14ኛው የኢትዮ- ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ዐብይ ኮሚቴ ስብሰባ
ከመጋቢት 4 – 8 ቀን 2017 የሚካሄደዉ 14ኛው የኢትዮ– ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒትን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ የተቋቋመው ዐብይ ኮሚቴ የመጀመሪያ ስብሰባዉን አካሄደ።
ይህንኑ መድረክ የመሩት በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የወጪ ንግድ ትስስርና ፕሮሞሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ያስሚን ውሀብረቢ እና የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ፀኃፊ ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ ሲሆኑ ፤ በውይይቱ ላይም ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር፥ ከውጪ ጉዳይ፥ ከኢንዱስትሪ ፣ ከስራና ክህሎት እና ከማዕድን ሚኒስቴር እንዲሁም ከተጠሪ መ/ቤቶች የተወጣጡ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
‘’የኢትዮጵያን ይግዙ‘’ በሚሉ መሪ ሃሳብ የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱ ፤ ጠንካራና ዘላቂ አቅም ያለዉ የግል ዘርፍ በመፍጠር ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲያድግ የማገዝ፤ በሌላም በኩል የግሉ ዘርፍ የዓለም ዓቀፍ የገበያ ትስስሮችን የሚፈጥርበት፣የእውቀት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያደርግበት ብሎም የአምራች እና አገልግሎት አቅራቢዎች ከዓለም ዓቀፍ ኩባንያዎች ጋር ልምድ የሚለዋወጡባቸው መድረኮች በማዘጋጀት ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ምቹ ሁኔታዎች እንዲኖሩ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ዓላማ ያለው ነው፡፡
ለአምስት ቀናት በሚቆየው ዓለም ዓቀፍ የንግድ ትርዒቱ ከዋናው መርዐ ግብር ባሻገር የአቻ ለአቻ የንግድ መድረክ፥ የቢዝነስ ፎረም እና የፓናል ውይይቶች ይካሄዳሉ፡፡

