በአዳማ ከተማ ሲካሄድ የነበረዉ የኢትዮ ቻምበር የንግድና ኢንቨስትመንት ባዛር ተጠናቀቀ።



የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ያዘጋጀውና በአዳማ ከተማ ሲካሄድ የነበረዉ የኢትዮ ቻምበር የንግድና ኢንቨስትመንት ባዛር ተጠናቀቀ።
ዝግጅቱ በተለያዩ ምክንያቶች ቢዝነሶቻቸዉ የተቀዛቀዘባቸዉ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ለማነቃቃትና የገበያ ትስስር ለመፍጠር የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከአዳማ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትና ከከተማ አስተዳደሩ የስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው፡፡
ከመጋቢት 18-20/2018 ድረስ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የነበረዉ የኢትዮ ቻምበር የንግድና ኢንቨስትመንት ባዛር በዛሬዉ ዕለት ተጠናቋል።


በባዛሩ የማጠቃለያ ስነ-ስርዐት ላይ ተገኝተዉ ለተሳታፊዎች የተሳትፎ የምስክር ወረቀት የሰጡት የአትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ምክትል ዋና ፀሐፊ ወ/ሮ ሔለን ረታ ባስተላለፉት መልዕክት የባዛሩ ተሳታፊዎች እርስ በርስ የምርትና አገልግሎት ተመጋጋቢነትን በማሳደግና ጠንካራ ትስስር በመፍጠር መስረት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል የንግዱ ማህበረሰብ ተወዳዳሪ ለመሆን የዲጅታል ማርኬቲንግ ግንዛቤዉን በማዳበር ከዘልማዳዊ የግብይት ስርዐት በመላቀቅ የእጅ ስልኮቻችንና ሌሎች ግብዓቶችን በመጠቀም ምርትና አገልግሎታችንን ማስተዋወቅና የመገበያየት ልምድ ማዳበር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
ማህበረሰቡም ኤግዚቢሽንና ባዛሮች በሚዘጋጁበት ወቅት ወደ ዝግጅቱ በመምጣት ጥራት ያላቸው ምርትና አገልግሎቶችን መገበያየት እንደሚጠበቅበት ተጠቁሟል፡፡

