Mon - Fri: 8:30 - 05:30 PM
info@ethiopianchamber.com

Read more

Dec 17, 2025 .

ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ እያደረጉ ላለዉ ታሪካዊ ጉብኝት ያለኝን ጥልቅ አድናቆት እገልጻለሁ፡- ሰብስብ አባፊራ አባጆቢር

  

የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ናሬንድራ ሞዲ ቀደምት የሰዉ ልጅ መገኛ ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ በመምጣት ጉብኝት ማድረጋቸው፣ በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ስም ከልብ የመነጨ የእንኳን ደህና መጡ መልእክት ሳስተላልፍ ታላቅ ክብርና ደስታ ይሰማኛል።

ይህ ታሪካዊ አጋጣሚ እና ክስተት በታላላቆቹ የኢትዮጵያ እና የህንድ ሀገራት መካከል ያለውን የወዳጅነት፣ የትብብር እና የጋራ ዕድገት ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር ያለንን ቃል ኪዳን የሚያድስ ነው። በኢትዮጵያ እና በህንድ መካከል ያለው የዲፕሎማሲያዊ እና የኢኮኖሚ ግንኙነት ለሁለቱ ሀገራት ዘላቂ ወዳጅነት ምስክር ነው። ይህም የክቡር ጠቅላይ ሚንስትራችን ዶ/ር አቢይ አህመድ የዲፕሎማሲ ሥራ ከምንጊዜም በላይ እየተጠናከረ መምጣቱን ያሳያል።

ላለፉት አስርት ዓመታት ህንድ ለኢትዮጵያ የቅርብ አጋር በመሆን ለጋራ እድገት አስተዋፅዖ ስታደርግ ቆይታለች።
በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍም ግንኙነታችን እያበበ ይገኛል። ህንድ አሁንም የኢትዮጵያ ቁልፍ የንግድ አጋር ሆና ቀጥላለች። እ.ኤ.አ. በ2024 መረጃ መሰረት፣ ኢትዮጵያ ወደ ህንድ የምትልከው ምርት ዋጋ ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ የደረሰ ሲሆን፣ እንደ ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ የጥራጥሬ እህሎች እና ቆዳ እና የቆዳ ዉጤቶች የመሳሰሉት ምርቶች የኤክስፖርት ድርሻችንን ዋናውን ቦታ ይይዛሉ።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከህንድ መድኃኒቶችን፣ ማሽነሪዎችን፣ ኬሚካሎችን እና የኤሌክትሪክ ዕቃዎችን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችን የምታስገባ ሲሆን፣ ይህም በ2024/25 ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሆኗል። የኢትዮጵያ የንግድ ተቋማት የህንድን ሰፊ ገበያ በመጠቀም ላይ ሲሆኑ፣ የህንድ ኩባንያዎች ደግሞ ለኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያደረጉ ይገኛሉ።

በተለይም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በመሰረተ ልማት ዝርጋታ መስኮች በኢትዮጵያ የተሰማሩ የህንድ ኩባንያዎች የስራ እድል በመፍጠር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ እና የክህሎት ልማትን በማፋጠን ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ይገኛል።

ይህ የንግድ ልውውጥ በሁለቱ ሀገሮች መካከል እያደገ የመጣውን ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር እና ወደፊት ሰፋፊ እድሎች እንዳሉ ያመለክታል። ኢትዮጵያ እና ህንድ የብሪክስ (BRICS) አባላት መሆናቸው ያላቸውን ልዩ የኢኮኖሚ ትስስር ግምት ውስጥ በማስገባት ለሁለቱም ሀገራት የተሻለ ኢኮኖሚ ጥቅሞችን ያስገኛል።

አብዛኛው የዓለም የተፈጥሮ ሀብትና ወጣት የሰው ኃይል ያለው በደቡብ ሀገራት (አፍሪካ፣ እስያ፣ ላቲን አሜሪካ) በመሆኑ፣ ትብብሩ የዓለምን ኢኮኖሚ መሪነት ወደ ደቡብ እያዞረው ስለሆነ፣ ሁለቱ ሀገራት የንግድ እና የኢንቨስትመንት ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር ያደርጋል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ ባላት የተፈጥሮ ሀብትና የሰዉ ሃይል በዓለም መድረክ “ተመዝጋቢ” ብቻ ሳትሆን “መሪ” እንድትሆን ዕድል ይፈጥራል፡፡ ከሚፈጠረዉ የኢኮኖሚ ዕድሎች እና  ጠንካራ የኢኮኖሚ ግንኙነት የግሉ ዘርፎቻችንም በእጅጉ ተጠቃሚ ይሆናሉ ብሎ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ያምናል፤ ለስኬቱም ጠንክሮ ይሰራል፡፡

በቅርቡ በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት (ECCSA) እና በህንድ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች ፌዴሬሽን (FICCI) መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ (MoU) በአጋርነታችን ውስጥ ወሳኝ ምዕራፍ ነው። ይህ ታሪካዊ ስምምነት በንግድ ማህበረሰቦቻችን መካከል ጥልቅ ትብብር ለመፍጠር መንገድ የሚጠርግ ነው። ይህም በኢትዮጵያ እና በህንድ መካከል ያለውን የንግድ እና የኢንቨስትመንት ልውውጥ ለማሳደግ አዲስ ምዕራፍ መጀመሩን ያበስራል። በዚህ የመግባቢያ ሰነድ አማካኝነት የላቀ ትብብርን ለማመቻቸት፣ የግሉን ዘርፍ እድገት እና ተጠቃሚነትን ለመደገፍ እና አዳዲስ የትብብር እድሎችን ለመፍጠር፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ እና የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር ሙሉ በሙሉ ቁርጠኛ ነን። በግሉ ዘርፎቻችን መካከል በሚኖር የትብብር መንፈስ፣ ኢትዮጵያ እና ህንድ በሚቀጥሉት ዓመታት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚሸጋገሩ እናምናለን።
አባላቶቻችን እና የንግድ ድርጅቶች ከዚህ አጋርነት ተጠቃሚነታቸውን እንዲያሳድጉ ለመደገፍ፣ እንዲሁም ለኢንቨስትመንት፣ ለፈጠራ እና ለዘላቂ ልማት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር በጋራ እንሰራለን።

ባጠቃላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ እያደረጉ ላለዉ ታሪካዊ ጉብኝት ያለኝን ጥልቅ አድናቆት በድጋሚ እየገጽኩ  የሀገሬ ኢትዮጵያና የህንድ የሁለትዮሽ ግንኙነት ዘላቂነት እና ስኬት አስተዋፅዖ ለማድረግ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ምንጊዜም ዝግጁ መሆኑን እገልጻለሁ፡፡
አመሰግናለሁ!
ሰብስብ አባፊራ አባጆቢር
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Ethiopian Chamber of Commerce and Sectoral Associations

Contact Info

Mon - Fri : 8:00 AM - 05:00 PM
Sat : 8:00 - 06:00 PM
+251 115 514 005
info@ethiopianchamber.com
+251-115-517699
517

Office Address

Mexico Square, Addis Ababa, Ethiopia