ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ከኢትዮጵያ ቡና ቆይዎች ፈጭቶ አሻጊዎች የዘርፍ ማህበራት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ጋር በጽ/ቤታቸዉ ተወያይተዋል።

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ከኢትዮጵያ ቡና ቆይዎች ፈጭቶ አሻጊዎች የዘርፍ ማህበራት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ጋር በጽ/ቤታቸዉ ተወያይተዋል።
ዋና ፀሐፊዉ የምክር ቤቱን ዋና ዋና ተልዕኮዎችንና በአዋጅ የተሰጡትን ስልጣኖች በዝርዝር ያስረዱ ሲሆን የግሉ ዘርፍ ተሰሚነትን ለማግኘት ተደራጅቶ መንቃሳቀስ ተገቢ ስለሆነ ቡና በመቁላትና ፈጭቶ በማሸግ ዘርፍ የተሰማሩት በዘርፋቸዉ በማህበር መደራጀታቸዉ ይበል የሚያሰኝ ነዉ ብለዋል። የዘርፍ ማህበሩ የበለጠ ለመጠናከርና አስፈላጊዉን ድጋፍ ለማግኘት የአገር አቀፉ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አባል መሆን እንዳለበትም አሳዉቀዋል።
የኢትዮጵያ ቡና ቆይዎችና ፈጭቶ አሻጊዎች የዘርፍ ማህበራት ፕሬዚዳንት አቶ ወንድምአገኝ አለማየሁ በበኩላቸዉ የዘርፍ ማህበሩ በቡና ቆይነትና ፈጭቶ ማሸግ ዘርፍ የተሰማሩ ከ20 በላይ ኩባንያዎችን ይዞ መመስረቱን ጠቁመዉ ምንም እንኳን የዘርፍ ማህበሩ ህጋዊ እዉቅና አግኝቶ ከተመሠረተ ገና አንድ ዓመቱ ቢሆንም መስራች ኩባንያዎቹ በዘርፉ የበርካታ አመታት ልምድ ያላቸዉ ናቸዉ ብለዋል።

የዘርፍ ማህበሩ ዋነኛ ዓላማም ለዘመናት ወደ ዉጭ እየተላከ ባለዉ አረንጓዴ ቡና ላይ እሴት ጨምሮ መላክ ነዉ ያሉት አቶ ወንድምአገኝ አባላቶቹም ከጥቃቅንና አነስተኛ እስከ ላኪዎች ያሉ መሆናቸዉንም አስረድተዋል።
የዘርፍ ማህበሩ አቅሙን በአግባቡ ለመገንባትና በአገር አቀፍ ደረጃ የተራጁ ነጋዴዎችና አምራቾች የሚያገኙትን ጥቅማጥቅሞች ለማግኘት ከኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር ተቀራርቦ ለመስራት እንደሚፈልጉና አመጣጣቸዉም ይህንኑን ግንኙነት ለመፍጠር መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የግሉ ዘርፍ ድምፅና የመንግስትና የግሉ ዘርፍ አገናኝ ድልድይ እንደመሆኑ መጠን አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችን እንደሚሰጣቸዉ ዶ/ር ቀነኒሳ አረጋግጠዉላቸዋል።

