የንግድ (ቢዝነስ) ፎረም ማለት የንግድ እና ኢንቨስትመንት እድሎችን ለማሰስ የሚገናኙበት መድረክ ነው።

የንግድ (ቢዝነስ) ፎረም ማለት የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች፣ ባለሀብቶች፣ የንግድ ምክር ቤቶች እና የልማት አጋሮች ሀሳቦችን ለመለዋወጥ እንደዚሁም ያሉትን የንግድ እና ኢንቨስትመንት እድሎችን ለማሰስ የሚገናኙበት መድረክ ነው።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እየሰራ ካላቸዉ አቢይ ተግባራት አንዱ በሀገራችን ንግድ እና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ እና የሀገራችን ምርቶች እና አገልግሎቶች በአለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቁና ተፈላጊ እንዲሆኑ በማድረግ የግሉ ዘርፍን እና የሀገራችንን ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ነዉ፡፡
በክቡር አቶ ሰብስብ አባፊራ አባጆቢር ፕሬዚዳንትነት እና በዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ ዋና ጸሀፊነት እየተመራ ያለዉ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የተቋቋመለትን አላማ እና የመንግስት የልማት አቅጣጫን መሰረት በማድረግ ከምንጊዜዉም በላይ በዉጭ ሀገር በሚዘጋጁ የቢዝነስ ፎረሞች እና የንግድ ትርኢቶች ላይ የሀገራችን ባለሀብቶች እንዲሳተፉ እና ምርት እና አገልግሎታቸዉን በአለም አቀፍ መድረኮች እንዲያስተዋዉቁ እና በስፋት ወደ አለም ገበያ እንዲቀላቀሉ በትጋት እየሰራ ይገኛል፡፡
በሌላ በኩልም በሀገር ዉስጥ ከተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ማለትም ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ከኢንቨትመንት ኮሚሽን፣ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከማዕድን ሚኒስቴር እና ከሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ጋር በመተባበር የቢዝነስ ፎረሞችን በማዘጋጀት፤ የተለያዩ የዉጭ ሀገራት ባለሀብቶች እና የሀገር ዉስጥ ባለሀብቶች በመድረኩ እንዲሳተፉ በማድረግ ኢትዮጵያ ያላትን የንግድ እና የኢንቨስትመንት እድሎችን እንዲገነዘቡ እና በተለይም የዉጭ ሀገራት ኩባኒያዎች በሀገራችን የኢንቨስትመንት እድሎች እንዲሳቡ እየተሰራ ይገኛል፡፡


እንደዚሁም የሀገራችን ባለሀብቶች እና ኩባኒያዎች መድረኩን በመጠቀም ምርት እና አገልግሎታቸዉን እንዲያስተዋዉቁ እና ያለምንም የገንዘብ ወጪ እና የጊዜ ብክነት ከዉጭ ኩባኒያዎች ጋር የንግድ ለንግድ ዉይይት እንዲያደርጉና ለምርቶቻቸዉ ገበያ እንዲያፈላልጉ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ለአብነትም በ2018 ዓ.ም የበጀት አመት እስከ ታህሳስ ወር መግቢያ ብቻ በአዲስ አበባ ዉስጥ ከ10 ሀገራት ጋር የቢዝነስ ፎረሞችን አካሂደናል፡፡ እነዚህም፦
1. ኮሎምቢያ
2. ቻይና
3. ፓኪስታን
4. አዛርባጃን
5.ተርኪዬ
6.ማሌዢያ
7.ስዊዲን
8. ሳዉዲ አረቢያ
9. ህንድ
10. ደቡብ ኮሪያ ናቸዉ፡፡
ከነዚህ ዉስጥም ከፓኪስታን የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት እና ከህንድ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች ፌዴሬሽን ጋር በቀጣይነት በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመናል፡፡

የሀገራችን የንግድ ማህበረሰቦች በየደረጃው በሚገኙ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የግሉ ዘርፍ ድምጽ ሆኖ ከምንጊዜዉም በላይ ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን በመገንዘብ አባል ያልሆናችሁ አባል በመሆን ተቋማችሁን እንዲታጠናክሩ፣ ባሉ የንግድና የኢንቨስትመንት እድሎች እንዲትጠቀሙ፣ በሚዘጋጁ የቢዝነስ ፎረሞች እና የንግድ ትርኢቶች በንቃት በመሳተፍ ምርትና አገልግሎታችሁን በማስተዋወቅ ተጠቃሚ እንድትሆኑ እንላለን፡፡

