የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ማሥተባበሪያ ክፍል ለክህሎት መሻሻልና ለሥራ ፈጠራ የላቀ ፋይዳ ይኖረዋል፡- ዶክተር ተሻለ በሬቻ

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በመተባበር የተቋቋመው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ማሥተባበሪያ ክፍል በይፋ ስራ ጀመረ፡፡
የማስተባበሪያ ክፍሉ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እንዲሁም ከጅአይዜድ (GIZ) ጋር በመተባበር የተቋቋመው ነው፡፡
ማስተባበሪያ ክፍሉ በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት ዋና መስሪያ ቤት ስራውን በጀመረበት ፕሮግራም ላይ የተገኙት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሻለ በሬቻ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው የክህሎት ማሣደግና የሥራ ፈጠራ በትኩረት የሚሠራባቸው መስች መሆኑንና አዲስ የተቋቋመው ክፍልም ለዚህ ትልቅ አጋጣሚ መሆኑን አንስተዋል። የመንግሥትና የግል ትብብር እጅግ አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ተሻለ በሬቻ፣ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት የቦርድ አባላት፣ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳዊት ሞገስ፣ የጂአይዜድ GIZ) STEP ማናጀር ሞሀመድ አሊ ካሃንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።


የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ ( ተባባሪ ፕሮፌሠር) ማስተባበሪያ ክፍሉ በኢንዱስትሪውና በሥልጠና ተቋማት መካከል ያለውን የሠለጠነ የሠው ኃይል ፍላጎትና አቅርቦት የተሻለ፣ በፍላጎት ላይ የተመሠረተና ውጤታማ እንዲሆን ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የጂአይዜድ GIZ) STEP ማናጀር ሞሀመድ አሊ ካሃን በበኩላቸው በቴክኖክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ውጤት ለማምጣት የግሉ ዘርፍ ተሣትፎ በእጅጉ አሥፈላጊና ሊተካ የማይችል መሆኑን ገልጸው አሁን የተከፈተው የማሥተባበሪያ ክፍል ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

በቀጣይም ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን ሰለጠነና አስፈላጊውን ክህሎት ያለው የሰው ኃብት ለማፍራት ለሚደረገው ጥረት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከምክር ቤቱ እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በትኩረት እንደሚሰራም በፕሮግራሙ በተካሄደው ውይይት ላይ ተነስቷል፡፡

