Mon - Fri: 8:30 - 05:30 PM
info@ethiopianchamber.com

Read more

Jul 08, 2026 .

የወጪ ንግድን ለማስፋፋት፣ ጥራት ያለው ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ስራዎች ቁልፍ ሚና አላቸው:- ሰብስብ አባፊራ አባጆቢር

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀነው  ከፍተኛ የወጪ ንግድና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መድረክ (High-Level Export and Economic Diplomacy Forum) በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በመድረኩም ከጉዳዩ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው የመንግስት ተቋማት ተወካዮች፣
ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት፣ የምክር ቤታችን የዴሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት፣ የድጋፍ ሰጪ እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ አድርገዋል።

እንደሚታወቀው፤ የወጪ ንግድን ለማስፋፋት፣ ጥራት ያለው ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ ቱሪዝምን ለማበረታታት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠን፣ የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትን ለማጠናከር እና ዘላቂ የስራ ዕድሎችን ለመፍጠር ሌሎች ወሳኝ ቅድመ ሁኔታዎች እንደተጠበቁ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ስራዎች ቁልፍ ሚና አላቸው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በፋይናንስ ዘርፍ፣ በኢንቨስትመንት ሥርዓት፣  በታክስ፣ በሎጂስቲክስ እና በአጠቃላይ እየተደረጉ ያሉ ማሻሻያዎች ለአገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች አዳዲስ ዕድሎችን እየፈጠሩ ሲሆን ግባቸውም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የማኑፋክቸሪንግ፣ የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የሎጂስቲክስ ማዕከል ማድረግ  ነው።

ይህንን ራዕይ ለማሳካትም በአገር ውስጥ በመንግስትም ሆነ በግሉ ዘርፍ እየተከናወኑ ካሉ ስራዎች ባሻገር የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ስራዎቻችንን የውጭ ግንኙነታችን ማዕከል የሚያደርግ አቀራረብ ያስፈልጋል።

የዛሬው መድረክ ዓላማም እነዚህን ግቦቻችንን የበለጠ ማስተሳሰር ሲሆን፤ በይበልጥም ከወጪ ንግድ አንፃር እየገጠሙን ያሉ ሁኔታዎችን ወደመልካም አጋጣሚ  የምንቀይርባቸው አስቻይ አሰራሮች ላይ ለመምከር ጎን-ለጎንም ልንከውናቸው በሚገቡ ቀጣይ ስራዎች  ላይ የጋራ አስተሳሰብ እንዲኖረን ለማድረግ ነው።

በመሆኑም  የምክር ቤታችንም ሆነ  የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ተልዕኮዎቻችን ግብ:- የኢትዮጵያን ወጪ ምርቶች ማስተዋወቅ ፣ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንትን መሳብ፣ የንግድ አጋርነት ማጠናከር ብሎም የወጪ ንግድ መረጃ ምንጮች መሆን  ነው።

በመሆኑም የኢትዮጵያ  የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲም  ሆነ የምክር ቤታችን  የንግድና ኢንቨስትመንት ማስፋፋት ተልዕኮዎች ለሚከተሉት ስትራቴጂያዊ  ቁልፍ ተግባራት ትኩረት  መስጠት ይኖርባቸዋል።

በመጀመሪያ፣ አዳዲስ የወጪ ገበያዎችን የመለየት እና እያጋጠሙ ያሉ እንቅፋቶችን  ከአገራት  ጋር በመመካከር ለማስወገድ ጥረት ማድረግ ፤ እንዲሁም  የንግድ ትስስሮችን ማመቻቸት እና የኢትዮጵያ ምርቶችንና አገልግሎቶችን ማስተዋወቅ።

ሁለተኛ፣  የምንስበው ኢንቨስትመንት ምርታማነትን የሚያሳድግ እና ወደ ወጪ ንግድ ያዘነበለ መሆን ይገባዋል ። በተጓዳኝም ኢንዱስትሪያሊዜሽንን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን፣ እሴት ጭማሪን፣ የሥራ ዕድል ፈጠራንና የውጭ ምንዛሬ ገቢን የሚያሳድግ ጥራት ያለው ኢንቨስትመንት  መሳብ የጋራ ግባችን መሆን አለበት።

በሦስተኛ ደረጃ:- ኤምባሲዎቻችን አስተማማኝ የገበያ መረጃዎችን በመሰብሰብና በማሰራጨት የኢትዮጵያ ላኪዎችና ባለሀብቶች ትክክለኛ የንግድ ውሳኔዎችን እንዲወስኑ ማገዝ አለባቸው።

አራተኛ፡- ዲፕሎማሲያችን በአስተናጋጅ ሀገራት ካሉ የንግድ ምክር ቤቶች፣ የንግድ ማህበራት፣ ባለሀብቶች፣ የፋይናንስ ተቋማትና አግባብ ካላቸው የመንግሥት ተቋማት ጋር ዘላቂ የንግድ አጋርነቶችን ለመፍጠር የሚያስችል  ትብብርን ማጠናከር ያለበት ሲሆን፤ ለዚህም ከምክር ቤታችን ጋር  በቅርበት መስራታችንን ማጠናከር ይኖርብናል።

በአምስተኛ ደረጃም:-  የኢኮኖሚ ማሻሻያዎቻችንን፣ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን፣ የወጪ ንግድ አቅምን፣ የቱሪዝም ሀብቶችን እና በተለይም በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ማዕቀፍ ውስጥ እያደገ ያለውን የኢትዮጵያ ሚና በብቃት ማስተዋወቅ መሆን ይኖርበታል ።

ከላይ ካስቀመጥኳቸው  እይታዎች ባሻገርም ፤ ከግሉ ዘርፍ አንፃር ንግዶቻችንን ከዓለም አቀፍ ገበያዎች ጋር በማስተሳሰር ወደተጨባጭ ስኬት የመቀየር ሚና የመጫወት ሚና ይኖረናል።

በመጨረሻም ከላይ ባስቀመጥኳቸው አበይት እይታዎችም ሆነ ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የተካሄደው የዛሬው ከፍተኛ የወጪ ንግድና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መድረክ (High-Level Export and Economic Diplomacy Forum) ዝርዝር ሁኔታዎችን ከነመፍትሄ አቅጣጫዎች የተወያይበት ብቻ ሳይሆን፤ የተቀመጡ የመፍትሄ ሀሳቦችን ወደመሬት ለማውረድ ቃል የገባንበትም ጭምር  ነው።

ሰብስብ አባፊራ አባጆቢር
የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Ethiopian Chamber of Commerce and Sectoral Associations

Contact Info

Mon - Fri : 8:00 AM - 05:00 PM
Sat : 8:00 - 06:00 PM
+251 115 514 005
info@ethiopianchamber.com
+251-115-517699
517

Office Address

Mexico Square, Addis Ababa, Ethiopia