ሰብስብ አባፊራ አባጆቢር የፓን አፍሪካ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ሰራ አስፈፃሚ ሆነው ተመረጡ

ሰብስብ አባፊራ አባጆቢር የፓን አፍሪካ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ሰራ አስፈፃሚ ሆነው ተመረጡ
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ሰብስብ አባፊራ አባጆቢር የፓን አፍሪካ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ( Pan-African Chamber of Commerce and Industry) የስራ አስፈፃሚ በመሆን ተመረጡ።
የምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ በሞሮኮ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔው ነው ፤ ሰብስብ አባፊራ አባጆቢርን በስራ አስፈፃሚነት የመረጠው።
የምክር ቤቱ ፅ/ቤት የጠቅላላ ጉባዔውን ውጤቱ ባሳወቀበት መልዕክቱ እንደገለፀው:- በስራ አስፈፃሚነት መመረጥዎ የፓን አፍሪካ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ( Pan-African Chamber of Commerce and Industry) የጠቅላላ ጉባዔ አባላት በእርስዎ ላይ ያላቸውን እምነት የገለፁበት ብቻ ሳይሆን እርስዎ በአህጉራችን ንግድን፣ ኢንቨስትመንትንና የግሉን ዘርፍ ለማሳደግ እያከናወኑ ባሉት ተግባራት እንዲሁም በፕሬዚደንትነት እየመሩት ያለውን የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተልዕኮን ለማስፈጸም እያከናወኗቸው ላሉት የለውጥ ስራዎች በተጨማሪም እያሳዩት ላለው ቁርጠኝነት ማሳያ ነው ብሏል።
የፓን አፍሪካ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት አክሎም፤ ጠቅላላ ጉባዔው እርስዎን የስራ አስፈፃሚ አድርጎ በመምረጡ እንኳን ደስ ያልዎት ያለ ሲሆን ፤ በተቀመጡ የአሰራር ስረዓቶች መሰረትም የተመረጡበት አዲሱ የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት በቅርቡ ወደስራ የሚገባ ይሆናል ሲል መልዕክቱን አጠናቋል።
የፓን አፍሪካ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት (PACCI) በአፍሪካ ውስጥ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት እንዲሁም የአህጉራዊ ኢኮኖሚ ውህደትን ለማፋጠን እና የግሉ ዘርፍ ዕድገትን ለማጎልበት እንዲቻል በአህጉሪቱ የሚገኙ ብሔራዊ የንግድ ምክር ቤቶችንና ማኅበራትን በአንድ ጥላ ስር ያሰባሰበ ተቋም ነው።

