14ኛው የኢትዮ- ቻምበር ዓለም አቀፍ ንግድ ትርዒት ከመጋቢት 4-8 ቀን 2017 በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ይካሄዳል ፡፡
14ኛው የኢትዮ- ቻምበር ዓለም አቀፍ ንግድ ትርዒት ከመጋቢት 4-8 ቀን 2017 በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ይካሄዳል ፡፡
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከኢትዮጵያ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን ምርቶች፣ አገልግሎቶችና ግብዓቶች በማስተዋወቅ፣ ለአገራችን ኢንዱስትሪ ልማት እድገት፣ ለስራ ፈጠራ እና ለንግድ ስራ መስፋፋት የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎች የሚቀርቡበት እንዲሁም ብዛት ያላቸው የሀገር ዉስጥና የዉጭ ኩባንያዎች መካከል የገበያ ትስስር፣የእዉቀትና የልምድ ልዉዉጥ የሚደረግበት 14ኛዉ የኢትዮ-ቻምበር ዓለም ዓቀፍ የንግድ ትርዒት “የኢትዮጵያን ይግዙ” በሚል መሪ ቃል ከመጋቢት 4-8 ቀን 2017 በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ያካሂዳል፡፡
የንግድ ትርዒቱን አስመልክቶም ዛሬ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መግለጫ የተሠጠ ሲሆን ፤ በመግለጫው ላይም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ደኤታ ወ/ሮ ያስሚን ወሀብረቢ እና የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ፀኃፊ ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ( ተባባሪ ፕሮፌሰር ) ተግኝተዋል ።
በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ለአምስት ቀናት የሚቆየው ኤግዚቢሽን በዓለም ዓቀፍ የንግድ ተቋማት እና በአገር ውስጥ ኢንተርፕራይዞች ምርቶች እና አገልግሎቶች ይቀርባሉ እንዲሁም የአቻ ለአቻ የንግድ መድረክ ይካሄድበታል ፡፡
ከመላው አገሪቱ የተወጣጡ ኢንተርፕራይዞች ተሳታፊ የሚሆኑበት ይህ ኤግዚቢሽን እና ባዛር ከውጭ የሚመጡ የንግድ አካላት የሚሳተፉበት እንደመሆኑ ልምድ ለመለዋወጥ እና ትስስር ለመፍጠር ትልቅ ጠቀሜታ ያለው ነው፡፡
ይህ የአገር ውስጥ እና የውጪ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት የንግድ ትርዒት ሲከፈት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣የንግዱ ማሕበረሰብ፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ፡፡


