ቡና ከዘልማዳዊ አሰራር ተላቆ መካናይዝድ እና ዲጂታላይዝድ ማድረግ ላይ ትኩረት መደረግ አለበት:- አቶ አዲሱ አረጋ

ቡና ከዘልማዳዊ አሰራር ተላቆ መካናይዝድ እና ዲጂታላይዝድ ማድረግ ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት ክቡር ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡
ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረግን ቢሆንም የቡና መገኛ ከመሆናችን፣ ቡናን ለመላው አለም ከማስተዋወቅ እና ከማላመዳችን አንጻር ብዙ መራመድ ይጠበቅብናልም ብለዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትሩ ክቡር አቶ አዲሱ አረጋ በዛሬው እለት ከቡናው ማህበረሰብ ጋር ሰፋ ያለ ውይይት አድርገዋል፡፡ በመድረኩ ላይ ቡናን ዘመናዊ አድርጎ ከማልማት አንጻር ከፍተኛ ልምድ ያካበቱት ቀርጫንሼ ግሩፕ እና ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ተሞክሯቸውን በስፋት አቅርበዋል፡፡

የቡናና ሻይ ባለስልጣን ባዘጋጀው እና በስካይ ላይት በተደረገው የውይይት መድረክ ላይ ከ80 በላይ ቡና ላኪ ባለሀብቶች፣ የፌዴራል እና ክልል የቡናው ዘርፍ የስራ ሀላፊ እና ባለሙያዎች፣ የቡና ማህበራት የስራ ሀላፊዎች እና ሌሎች የዘርፉ ተዋናዮች ተሳትፈውበታል፡፡
መድረኩን በይፋ ሲከፍቱ ክቡር ሚኒስትሩ እንዳሉት መንግስት የግብርናውን ዘርፍ ለመደገፍ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ቁርጠኝነቱን እያሳየ መሆኑን እና በዚህም በባለፉት አምስት እና ስድስት አመታት ከፍተኛ ውጤቶች መመዝገባቸውን እና ከነዚህ የግብርና ውጤቶች መካከል ደግሞ ቡና አንዱ እንደመሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጠንም ሆነ በገቢ ከፍተኛ የሚባል ውጤት እየመጣ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከዛሬ 6 አመት በፊት እየተላከ የነበረው 200ሺ ቶን እና ገቢውም ከ500 እና 600ሺህ የዘለለ ያለመሆኑን ያስታወሱት ክቡር አቶ አዲሱ ዛሬ ላይ 2.56 ቢሊየን ላይ መድረሱን እና ይህም በመንግስት በተካሄዱ የተለያዩ የማሻሻያ ስራዎች፣ በወጡ አሰራሮች፣ ደንቦች እና መመሪያዎች ከአርሶ አደሩ ጀምሮ የዘርፉ ተዋናዮች ባደረጉት ርብርብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የምርምር ተቋማትም ምርታማነታቸውና ጥራታቸው የተረጋገጠ በሽታ መቋቀቋም የሚችሉ ዝርያዎች በማውጣት እና ለህብረተሰቡ በማከፋፈል ረገድ ቀላል የማይባል ስራ ሰሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቁመዋል፡፡
እነዚህ ሁሉ መልካም ቢሆኑም ግን የቡና መገኛ ከመሆናችን፣ ቡናን ለመላው አለም ከማስተዋወቅ እና ከማላመዳችን፣ በመላው አለም ተወዳጅ ቡና ያለን ከመሆኑ፣ ሰፊ መሬት፣ ምቹ የአየር ፀባይ፣ ብዙ ወጣት እና ሌላም ምቹ ሁኔታዎች አንጻር ብዙ ጥረት ማድረግ፣ ብዙ መራመድ ይጠበቅብናልም ብለዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ እንዳሉት ቡና ከዘልማዳዊ አሰራር ተላቆ መካናይዝድ እና ዲጂታላይዝድ ማድረግ ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በቅርቡ በጉጂ ዞን የሚገኘውን እና በቀርጫንሼ ግሩፕ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ እየለማ የሚገኘውን ሰፊ የቡና እርሻ መጎብኘታቸውን አስታውሰው አገራችን እና መላ ባለሀብቶች አይናቸውን ገልጠው አገራችንን ከድህነት ለማውጣት የሚያስችል መሰል ዘመናዊ አመራረት እና የአሰራር ዘዴን ተግባራዊ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተመሳሳይም እንደ ሚድሮክ ኦንቨስትመንት ግሩፕ የመሳሰሉ ትልልቅ ድርጅቶችም መሰል ተሞክሮ እንዳላቸው እንደሚያውቁም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡
ከክቡር ሚኒስትሩ መክፈቻ ንግግር በኋላ ክቡር አቶ ሻፊ አጠቃላይ የአገራችንን የቡና ሁኔታ፣ የመልማት አቅም፣ የግብይት አጠቃላይ ሁኔታ እና አዝማሚያ እንዲሁም ለኢንቨስትመንት ያለውን ምቹ ሁኔታ በተመለከተ ማብራሪ አቅርበዋል፡፡
ዶክተር እስራኤል ደገፋ በቀርጫንሼ ግሩፕ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ እየለማ የሚገኘውን ሰፊ የቡና እርሻ በተመለከተ ሰፊ ልምዳቸውን ያካፈሉ ሲሆን በተመሳሳይ አቶ ፈለቀ የሚድሮክ ኦንቨስትመንት ግሩፕን ተሞክሮ አቅርበው ሰፊ ውይይት ሲካሄድበት ውሏል፡፡

