የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ዋና ፀሐፊ ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክንና ነፃ የንግድ ቀጣናን ጎበኙ።

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ዋና ፀሐፊ ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክንና ነፃ የንግድ ቀጣናን ጎበኙ።
በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪ ፓርኩ ዉስጥ በሶስት ዘርፎች ማለትም በፓኬጂንግ ( ቀደም ሲል ከዉጭ ሲገባ የነበረዉን የሲሚንቶ ከረጢቶችንበማምረት)፣በተሽከርካሪና ጀነሬተሮችን በመገጣጠም ላይ የተሰማሩ አምራቾች በስራ ላይ መሆናቸዉን አይተዋል።
በተመሳሳይ በኢንዱስትሪ ፓርኩ ዉስጥ በተቋቋመዉ ነፃ የንግድ ቀጠና አስር የዉጭ አገራት ድርጅቶችና ሃያ ገደማ የሚሆኑ የአገር ዉስጥ የንግድ ድርጅቶች ቦታ መረከባቸዉንና አብዛኞቹ ወደ ስራ መግባታቸዉን በጉብኝቱ ወቅት ለማወቅ ተችሏል።

በነፃ የንግድ ቀጣናዉ ዉስጥ ግብይቱ የሚከናወነዉ በዉጭ ምንዛሪ በመሆኑ ለመንግስት የዉጭ ምንዛሪ ማግኛ ሲሆን አስመጪዎችና አከፋፋዮችም ዕቃ ለማምጣት ወደ ዉጭ ለመሄድ ሳይገደዱ በአገር ዉስጥ ካለዉ ነፃ የንግድ ቀጣና መግዛት እንደሚችሉና LC ለመክፈትም በቀጣናዉ ዉስጥ አራት ባንኮች በመኖራቸዉና ሌሎች ባንኮችም እየገቡ በመሆናቸዉ እንዲሁም የጉሙሩክ ጉዳዮችን እዚያዉ መጨረስ እንዲቻል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አስጎብኝዎቹ አስረድተዋል።
በተመሳሳይ ዋና ፀሐፊዉ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ደረቅ ወደብ እና ተርሚናልንም ጎብኝተዋል።
የደረቅ ወደቡን ያስጎበኙ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ኦፕሬሽን ማናጀር በተርሚናሉ የጉሙሩክ አገልግሎት እየተሰጠ ቢሆንም የገቢ ምርቶች ጥራትና ደህንነት ማረጋገጫ ላብራቶሪ በማዕከሉ አገልግሎት ባለመጀመሩና ናሙናዎች እየተወሰዱ ከተማ ተወስደዉ ስለሚሰሩ የተቀላጠፈ አገልግሎት እየተሰጠ አለመሆኑንና ይህም የንግዱን ማህበረሰብ ለእንግልት፣ ለምርቶች ያለአግባብ በወደቡ መቆየት ምክንያት መሆኑን ጠቁመዉ የሚመለከተዉ አካል አፋጣኝ የማሻሻያ እርምጃ እንዲወስድም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ዋና ፀሐፊ ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ ሁለቱም ተቋማት ለንግዱ ማህበረሰብ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠራቸዉንና ለአገር የኢኮኖሚ ዕድገት እያበረከቱ ያሉት አስተዋፅኦ ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል።
በድሬዳዋ ደረቅ ወደብና ተርሚናል የምርት ጥራትና ደህንነት ማረጋገጫ ላብራቶሪ አለመቋቋሙ የጉሙሩክ ጉዳይን ጨርሰዉ ዕቃዎችን ወደ መሃል አገር ገበያ ለማድረስ መዘግየትን እንደሚፈጥሩና ዕቃዎችን ለመጫን የሚላኩ ተሽከርካሪዎችም ለረጅም ጊዜ ስለሚቆሙ ለአላስፈላጊ ወጪ እየተዳረጉ መሆናቸዉን የንግዱ ማህበረሰብ በተደጋጋሚ የሚያነሳዉ ቅሬታ ስለሆነ መንግስ አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃ ሊወስድ ይገባልም ብለዋል።

