የካናዳ ኤምባሲ ልዑክ ቡድን ከሲዳማ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር ውይይት አካሄደ!

የካናዳ ኤምባሲ ልዑክ ቡድን ከሲዳማ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር ውይይት አካሄደ!
በመድረኩ ላይ የሲዳማ እና የሀዋሳ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ቦርድ አመራሮች እንዲሁም የካናዳ ኤምባሲ አምባሳደር ክቡር ኒኮላስ ሲማርድ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሲዳማ ክልል የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ አቶ ደመቀ ደፋሮ፤ የተከበሩ አምባሳደሩን እና እንግዶችን ወደ ለምለምቷ ሲዳማ ሀዋሳ በሰላም መጣችሁ በማለት ሞቅ ያለ አቀባበል አድርገዋል።
በንግግራቸውም የክልሉን የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝም አቅሞች እንዲሁም በግብርናው ዘርፍ በተለይም ቡና እና አቮካዶን ወደ ውጭ በመላክ ሂደት ላይ ያተኮሩ ሰፊ የገበያ ትስስር ነጥቦችን አንስተዋል።

በመቀጠልም የሀዋሳ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር መስፍን ዳኜ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት በማስተላለፍ፤ የሲዳማ ክልል ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ አጉልተው አሳይተዋል። ሀዋሳ ከተማ ከሀገራችን ሁለተኛው የቱሪስት መዳረሻ መሆኗን ጠቅሰው፣ ኤምባሲው የግሉን ዘርፍ አቅም ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በንግድ ለንግድ (B2B) ትስስር ላይ ድጋፍ እንዲያደርግ አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት ዶ/ር ጎበና በሪሄ በበኩላቸው፤ የሲዳማ ባለሀብቶች ከካናዳ ባለሀብቶች ጋር በቀጥታ የሚገናኙበትን እና የንግድ አጋርነት የሚፈጥሩበትን ሁኔታ አስመልክቶ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የተከበሩ አምባሳደሩ ኒኮላስ ሲማርድ በተነሱት ሀሳቦች ላይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ በቀጣይ ከክልሉ የንግድ ምክር ቤት ጋር በቅርበት በመቀናጀት በተለይ በቡና ላኪነት፣ በአቮካዶ ዘይት ልማት እና የግሉን ዘርፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ በሚያስችሉ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ላይ በጋራ ለመስራት ቃል ገብተዋል።
በመጨረሻም ዋና ፀሐፊ አቶ ደመቀ ደፋሮ ለክቡር ለአምባሳደሩ እና ለልዑካ ቡድናቸው ልባዊ ምስጋና በማቅረብ፣ በውብቷ ሲዳማ ሀዋሳ የሚኖራቸው ቆይታ ማራኪ እና ስኬታማ እንዲሆን በተቋሙ ስም ምኞታቸውን ገልጸዋል።(ሲዳማ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት)

