ታማኝነቱ አጠራጣሪ በሆነበትና ክልከላና ጫና በበዛበት የአለም የገበያ ስርዓት በራስ ምርት የመጠቀም ስትራቴጂ መከተል አማራጭ ሳይሆን ግዴታ ነው:- ፕሬዚዳንት ታዬ


ታማኝነቱ አጠራጣሪ በሆነበትና ክልከላና ጫና በበዛበት የአለም የገበያ ስርዓት በራስ ምርት የመጠቀም ስትራቴጂ መከተል አማራጭ ሳይሆን ግዴታ ነው። ፕሬዚዳንት ታዬ አስቀስላሴ
አሁን በሚስተዋለው ታማኝነቱ አጠራጣሪ፣ክልከላና የታሪፍ ጫና በበዛበት የአለም የገበያ ስርዓት በራስ ምርት የመጠቀም ስትራቴጂ መከተል አማራጭ ሳይሆን ግዴታ መሆኑን ክቡር ፕሬዚዳንት ታዬ አስቀስላሴ አስታወቁ።
ክቡር ፕሬዚዳንቱ የኢትዮጵያን ምርት እንግዛ ስንል የእጣ ወይም የእድል ጉዳይ ሳይሆን ስትራቴጂያዊ ምርጫ ነው ያሉ ሲሆን ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት እና በተፅእኖ የሚመጣን የገበያ ሁከትን ለመቋቋም፣የስራ እድልን ለማበራከትና ማህበረሰባችን በራሱ እንዲተማመን የማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ሲሉ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያን ይግዙ መርህ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው ጉልህና በጎ ትሩፋት በመሸጥና በመግዛት ብሎም በማትረፍ የሚገኘው ገንዘብ በሀገራችን ገንዘብ ለማባዛትና ኢኮኖሚውን የማሳደግና የማደራጀት አቅም ይፈጥራል ያሉት ፕሬዚዳንቱ አሜሪካን ጨምሮ ብዙ አገሮች ዜጎች የሀገራቸውን ምርት እንዲሸምቱና እንዲጠቀሙ በህግ ሳይቀር እንደሚያስገድዱ አንስተዋል።
እንደ ፕሬዚዳንት ታዬ ገለፃ በሀገር ምርት ሽያጭ የተገኘ ትርፍ በማህበረሰቡ ዘንድ ሌላ ትርፍ ያስገኛል ያሉ ሲሆን በ100 ብር በሀገር ውስጥ የተመረተን ምርት መግዛት 100 ብር በአገር ኢኮኖሚ እድገት ላይ እንደሚያመጣ እርግጠኛ ነኝ ብለዋል።
የኢትዮጵያን ምርት መግዛት ሌላው ፋይዳው በማምረትና በመግዛት ክዋኔ ውስጥ ስራን መፍጠርና ማባዛት መቻሉ ሲሆን ይህም ለጤናማ የኢኮኖሚ እድገት መሠረት እንደሚጥል ፕሬዚዳንት ታዬ አስቀስላሴ ገልፀዋል። (ምንጭ ን/ቀ/ት/ሚ)

