የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ከኦሮሚያ ቡና ገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ጋር ተወያየ


የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ከኦሮሚያ ቡና ገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ጋር አብሮ መስራት በሚያስችሏቸው የጋራ ጉዳዮች ላይ ተወያየ፥ በምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) የተመራው የማኔጅመንት ቡድን ከህበረት ስራ ዩኒየኑ የማኔጅመንት አባላት ጋር በተለይም በአቅም ግንባታ ስራዎች ላይ ያተኮረ ሰፊ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ፤ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ተግባራዊ ባደረገው የለውጥ ስራ ለንግዱ ማህበረሰብ ከሚጠብቀው አለም አቀፍ ብርቱ ፉክክርና በአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ሊኖረው ከሚገባው አበርክቶ አንፃር ሊያዘጋጀው በሚችል መልኩ አቅሙን ለመገንባት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ዶ/ር ቀነኒሳ አስርድተዋል። አሁን አገራችን የአለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ጫፍ ላይ በደረሰችበት ወቅት እና የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና እንዲሁም የብሪክስ አባል በሆነችበት የአገራችን የንግዱ ማህበረሰብ ለሚጠብቀው ብርቱ ፉክክር እራሱን ማዘጋጀት አለበት ያሉት ዋና ፀሐፊው፤ ለዚህ ደግሞ ቢዚነሶች በቴክኖሎጂ ላይ ብቻ ኢንቨስት ማድረግ ብቻውን ተወዳዳሪ ለመሆን ስለማያስችል ቴክኖሎጂውን ተጠቅሞ ብቁ ተወዳዳሪ ሊያደርጋቸው በሚችል የሰው ኃይልም ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው አስረድተዋል። ለዚህ ደግም የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት የስራ አመራር አካዳሚ ወቅቱን የዋጁ ስልጠናዎችን ስለሚሰጥ በዚህ ዕድል እንዲጠቀሙም አሳስበዋል።



የኦሮሚያ ቡና ገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ደጀኔ ዳዲ በበኩላቸው ዩኒየኑ ከግማሽ ሚሊዮን አባላት በላይ ባላቸው 413 መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት የተደራጀና በአፍሪካ ትልቁ ዩኒየን እንዲሁም አለምአቀፍ ዕውቅና ያለው መሆኑን አንስተው፤ አሁን በአለም አቀፍ ደረጃ በስፔሻሊቲና ፕሪሚየም የቡና ሽያጭ ያለውን ተደራሽነትና ተወዳዳሪነቱን አጠናክሮ ይዞ ለመቀጠል የአቅም ግንባታ እጅጉን እንደሚያስፈልገው ገልፀዋል። ም/ቤቱ ዩኒየናችን አዲስ የለውጥ ጎዳና በጀመረበት ይህንን ሀሳብ ይዞ በመምጣቱ ደስተኛ ነው ያሉት አቶ ደጀኔ በተመቻቸልን ዕድል ለመጠቀም ዝግጁ ነንም ብለዋ።
የኦሮሚያ ቡና ገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን በአሜሪካና በአውሮፓ እንዲሁም በአውስተራሊያ ያለውን የገበያ ተደራሽነት በአፍሪካ ውስጥ የለውም ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ፤የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ከአቻ የአፍሪካ ንግድ ም/ቤቶች ጋር በመነጋገር የገበያ ተደራሽነቱን እንዲያሰፋም ጠይቀዋል።


