በዓለም አቀፍ የጎብኚዎች የአመራር ፕሮግራም (International Visitor Leadership Program – IVLP 2026) ላይ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ ነው።

በአሜሪካ መንግሥት በሚዘጋጀውና ዓለም አቀፍ ውይይት፣ ሙያዊ ትስስር፣ የእውቀት ልውውጥና የጋራ መግባባት ጠቃሚ መድረክ በሚፈጥረው ዓለም አቀፍ የጎብኚዎች የአመራር ፕሮግራም (International Visitor Leadership Program – IVLP 2026) ላይ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ ነው።
በዚህ ዓለም አቀፍ መርሐ ግብር በአሜሪካ ከሚገኙ መንግሥታዊ ተቋማት፣ ንግድ ድርጅቶች ፣ ሙያዊ ማኅበራትና ከሌሎች ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ጋር የልምድ ልውውጥ እና የአቻ ለአቻ ውይይቶች እየተካሄዱ ነው።
በተጨማሪም በአመራር፣ በተቋማት አስተዳደር፣ በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲሁም ወቅታዊ የልማት ተግዳሮቶችን ለመፍታት በሚያግዙ አዳዲስ አሰራሮች ላይ ውይይቶች እየተካሄዱ ነው።


ከዚህ ጋር ተያይዞም፤ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ ፤ በአሜሪካ-ከኢትዮጵያና ኤርትራ ማኅበረሰብ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት እንዲሁም በዳላስ፣ ቴክሳስ ከሚገኘው የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤት ተወካዮች ጋር በኢትዮጵያና በአሜሪካ የንግድ ማኅበረሰብ መካከል ያለውን የንግድና የኢንቨስትመንት ትስስር ለማጠናከር በሚያስችሉ ቁልፍ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።
በዚህ ንግድና ኢንቨስትመንት ነክ ውይይት፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የግሉን ዘርፍ ትብብር ማሳደግ፣ የንግድ ግንኙነቶችን ማጠናከር እና አዳዲስ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን መለየት ላይ ትኩረት የደረገ ነው።
በዋንኛነትም ፤ የንግድ-ለንግድ (B2B) መድረኮች፣ የንግድ ትርኢቶች፣ የኢንቨስትመንት ማስተዋወቂያ መርሐ ግብሮችን እና የንግድ ትስስር መድረኮችን በትብብር እና በጋራ ማዘጋጀት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
በተጨማሪም በትምህርት ተቋማት መካከል ያለውን ትስስር በማጠናከር፣ በሁለቱ አገራት መካከል የእውቀት ልውውጥን ማሳደግ፣ የክህሎት ልማትን ማበረታታት እና ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያግዝ የሰው ኃይል አቅም ግንባታን ለማጠናከር ሊደረጉ በሚችሉ የትብብር ስራዎች ላይም ተወያይተዋል።
በውይይት መድረኩም ፤ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፤ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን በመጠቀም የንግድና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለማስፋት፣ የግሉን ዘርፍ ትስስር ለማጠናከር እና የቢዝነስ ፖሊሲ ምርምር እና አድቮኬሲ ስራዎችን ለማጠናከር ከምክር ቤቶቹ ጋር በትብብር ለመስራት ያለውን ፍላጎት ገልፆል።
ውይይቱ በተጨማሪም ፤ በኢትዮጵያ ያሉ የንግድ ተቋማትን በቴክሳስ ከሚገኘው ሰፊው የኢትዮጵያና የኤርትራ የንግድ ማኅበረሰብ ጋር ለማገናኘት መሰረቶችን እንደሚጥል ይጠበቃል።
በቀጣይ ቀናት በሚኖር ቆይታም በአሜሪካ ከሚገኙ የተለያዩ መንግሥት ተቋማት፣ ኩባንያ ኃላፊዎች፣ ከኢንቨስተሮችና ከሌሎች ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶች የሚካሄዱ ሲሆን፤ የኢትዮጵያን የግሉ ዘርፍ የንግድና የኢንቨስትመንት እድሎች የበለጠ ለማስተዋወቅ፣ አዳዲስ የትብብር አቅጣጫዎችን ለመለየትና ዘላቂ የንግድ ትስስሮችን በመፍጠር ረገድ ጠቃሚ ዕድል የሚፈጥሩ ይሆናል።

