የአዲስ ቻምበር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ከከተማው ንግድ ቢሮ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ።

የአዲስ ቻምበር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ከከተማው ንግድ ቢሮ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ዘላቂ፤ ጤናማ እና ተወዳዳሪ የንግድ ስርአት እውን በሚሆንበት ሁኔታ ላይ ተወያዩ።
ንግድ ምክር ቤቱና የከተማው ንግድ ቢሮ ቀልጣፋና አስተማማኝ የንግድ ስርአት እንዲጎለብት በጋራ በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡
በተለይም ከቅርብ ወራት ወዲህ ንግድ ምክር ቤቱ አደረጃጀቱን በወረዳና በክፍለ ከተሞች በመዘርጋት የንግዱን ማህበረሰብ የሚያጋጥሙ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በቀላሉ ለመረዳትና መፍትሄ ለመስጠት መቻሉን በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የምክር ቤቱ ፕረዚደንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ ናቸው፡፡
በዚህ የውይይት መድረክ ላይ አዲስ ቻምበር በዋና ጸሀፊው አማካኝነት በባለፉት ሶስት ወራት ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
በሪፖርቱ ከተካከቱት ነጥቦች መካከል ንግድ ምክር ቤቱ የንግድ ምክር ቤቱ በንግዱ ህብረተሰብ የሚነሱ ቅሬታዎችን ከሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ቢሮዎች ጋር በጋራ በመሆን እየፈታ መሆንን፤ የንግዱን ማህበረሰብ አቅም በመገንባት እያደረገ ያለውን ጥረት እንዲሁም የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረኮችን በማዘጋት አመቺ ህጎች፤ አሰራሮችና ፖሊሲዎች እንዲተገበሩ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ በዚህ መድረክ ላይ የከተማው ንግድ ቢሮ የአንድ አመት ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ተሳታፊዎች አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ የተሳተፉት የንግድ ቢሮው አመራሮች አጋርነት እንደ አንድ ቁልፍ መሳሪያ በመጠቀም የከተማው ንግድ ቢሮ ከአዲስ ቻምበር ጋር ይበልጥ ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
በተለይም የከተማው ንግድ ቢሮ በንግድ ግብይት ሰራተኞቹ አማካኝነት የንግዱ ማህበረሰብ የአዲስ ቻምበር አባል እንዲሆን በማድረግ በንግድ ዙርያ የሚነሱ ቅሬታዎችን በተደራጀ መልኩ ለማቅረብና ምላሽ ለማግኘት እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም የምክር ቤቱ ፕረዚደንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ እንደ ገቢዎችና የንግድ ቢሮዎች የመሳሰሉት በከተማዋ ውስጥ የሚገኙት የመንግስት ተቋማት ለንግድ ምክር ቤቱ የሚሰጠቱትን ድጋፍ አመስግነው እንዲህ አይነት ግንኙነቶችን በዘላቂነት ማስቀጠል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በተለያዩ ማህበራት ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ የንግድ ማህበራት በአዲስ ቻምበር አደረጃጀት ውስጥ ተካተው በንግድ ዙርያ የሚያጋጥማቸውን ችግሮች በቅንጅት መፍታት እንደሚችሉ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ (የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት)

