በ2015 የተዘጋጀው የጥራት ፖሊሲ ምን ይላል?

የዘመነ ግሎባላይዜሽን የንግድ ማዕቀፍ ምርትና አገልግሎቶች በአቅርቦት ሰንሰለት ዉስጥ እንዲቆራኙ ምቹ ከባቢን ፈጥሯል።
ኢትዮጵያም በዚህ ዓለም አቀፋዊ የንግድ ትስስር ዕድገት ተጠቃሚ በመሆን በማህበራዊና በኢኮኖሚ ዘርፍ ልማትን
ማረጋጋጥ፣ ድህነትን መቀነስና በአካባቢ ላይ የሚደርስ ተጽዕኖን መቋቋም ይኖርባታል፡፡
በዚህም የተነሳ በአሁኑ ወቅት
የምርትና አገልግሎት ጥራትና ደህንነትን ማረጋገጥ የፖሊሲ አዉጪዎች ትኩረትን በከፍተኛ ሁኔታ በማግኘት ላይ ይገኛል፡፡
ስለሆነም የኢትዮጵያ አምራቾች፣ላኪዎች ወይም አቅራቢዎች በዚህ አለማቀፋዊ የንግድ ትስስር ሲገቡ የሚያጋጥማቸዉን ፈታኝ ሁኔታ በመረዳት መፍትሄ ማስቀመጥ ተገቢ ነዉ።
ለዚህ ምክንያት የሚሆነው በዓለም አቀፉ ገበያ በተለይም በወጪ ምርቶች መዳረሻ አገራት የሚገኘዉ ሸማች በመረጃ የዳበረና ንቃተ ህሊናዉ ከፍ ያለ ከመሆኑም ባሻገር በምርትና አገልግሎቶች ጥራትና ደህንነት ቁጥጥር የሚያደርጉ ተቋማት ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥጥራቸዉን እያጠበቁ ስለሚገኙ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም በአንድ ወገን የወጪ ምርት መዳረሻ ገበያዎች በአቅርቦት ሰንሰለት ዉስጥ ብዛት ያላቸዉን አገራት በማሳተፍ፣
አገልግሎቶችና ግብአቶች ጥራታቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ በአነስተኛ ዋጋ፣በተፈላጊ መጠን፣ በአስተማማኝ ሁኔታና
በዘላቂነት እንዲቀርቡላቸዉ ይፈልጋሉ።
በሌላ በኩል ላኪ ሃገራት ለተመሳሳይ የምርት መዳረሻ ገበያ ተመሳሳይ፣ ጥራቱና
ደህንነቱ የተረጋገጠ ብሎም የተቆጣጣሪ አካላትን መስፈርት ያሟላ ምርት፣ አገልግሎት ወይም ግብአት በማቅረብ በሂደቱ ብቸኛ ተጠቃሚ ለመሆን ዉድድሩንአጠናክረዉታል።
በአንጻሩ አብዛኛው የኢትዮጵያ ምርትና አገልግሎቶች ለብክነትና ብክለት የተጋለጡ፣ ጥራትና ደህንነታቸዉ ያልተጠበቀና ዋጋቸዉም ከፍተኛ በመሆኑ ወደ ኢንዱስትሪያላይዜሽን በሚደረገዉ መዋቅራዊ ሽግግር ላይ ተግዳሮት ሆኖ ቀጥሏል፡፡
በተጨማሪም በስፋት ገበያ ዉስጥ የተሰራጩና ጥቅም ላይ የዋሉ ምርትና አገልግሎቶች የምርት ዱካቸዉ በትክክል
የማይታወቅ ወይም በከፍተኛ ሁኔታ የጥራትና ደህንነት ችግር ያለባቸዉ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ለህብረተሰቡ ጤንነትና ደህንነት ጉልህ የስጋትና አደጋ መንስኤ ከመሆናቸዉም በላይ በአገራዊ ምርትና አገልግሎቶች ተወዳዳሪነት ላይ እንቅፋት መሆናቸዉ እሙን ነዉ፡፡
ስለሆነም አምራቹና አገልግሎት ሰጪዉም ሆነ አቅራቢዉ ቀጣይነቱ የተረጋገጠ፣ ፍላጎት መራሽ፣ ደንበኛ ተኮር፣ ምሉዕ፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን በመቋቋም አገልግሎቱን ማስቀጠል የሚችል፤ የመደገፍ፣
የማብቃትና ቁጥጥር ተልዕኮን ያነገበ እና የተሰናሰለ የጥራት መሰረተ ልማት ምህዳር ተግባራዊና ተደራሽ ማድረግ ዋነኛ የፖሊሲ
ስልት ነዉ፡፡
ይህ ማዕቀፍ ከተናበበ መዋቅራዊ አሰራርና የቴክኒክ ደንብ አፈፃፀም ጀምሮ፣ የደረጃ ዝግጅትና ትግበራ፣ሥነ ልክ፣ አክሪዲቴሽን፣ ተስማሚነት ምዘና፣የገበያ ክትትል፣የአቅም ግንባታ፣የግንዛቤ ማስጨበጫ፣የተግባቦት፣የስልጠና እና ትምህርት
ስራዎችን በማቀናጀት የጥራት ባህል ግንባታ እንዲያካትት ማድረግ ተገቢ ነዉ፡፡
ይህንን ሃገራዊና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታን በቅጡ በመረዳት መንግስት የጥራት መሰረተ ልማት ስትራቴጂ
ቀርፆ ወደ ተግባር የገባ ሲሆን አገልግሎቱን የሚሰጡ አካላት ማለትም የደረጃ፣ ሥነ ልክ፣ አክሪዲቴሽን እና ተስማሚነት ምዘና
ተቋማትን ቀዳሚ ትኩረት ሰጥቶ እያጠናከራቸዉ ይገኛል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የገቢና ወጪ ምርትን ጨምሮ ክትትሉንና ቁጥጥሩን ለማጠናከር ሴክተር ተኮር ተቆጣጣሪ አካላት በአዲስ መልክ ተጠናክረዉ ከመቋቋማቸዉም በላይ ሴክተሮችን የሚደግፉ የአቅም ግንባታና የምርምር ኢንስቲትዩቶች ከግሉ ሴክተር ጋር ተደጋግፈው ውጤታማ የሚሆኑበት ምህዳር
ፈጥሯል።
ከዚህ አንፃር በ2015 የተዘጋጀው የጥራት ፖሊሲ ምን ይላል። (በረቂቅ ደረጃ የነበረውን ይህንን ዶክመንት አያይዘናል።)
Read the full PDF file

