የንግድ ምህዳሩን ምቹ የሚያደርጉ ተግባራት በዘላቂነት ተጠናክረው ይቀጥላሉ:- የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዶክተር ካሣሁን ጎፌ

የንግድ ምህዳሩን ምቹ የሚያደርጉ ተግባራት በዘላቂነት ተጠናክረው ይቀጥላሉ:- የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዶክተር ካሣሁን ጎፌ።
“የኢትዮጵያን ይግዙ” የንግድ ሳምንት ኤክስፖ 2017 በጀት ዓመት መገናኛ አካባቢ በሚገኘው የጥራት መንደር ውስጥ እየተካሄደ ሲሆን እስከ ነሐሴ 29 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ክፍት ሆኖ ይቆያል።
በዛሬው ዕለትም ከኤስፖው ጎን ለጎን የሀገር ውስጥ ንግድን ህጋዊነትና ተደራሽነት ከማረጋገጥ በተጓዳኝ ማዘመን ላይ ትኩረት ያደረገ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ የንግድ ምህዳሩን ለሸማቾች እና ንግዱ ማህበረሰብ ምቹ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
በዚህም የሸማች እና የንግዲ ማህበረሰብ እርካታ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ እያደገ መምጣቱን ጠቁመው፤ በቀጣይነትም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 3 ነጥብ 25 ሚሊዮን ተገልጋዮች የኦንላይን ንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት መሰጠቱን ተናግረዋል።
ለገበያ መሰረተ ልማት መስፋፋት ትኩረት መሰጠቱን የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ ገበያውን ለማረጋጋት ከፍ ያለ ፋይዳ ያላቸው በርካታ የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉንም አመልክተዋል።
ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ ከህግና ስርዓት ውጪ በሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች ላይም የሚወሰደው እርምጃ መቀጠሉን ተናግረዋል።
ለአብነትም በ2017 በጀት ዓመት 110 ሺህ ህገ ወጥ ድርጊት የፈጸሙ ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን በመጥቀስ።

የንግዱን ዘርፍ ምቹ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ መሰል የውይይት መድረክ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለይቶ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማመላከት የላቀ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።

የፓናል ውይይቱ በቀጣይ ሶስት ቀናትም በጥራት መሠረተ ልማት፣ በወጪ ንግድና በኢ-ኮሜርስ ንድፎችና ተግባራት ላይ አተኩሮ ይቀጥላል። (ምንጭ ን/ቀ/ት/ሚ)

