Apr 03, 2025 .
የንግድ ፖሊሲ ማጠቃለያ ግብአት ማሰባሰቢያ መድረክ እየተካሄደ ነው::

የንግድ ፖሊሲ ማጠቃለያ ግብአት ማሰባሰቢያ መድረክ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ 25/07/2017(ንቀትሚ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በረቂቅ የኢትዮጵያ ንግድ ፖሊሲ ላይ የማጠቃለያ ግብአት ማሰባሰቢያ መድረክ እያካሄደ ነው፡፡
በንግድ ዘርፉ የሚስተዋሉ መሰረታዊ ችግሮችን በመፍታት፣ ዘርፉን በማዘመን እና ተወዳዳሪ በማድረግ የላቀ ውጤት ለማምጣት ለሀገራችን የመጀመሪያ የሆነው የንግድ ፖሊሲ መዘጋጀቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
የፖሊሲው ረቂቅ ሲዘጋጅ ሀገራዊ ግብን፣ ነባራዊ ሁኔታንና ዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን መሰረት በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ በዝግጅት ሂደቱ ላይ የግሉ ዘርፍ፣ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች፣ የልማት አጋሮች እና የተለያዩ የክልልና የፌደራል ተቋማት ተወካዮች የተወያዩበት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ከፌደራል መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ በክልል እና በተለያየ ደረጃ ካሉ የመንግስትና የግል ባለድርሻ አካላት ጋር የመጨረሻ ግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ኃይሌ ግራንድ ሆቴል እየተካሄደ ይገኛል፡፡

