የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል በንግድና ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ኩነቶችና ትዕይንቶች ላይ እንዲሳተፍ ማስተባበር እና ማገዝ ዋንኛው ነው።

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል የንግድ ማኅበረሰቡ በንግድና ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ኩነቶችና ትዕይንቶች ላይ እንዲሳተፍ ማስተባበር እና ማገዝ ዋንኛው ሲሆን ፤ በዚህም የንግድ ግንኙነቶችን በመፍጠርና ያሉትንም በማጠናከር በዓለም አቀፍ የገበያ ስርዓት ውስጥ እውቅናን እንዲያገኙ ማገዝ ነው።
ከዚህ ጋር በተገናኘም ዛሬ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የስራ ኃላፊዎች ከጣሊያን ኤምባሲ የንግድ ማስፋፊያ ክፍል (የጣሊያን ንግድ ኤጀንሲ) ጋር ውይይት አካሂደዋል ።
ውይይቱ በጣሊያን ሊካሄድ የታቀደው የ EIMA አለም አቀፍ የግብርና እና አትክልት ማሽነሪ ኤግዚቢሽን ላይ ኢትዮጵያውያን የግብርና ማሽነሪ አስመጪዎች እና አከፋፋዮችን በሰፊው ማሳተፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው፡፡
የሚካሄደው የንግድ ትርሂት በዘርፋ ያሉ የግሉ ዘርፍ ተዋንያን ከአቻ የንግዱ ማኅበረሰብ ጋር እንዲተዋወቁና የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ እንዲሁም ተሞክሮ እንዲለዋወጡ እና በጋራ የሚሰሩበት ሁኔታን በማመቻቸት ረገድ ሚናው ከፍ ያለ ነው ።
በመሆኑም ምክር ቤታችን ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ እና ለማስፋፋት በሚያደርገው ጥረት መሰል መድረኮችን ማዘጋጀት እንዲሁም ከላይ በተጠቀሰው አግባብ በሚዘጋጁ የንግድ ትርዒቶች ላይ የንግዱ ማኅበረሰብ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ መስራት አንኳር ተግባሩ በመሆኑ፤ አጠናክሮ የሚቀጥልበት ይሆናል።
ሰብስብ አባፊራ አባጆቢር
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት

