ለምክር ቤታችን የዳይሬክተሮች ቦርድ እንዲሁም ለአባል ምክር ቤቶች አመራሮች ስልጠና አስጀምርያለው- የተከበሩ ሰብስብ አባፊራ

ለምክር ቤታችን የዳይሬክተሮች ቦርድ እንዲሁም ለአባል ምክር ቤቶች አመራሮች በቢሾፍቱ ከተማ የአቅም ግንባታ ስልጠና አስጀምርያለው ።
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፤ የንግድና ኢንዱስትሪ ተቋማት ፍላጎትና ጥቅም ለማስጠበቅ፣ ምቹ የንግድ አካባቢ እንዲፈጠር መስራት፣ የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚያዊ ዕድገት ውስጥ ያለውን ሚና ለማጠናከርና የአባል ምክር ቤቶቻችንን ተቋማዊ አቅም ለማሳደግ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል ። የግሉ ዘርፍ በሀገራዊ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖረው ሚና ከንግድና ከትርፍ ፈጠራ በላይ ነው።
ዘርፉ የስራ ዕድል በመፍጠር፣ ኢንቨስትመንትን በማበረታታት፣ የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ፣ የወጪ ንግድን በማስፋፋት፣ ቴክኖሎጂንና ፈጠራን በመጠቀም እንዲሁም የዜጎችን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል ረገድ ሚናው ከፍ ያለ ነው።
ምክር ቤታችን አባል ምክር ቤቶችን በማቀናጀት፣ የግሉ ዘርፍ የጋራ ጥቅምን በማስጠበቅ፣ ከመንግሥትና ከሌሎች ተቋማት ጋር ያለውን ውይይት በማጠናከር እና ለአባላቱ የተሻሉ የንግድ ዕድሎችን በመፍጠር ያለውን ሚና በተሻለ ደረጃ ለመወጣት ተቋማዊ ብቃቱን ማሳደግ አለበት። የምክር ቤቱ ውስጣዊ አሰራር ውጤታማ ሲሆን በአባላቱ አገልግሎት ላይ ይንጸባረቃል፤ የአባላቱ አቅም ሲጠናከር ደግሞ የግሉ ዘርፍ አጠቃላይ አቅም ይጨምራል።
በዚህ ረገድ ከካይዘን የልህቀት ማዕከል ጋር የጀመርነው አጋርነት ለአነስተኛ፣ ለመካከለኛና ለትላልቅ የንግድ ተቋማት የአቅም ግንባታ፣ የስልጠናና የምክር አገልግሎቶችን ለማስፋፋት ጠቃሚ መሠረት ይፈጥራል።
በመጨረሻም፤ ይህንን ጠቃሚ አጋርነት ለማስጀመርና ለማጠናከር ለምታደርጉት ትብብር ለካይዘን የልህቀት ማዕከል እና ለJICA ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
የተከበሩ ሰብስብ አባፊራ አባጆቢር
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት

