የየክልሎቻቸው የአመራርነት ኃላፊነት በመረከባቸው እንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላለፉ – ሰብስብ አባፊራ አባጆቢር

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሰብስብ አባፊራ አባጆቢር፤ የአማራ፣ የሶማሌ፣ የሲዳማ እና የጋምቤላ ክልሎች ምክር ቤቶች ባካሄዱት የመንግሥት ምስረታና የመክፈቻ ጉባኤ የየክልሎቹን ርዕሰ መስተዳድሮች መሰየም ተከትሎ፣ ክቡር አቶ አረጋ ከበደ፣ ክቡር አቶ ሙስጠፋ ሙሀመድ፣ ክቡር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ እና ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ የየክልሎቻቸው የአመራርነት ኃላፊነት በመረከባቸው እንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
ፕሬዚደንቱ በመልዕክታቸው ፤ ክልሎቻችሁ ያላቸውን ሰፊ የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የምርት አቅም በማሳደግ፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማጠናከር፣ የስራ ዕድልን በማስፋፋት እና ዘላቂና አካታች የኢኮኖሚ ዕድገትን በማፋጠን የሚጠበቅባችሁን ኃላፊነት በብቃትና በስኬት እንደምትወጡ ያለኝን እምነት እገልጻለሁ ብለዋል።
አክለውም የክልሎቻችሁን የኢኮኖሚ አቅም በተጨባጭ ውጤት ለመቀየር፣ የግሉን ዘርፍ እንደ ዋና የኢኮኖሚ እድገት አጋር በማጠናከር እና ለንግድና ለኢንቨስትመንት ምቹ፣ ተወዳዳሪና ቀልጣፋ የስራ አካባቢ በመፍጠር ረገድ የሚኖራችሁ አመራር ወሳኝ ነው።
በዚህ ረገድ፣ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፤ ከየክልሎቹ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ጋር በቅርበትና በተቀናጀ መልኩ በመስራት፣ ለግሉ ዘርፍ ምቹ የንግድ ስራ ከባቢ ለመፍጠር፣ ኢንቨስትመንትንና ንግድን ለማስፋፋት፣ የንግድና የኢኮኖሚ ትስስር ለማጠናከር እና የግሉ ዘርፍ ያለውን የልማት አስተዋጽኦ የበለጠ ለማሳደግ ያለውን ቁርጠኝነት ላረጋግጥ እወዳለሁ።
በመጨረሻም፣ ክቡራን ርዕሰ መስተዳድሮች፣ በአዲሱ የአመራር ዘመናችሁ ለሕዝቦቻችሁ እና ለክልሎቻችሁ የላቀ ውጤት የምታስመዘግቡበት፣ ለንግድና ለኢንቨስትመንት የተሻለ ዕድል የምትፈጥሩበት እና የኢኮኖሚ ዕድገትንና የስራ ዕድልን በሚያፋጥን መልኩ ውጤትን የምታስመዘግቡበት የስኬት ዘመን እንዲሆንላችሁ ከልብ እመኛለሁ ሲሉ አጠቃለዋል።

