወቁ ናቸው፡፡ ጥራት ያለው ምርትና አገልግሎት እንዲኖር ለማስቻል የሚሰሩ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ናቸው፡፡
የዚህ ኤክስፖ ዓላማም ህብረተሰቡ ጥራትን መሰረት አድርገው የሚሰሩ ተቋማትን እንዲያውቅና እንዲያበረታታ፣ ምርቶችን እንዲገዛ እንዲሁም የንግዱ ማኅበረሰብ ወደነዚህ ተቋማት በመምጣት የጥራት መመዘኛዎችን መሰረት በማድረግ ማምረት እንዲችል ግንዛቤ መፍጠር ነው፡፡
የተቀመጡ የምርትና አገልግሎት መስፈርቶችን በማሟላትና በ International Organization for Standardization (ISO) መሰረት በማምረት ተወዳዳሪነትን ማሳደግና የተጠቃሚውን ደህንነት መጠበቅም ሌላው ዓላማ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት የማርኬቲንግና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ተክኤ ብርሃነ አስመጭ እና ላኪዎች፣ አምራቾች እና ሌሎች ነጋዴዎች ለሚሰጧቸው አገልግሎቶች እና ለሚያቀርቧቸው ምርቶች የተቀመጡ መስፈርቶችን ሲያሟሉ የእውቅና ምስክር ወረቀት እንደሚሰጣቸውና በየጊዜው ፍተሻ እና ምዘና እንደሚደረግላቸው ገልጸዋል፡፡
የተስማሚነት ምዘና ድርጅትም ጥራትን ለማረጋገጥ በቀዳሚነት የፍተሸ ላብራቶሪ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በባዮ ኬሚካልና በኤሌክትሮ ሜካኒካል 9 ላብራቶሪዎች አሉት፡፡ ሁለተኛው የኢንስፔክሽን አገልግሎት ሲሆን ሶስተኛው ደግሞ የሲስተም ሰርቲፊኬሽን ነው፡፡ ይህም ከአይ ኤስኦ ስታንዳርድ አንጻር የጥራት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት መስጠት ማለት ነው፡፡
በየዓመቱ የሚካሄደው ይህ ዝግጅት የጥራት እውቅና ምስክር ወረቀት ያላቸውን ከሌላቸው ለመለየትና እውቅና ምስክር ወረቀት የሌላቸው ወደ ስታንዳርድ እንዲመጡና ማረጋገጫ እንዲኖራቸው ለማስገንዘብ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡

