የግሉ ዘርፍ በንግድ ፓሊሲው ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ኖሮት የሚጠበቅበትን መወጣት እንዲችል ማድረግ ቁልፍ ተግባራችን ነው፡- ሰብስብ አባፊራ

ለኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣ ለተወሰኑ አባል ምክር ቤት አመራሮች እና ለምክር ቤቱ የስራ ኃላፊዎች በቅርቡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባፀደቀዉ የኢትዮጵያ የንግድ ፖሊሲ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የውይይት መድረክ እያካሄድን ነዉ።
ይህም የግሉ ዘርፍ በፓሊሲው ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ኖሮት የሚጠበቅበትን መወጣት እንዲቻለው ማድረግ ቁልፍ ተግባራችን ይሆናል ብለን ባስቀመጥነው አግባብ መነሻነት የተከናወነ የመጀመሪያ ዙር የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ነው።
ከኢፌዴሪ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እየተካሄደ ያለው ይህ መድረክ የምክር ቤት አመራሮች
በሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የንግድ ስርአትን በአግባቡ ለመምራት፣ በተመረጡ የገበያ ክፍተት ባለባቸው ዘርፎች ክፍተቶችን ለመሙላት የሚደረጉትን ጥረት ለማጠናከር፣ የሀገራችንን የወጪ ንግድና ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ረገድ በፖሊሲው የተቀመጡ አበይት ግቦችን የበለጠ ለመረዳት፣ ፍትሃዊ የንግድ አሰራርን ለመዘርጋት እንዲሁም የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ተወዳዳሪነትን እንዲገነቡና ምርታማነትን እንዲያሳድጉ ለማስቻል የግሉን ዘርፍ ሚና በግልፅ አውቆ ለመንቀሳቀስ ብሎም በዘርፉ ያሉ ተግዳሮችን ለመፍታት በሚያስችል መልኩ ወደስራ ለመግባት የሚያስችል ነው፡፡
ከሳምንት በፊት ባስተላለፍኩት መልዕክትም ከፖሊሲ ዝግጅቱ ጀምሮ ተሳትፎ ለነበራቸውና በየደረጃው ለሚገኙ አካላት በመላው የንግዱ ማኅበረሰብ፤ በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና በራሴ ስም ላቅ ያለ ምስጋናዬን ያቀረብኩኝ ሲሆን ፤ዛሬም ለኢፌዴሪ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናውን እየሰጡልን ላሉ የሚኒስቴር መ/ቤቱ አመራሮች እና ባለሙያዎች ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
በመጨረሻም በፓሊሲው ላይ የሚካሄደው ውይይትና የግንዛቤ ማስጨበጫ በስፋት ተደራሽ በሚሆን መልኩ አጠናክረን የምንቀጥልበት መሆኑን አረጋግጣለሁ።
ሰብስብ አባፊራ አባጆቢር
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት

