ለተሻለ የኢኮኖሚ ለውጥ መንግሥትና የግሉ ዘርፍ ይተባበሩ- ም/ጠቅላይ ሚኒሥትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ
የተሻለ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ለውጥ ለማምጣት መንግሥትና የግሉ ዘርፍ ተባብረው መሥራት እንዳለባቸው የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒሥትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።
በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ትብብር የተዘጋጀው 4ኛው የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒሥትሩ አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒሥትር ዶክተር ካሣሁን ጎፌ፣ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት አቶ ሰብስብ አባፊራ፣ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ሥምምነት ሴክሬታሪያት ዋና ጸሐፊ ዋምኬሌ ሜኔ፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የግሉ ዘርፍ ተወካዮች፣ በኢኮኖሚው ውስጥ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ተሸላሚ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት፣ የኤምባሲ ተወካዮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡
መንግሥት ሀገራዊ የኢኮኖሚ ለውጥ ለማምጣት በርካታ የሪፎርም ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመሥገን ጥሩነህ የግሉ ዘርፍ ያለው ድርሻ የላቀ እንዲሆን አሥፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግና በጋራ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የወጭ ምርቶች ማሳያ ማዕከል መገንባቱ እንዲሁም ለግሉ ዘርፍ እውቅና መሰጠቱና ትኩረት መደረጉ የሚበረታታ መሆኑን ያሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚው መሪና እንቀሣቃሽ እንዲሆን በተለይም የፋይናንሥ ዘርፉ እንዲያድግ bመንግሥት በኩል የለውጥ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል።
የወጭ፣ የገቢ፣ የችርቻሮና ጅምላ ንግድ ሥራዎች ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት በመሆናቸው ውጤት መመዝገቡን አንስተው የንግድ ሥርአቱ ቀልጣፋ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑንና የገቢ ምርት መተካትና የውጭ ንግድ ተወዳዳሪ እንዲሆንም ዋነኛው የትኩረት ነጥብ መሆኑን አንስተዋል።
በዓመቱ 3.8 ቢሊየን ብር የወጭ ንግድ ገቢ ተገኝቷል ሲሉ በስኬት ያነሱት አቶ ተመስገን ምርትና ምርታማነትን ለማሣደግና ገቢን ከፍ ለማድረግ ላኪዎችን በሥነ ምግባር በመታነጽ በርትተው እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡
ከፍተኛ ምርት የገዙና እውቅና የተሰጣቸው ሀገራት ይመሠገናሉ ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን በመተግበር ላይ ያለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትልቅ ለውጥ ማምጣቱን ጠቁመው ሁሉም የንግዱ ማህበረሠብ በውድድር ላይ የተመሠረት ሥራ እንዲሰራ አስገንዝበዋል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዶክተር ካሳሁን ጎፌ በበኩላቸው የምክክር መድረኩ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት በአዋጅ በተሰጡት ኃላፊነቶች እንዲሁም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና በምክር ቤቱ መካከል በተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት መሰረት የተዘጋጀና ለግሉ ዘርፍም ሆነ ለመንግስት አስፈላጊ ምክክር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የምክክር መድረኩ የተለያዩ አካላት ሀሣብ እንዲለወጡና የወል አሸናፊነት እንዲኖር ለማድረግ የሚያስችል ሲሆን መንግሥትና የግሉ ዘርፍ የሚያጋጥሙ ችግሮች ላይ ለመነጋገርና ለመፍታት ትልቅ መሳሪያ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
አዳዲሥ የመፍትሄ ሀሳቦችን ለመፈለግና ለመተግበር፤ በሚለካ እና የትብብር መንፈሥ ያለበት እንዲሁም መንግሥት ለግሉ ዘርፍ ሥራ አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚያግዘው አብራርተዋል፡፡
ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍ የተወሠዱ የመፍትሄ እርምጃዎች፣ ለላኪዎች የተሻለ ትርፍ እንዲያገኙ እያደረገ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የአፍሪካን ገበያ ለመጠቀምም በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ያሉ እድሎችን መጠቀም ላይ በትኩረት ትሠራለች ነው ያሉት።
በነዳጅ ዲጂታል ግብይትና ኦንላይን ንግድ አገልግሎት አሰራር የተሻለ ሥራ ስለመሰራቱ የገለጹት ዶክተር ካሳሁን የወጭና ገቢ ንግድን ለማሣለጥ አበረታች ተግባራት መከናወናቸውንም አብራርተዋል፡፡
የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዘርፍ የተቋቋመበት ዋና ዓላማም የግሉን ዘርፍ ከመንግሥት ጋር ማገናኘት፣ ማወያየትና የግሉን ዘርፍ ማነሣሣት ነው ያሉት ሚኒስትሩ ዶክተር ካሳሁን ጎፌ መንግሥትም የተሻለ የአሠራር ሥርአት ለመዘርጋት ይሰራል ብለዋል፡፡
ከተራው ይልቅ ያልተሠራው፣ ካሣካነው ይልቅ ያላሣካነው ብዙ ነውና እሡን ለማስተካከል በጋራ መትጋት አለብን ያሉት ዶክተር ካሳሁን ለሽልማት የበቁትን ላኪዎችና አሥመጭዎች፣ ቅዳሜና እሁድ ገበያዎች፣ ቀዳሚ ምርት የገዙ ሀገራትና ሌሎችም ተሸላሚዎችን አመስግነዋል፡፡የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት አቶ ሰብስብ አባፊራ በበኩላቸው ምክር ቤቱ ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ እና የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚውን የመሪነት ሚና በአግባቡ እንዲወጣ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የምክክር መድረኩም በግሉ ዘርፍ ነባራዊ ሁኔታ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲሁም በማክሮ ኢኮኖሚው የለውጥ ሂደት የግሉ ዘርፍ የሚጠበቅበትን እንዳያበረክት እንቅፋት የሆኑ ተግዳሮቶችን በማንሳት መፍትሄ ለማበጀት የላቀ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡ምክር ቤቱ በቀጣይም በግ ዘርፍና መንግስት ተቀራርበው እንዲሰሩና ለሚያጋጥሙ ችግሮች አፋጣኝ መፍትሄ እንዲያገኙ ለማድረግ የግሉ ዘርፍ ድምጽነቱን በማጉላት እንደሚሰራም በመድረኩ ጠቁመዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ሴክሬታሪያት ዋና ጸሐፊ ዋምኬሌ ሜኔ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ላይ ያሉ አጋጣሚዎችን ለመጠቀም የተሻለ እድል እንዳላት አንስተዋል፡፡
በተለይም የምስራቅ አፍሪካን አካባቢ ገበያ መጠቀም እንደምትችል ያነሱት ዋና ጸሐፊው ዋምኬሌ ሜኔ በአፍሪካ ግዙፍ የሆነውን አየር መንገድ የያዘችው ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ አፍሪካን በማስተሳሰርም ትልቅ ሚና እንደምትጫዎት ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በቀጣይ ዓመት ከ6 በመቶ በላይ እንደሚያድግ የጠቀሱት ዋና ጸሐፊው ሀገሪቱ በአፍሪካ ያላት የንግድ ድርሻ 9.1 በመቶ እንደነበርና ይህም በእጥፍ ማደጉን አንስተዋል፡፡የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በየጊዜው በመፍታት በአፍሪካ ያለውን የንግድ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ከኢትዮጵያ ጋር እንደሚሰራ በመድረኩ ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ ላይም ከግሉ ዘርፍ ተወካዮች በኢኮኖሚ ላይ ባሉ ወቅታዊ የጸጥታ መጓደል፣ የወጭና ገቢ ንግድ አሰራር፣ ከመሬት አቅርቦት፣ ከኃይል አቅርቦት፣ ከብልሹ አሰራር፣ ከፋይናንስ አቅርቦት፣ ከድጋፍ አሰጣጥ፣ ከመሰረተ ልማት አቅርቦትና ከመሳሰሉት ጋር የተያያዙ ችግሮች ተነስተው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ተመስን ጥሩነህ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

