15ኛው ኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ለሀገር ውስጥ ምርቶችና አገልግሎቶች ሰፊ እድል የሚፈጠርበት መሆኑ ተገለጸ፡፡

15ኛው ኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ለሀገር ውስጥ ምርቶችና አገልግሎቶች ሰፊ እድል የሚፈጠርበት መሆኑ ተገለጸ፡፡
ከጥር 27 እስከ የካቲት 1 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄደውን የንግድ ትርኢት በተመለከተ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። መግለጫውን የሰጡት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሀገር ውስጥ ንግድ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሊቁ በነበሩ እና የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ናቸው፡፡

የሀገር ውስጥ ንግድ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ሊቁ በነበሩ የንግድ ትርኢቱ የኢትዮጵያ ምርቶችና አገልግሎቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና ሰፊ የገበያ እንድል እንዲፈጠር የሚያግዝ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እየጣረች ባለችበት እንዲሁም የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ተግባራዊ ያደረገች ሀገር በመሆኗ መሰል ዝግጅቶች ምርትና አገልግሎትን በማስተዋወቅ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ፋይዳቸው የላቀ መሆኑን አቶ ሊቁ በመግለጫው ላይ አንስተዋል፡፡
የሀገር ውስጥ ምርቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅና የገበያ ትስስርን ለማጠናከር፣ የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ስላለው የንግድና ኢንቨስትመንት ሁኔታ እንዲረዱና ኢንቨስት እንዲያደርጉ፣ ቴክኖሎጂና አሰራር እንዲለዋወጡ የሚያደርግ መሆኑን ዋና ጸሐፊው ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ ገልጸዋል፡፡
በመስቀል አደባባይ በሚካሄደው የንግድ ትርኢት ላይ ከ20 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ከ50 በላይ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች እንዲሁም ከ300 በላይ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ምርትና አገልግሎቶቻቸውን በማቅረብ እንደሚሳተፉም አስታውቀዋል።
ዝግጅቱ ምርትን ከማስተዋወቅ ባለፈ በተቋማት መካከል የልምድ ልውውጥና የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የሀገሪቱን የንግድ እንቅስቃሴ በማነቃቃትና አዳዲስ የውጭ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ እንዲሁም ሀገራዊ ገጽታን በመገንባት ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑ ተብራርቷል፡፡
የንግድ ትርኢቱ የፊታችን የካቲት 27 ቀን 2018 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ የመክፈቻው ፕሮግራም ላይ የሚዲያ ተቋማት በመገኘት ሽፋን እንዲሰጡም በመግለጫው ላይ ተገልጧል፡፡

