የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ያዘጋጀው በምስራቅ ኢትዮጵያ ኮሪደር ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ መከላከል ዙሪያ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሄደ::


የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ያዘጋጀው በምስራቅ ኢትዮጵያ ኮሪደር ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ መከላከል ዙሪያ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሄደ::
በመድረኩም ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ከጉምሩክ ኮሚሽን፣ ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ ከአዲስ አበባ ፣ ከሶማሌ ክልል፣ ከሀረሪ እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል የንግድ ቢሮዎች፣ የፌደራል ፖሊስን ጨምሮ ከጸጥታ ተቋማት፣ ከቁም እንስሳት ነጋዴዎች ማኅበርና ከሌሎች ማኅበራትና ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ፣ ህገ-ወጥ ንግድ ህጋዊ ነጋዴውን ከገበያ በማስወጣት በሀገሪቱ የንግድ ስርዓት ላይ ከባድ ጫና ከማድረጉም ባሻገር በሀገር ደህንነት ላይ ስጋት የሚደቅን አደገኛ እንቅስቃሴ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የምስራቅ ኢትዮጵያ ኮሪደር ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚካሄዱበት ዋናው አካባቢ እንደመሆኑና ካለው የጠረፍ ስፋት አንጻር ለመቆጣጠር አስቸጋሪ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸው ተገልጿል፡፡

በውይይት መድረኩ እንደ ቶባኮ ምርቶች ህገ-ወጥ ዝውውርና ስርጭት ፣ ጎማ እንዲሁም ከቁም እንስሳት ንግድ ጋር በተያያዘ የመወያያ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን ምክር ቤቱ በተለይም በጉዳዩ ዙሪያ ቀጥተኛ ባለቤት የሆኑ ተቋማትን ያሳተፈ ምክክር በማዘጋጀቱ ተሳታፊዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከል ለማኅበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን መስራት፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም፣ በተለያዩ ጸጥታ ተቋማትና ሌሎች አካላት መካከል በቅንጅት መስራት፣ ለህጋዊ ነጋዴው ማበረታቻዎችን መዘጋጀትና የሚወሳዱ እርምጃዎችን ማጠናከር እንደመፍትሄ መወሰድ እንዳለባቸውም ተነስቷል፡፡

