የንግድና ዘርፍ ማኅበራትና የንግዱ ማኀበረሠብ ያላቸውን ልምድና ተሞክሮ መለዋወጣቸው ያላቸውን ጥንካሬ ለማሥፋትና ለሀገራዊ የኢኮኖሚ ለውጥ ትልቅ ሚና እንዳለው የንግድና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስትሩ ዶክተር ካሣሁን ጎፌ ገለጹ።




የንግድና ዘርፍ ማኅበራትና የንግዱ ማኀበረሠብ ያላቸውን ልምድና ተሞክሮ መለዋወጣቸው ያላቸውን ጥንካሬ ለማሥፋትና ለሀገራዊ የኢኮኖሚ ለውጥ ትልቅ ሚና እንዳለው የንግድና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስትሩ ዶክተር ካሣሁን ጎፌ ገለጹ።
ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በሸገር ከተማ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት አዘጋጅነት በተካሄደው 13ኛው ኦሮሚያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የልምድ ልውውጥ መድረክ በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው።
በመድረኩ ከመላው የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት ተወካዮች እና የንግዱ ማኀበረሠብ የተገኙ ሲሆን ይህም ሊበረታታ የሚገባው መሆኑን ጠቅሠዋል ሚኒሥትሩ።
ንግድ ድንበር ተሻጋሪ ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እንዲኖር ትልቁ መሣሪያ ነው ያሉት ዶክተር ካሣሁን ጎፌ ለዚህም እንደ አፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ሥምምነት ትግበራ ካሉ አሠራሮች ተጠቃሚ ለመሆን የግሉ ዘርፍ ሚና የማይተካ ነው ብለዋል።
የግሉ ዘርፍ ኢኮኖሚው ላይ ሚናውን እንዳይጫዎት የሚይዙ ችግሮችን ለመቅረፍ መንግሥት የፖሊሢ እና የህግ ማሻሻያ ሥራዎችን መሥራቱንም አብራርተዋል።



የጅምላ እና የችርቻሮ እንዲሁም ሌሎች የኢንቨሥትመንት አማራጮች ለውጭ አካላት ክፍት የተደረጉት የውጭ ተሞክሮን ለማላመድና ተጠቃሚነት መሆኑንም ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የልምድ ልውውጥ መድረኩ ከክልል አልፎ በሀገር አቀፍ ደረጃ እውቀት እና ልምድን ለማሥፋት እና ብፕትብብር ለመሥራት እንደ ተሞክሮ የሚወሠድና ትልቅ አሥተዋጽኦ እንዳለው የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት ፕራዚዳንት እና የኦሮሚያ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት አቶ ሰብስብ አባፊራ አባጆቢር ገልጸዋል።
13ኛው የኦሮሚያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የልምድ ልውውጥ መድረክም ላለፉት ዓመታት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለማሥወገድ እና የንግዱ ማኀበረሠብ በኦኮኖሚው ውሥጥ ያለውን አበርክቶ ለማሣደግ ሲካሄድ መቆየቱን ፕሬዚዳንቱ አንሥተዋል።
ለዝግጅቱ መሣካት አሥተዋጽኦ ያደረጉ አካላትን ያመሠገኑት አቶ ሰብስብ አባፊራ በቀጣይም ማኀበራት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በጋራ መሥራትእንዳለባቸው መልእክታቸውን አሥተላልፈዋል።
የሸገር ከተማ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት እና የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት የቦርድ አባል መጋቢ ሥርዓት ቀሲስ ታየ ለታ በበኩላቸው ይህ የልምድ ልውውጥ መድረክ ጠንካራ አሠራሮችና ልምዶች እንዲጠናክር እንዲሁም የሚያጋጥሙ እንቅፋቶችን ለመቅረፍ እና የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ውሥጥ የመሪነት ሚናውን እንዲወጣ የሚያሥችል መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህ የልምድ ልውውጥ መድረክ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገራት አምባሣደሮች፣ የክልል የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት የቦርድ አባላት እና ተወካዮች እንዲሁም የግሉ ዘርፍ ተወካዮች ታድመዋል።





