ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) 4ኛው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ 2018ን በይፋ ከፈቱ::



ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) 4ኛው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ 2018ን በይፋ በከፈቱበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ ሀገራዊ ምርትን ማሳደግ ከምጣኔ ሀብት ዕድገት ባለፈ የሀገርን ሉዓላዊነት እና ነጻነት ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
“አለማምረት በሌሎች ሰዎች በጎ ፈቃድ ላይ እንድንወድቅና ለተለያዩ ችግሮች እንድንጋለጥ ያደርገናል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው።
በግብርናው ዘርፍ በተለይም እንደ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር እና የማምረቻ መሣሪያዎችን በሀገር ውስጥ ማምረት ካልተቻለ፣ የምግብ ዋስትናን እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እንደማይቻል አጽንኦት ሰጥተዋል።
ባለፉት ሁለት ወራት በነዳጅ እና በጋዝ አቅርቦት ላይ ያጋጠመውን ፈተና በመጥቀስ፣ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የጋዝ እና የነዳጅ ሀብት እያላት ማምረት ባለመቻሏ በኢንዱስትሪው እና በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል መፈጠሩን በማሳያነት አንስተዋል።

“እርዳታ የሚቀበል፣ ምግብ የሚለምን እና ፍላጎቱን በሙሉ በገቢ ምርት ላይ ብቻ የመሠረተ ሀገር፣ ነጻ እና ሉዓላዊ ነኝ ማለት አይችልም” ነው ያሉት።
ጥገኝነት እና ልመና እስካላበቃ ድረስ ሀገራዊ ክብርን ማስጠበቅም ሆነ ለልጆች የሚተርፍ ነጻነትን ማረጋገጥ አዳጋች እንደሚሆንም አመላክተዋል።
በመሆኑም፣ ከጥገኝነት የተላቀቀች እና ክብሯ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ለመገንባት “የኢትዮጵያ ታምርት ቤተሰቦች” እና መላው የኢንዱስትሪው ዘርፍ ተዋናዮች ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የተጀመረውን የማምረት ንቅናቄ በትጋት፣ በኅብረት እና በቁርጠኝነት በማስቀጠል፣ ሉዓላዊነቷ የተከበረ ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ ሁሉም በቁርጠኝነት እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል።(EBC)

