May 15, 2025 .
ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ከUN WOMEN ተወካዮች ጋር ተወያዩ፡፡



የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ከUN WOMEN ተወካዮች ጋር ተወያዩ፡፡
ሁለቱ አካላት በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በተለይም በሴቶች አቅም ግንባታና ሌሎች ጉዳዮች ላይ እንደሚሰሩ ተወያይተዋል፡፡
የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ ምክር ቤቱ ለሴቶች፣ ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች ልዩ ትኩረት በመስጠትና የስራ ክፍል በማቋቋም እየሰራ መሆኑን ለተወካዮቹ አብራርተውላቸዋል፡፡

የማኅበረሰቡ ግማሽ አካል የሆኑት ሴቶችን አቅም ከፍ ለማድረግ ምክር ቤቱ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት በመስጠት ከልማት አጋሮች እና ከመንግስት ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል ፡፡
የUN WOMEN የኢኮኖሚ አቅም ግምባታ (WEE) ፕሮግራም ኃላፊ ስመኝ ኩማ በበኩላቸው የሴቶችን አቅም ለማጎልበት በአቅም ግንባታ እና ግንዛቤ ማሻሻል፤ የሴቶችን ተሳትፎ በሚሹ የበጀት፣ የግዥ እና የኦዲት በመሳሰሉ ጉዳዮች፣ በአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ኢኮኖሚ ልማት እንዲሁም በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ ዙሪያ በጋራ መስራት እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡
ሁለቱ አካላት ከሌሎች የመንግስት ተቋማት ጋር በመተባበር የሚያዘጋጁት የሴቶች አቅም ግንባታ ላይ ያተኮረ ፎረም እንደሚካሄድም ተጠቁሟል፡፡




