የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምርምርንና የፈጠራ ውጤቶችን ወደ ዘላቂ አገራዊ የኢኮኖሚ ልማት በመለወጥ ላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ ገለጹ።


የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፤ በአምራች ኢንዱስትሪውና በአካዳሚክ ተቋማት መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ዕውቀትን፣ ምርምርንና የፈጠራ ውጤቶችን ወደ ዘላቂ አገራዊ የኢኮኖሚ ልማት በመለወጥ ላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ ገለጹ።
ዶ/ር ቀነኒሳ በአሜሪካ ቴክሳስ ግዛት ከሚገኘው በዳላስ- ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቴክሳስ (UTD) የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰርና የዘላቂ ዓለም አቀፍ ንግድ ኢኒሼቲቭ ዳይሬክተር ከሆኑት ዶ/ር ሀብቴ ወልዱ እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና የፋኩልቲ አባላት ጋር ተገናኝተው በጉዳዩ ዙሪያ በምክር ቤቱ በኩል እየተከናወኑ ስላሉ ስራዎች ፍሬያማ ውይይት አካሂደዋል።

በውይይቱም፤ የግሉ ዘርፍ እና የአካዳሚክ ተቋማት ብሎም የአመራር ሚና ለዘላቂ ልማት ስራዎች ያላቸው አስተዋጽኦ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና በዳላስ -ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቴክሳስ መካከል የትስስር ዕድሎችን ለመፍጠር የሚቻልባቸው ጉዳዮች ተዳስሰዋል።
የአካዳሚክ ተቋማት የሚያመነጩትን ዕውቀትና የምርምር ውጤቶች ወደ ተግባራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ለመቀየር በግሉ ዘርፍና በትምህርት ተቋማት መካከል ጠንካራ ትስስር መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ዶ/ር ቀነኒሳ፦
በዚህ ረገድ፤ በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፤ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና (TVT)–ኢንዱስትሪ ትስስር ክፍል መቋቋሙ፣ በትምህርት ተቋማትና በንግዱ ማኅበረሰብ መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር ምክር ቤቱ እያደረገ ላለው ተግባራዊ ጥረት ማሳያ ነው ብለዋል።
በውይይቱ ማጠቃለያም ፤ በቀጣይ ተግባራዊ የሚደረጉ የትብብር መስኮችን ለመለየት፣ የዕውቀት ልውውጥን ለማሳደግና በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና በዳላስ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቴክሳስ መካከል ዘላቂ ተቋማዊ አጋርነት ለመፍጠር ከስምምነት ተደርሷል።
ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ በአሜሪካ መንግሥት በሚዘጋጀው የ2026 ዓ.ም. ዓለም አቀፍ የጎብኚዎች የአመራር ፕሮግራም (International Visitor Leadership Program – IVLP) ላይ በመሳተፍ ላይ መሆናቸው ይታወቃል።

