የጅማ እና አካባቢዋ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን 17ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በተሳካና ውጤታማ በሆነ ሁኔታ በማካሄድ አጠናቀናል።

የጅማ እና አካባቢዋ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን 17ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በተሳካና ውጤታማ በሆነ ሁኔታ በማካሄድ አጠናቀናል።
ጉባኤው ፤ የኦዲት እና የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት እንዲሁም የ2019 ዕቅድ ላይ በስፉት በመወያየት በሙሉ ድምፅ አድቋል።
በተጨማሪም፤ ምክር ቤቱን ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት የሚያገለግሉ ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲሁም ዘጠኝ የቦርድ አባላትን የመረጠ ሲሆን፤ ጠቅላላ ጉባኤው ለኦሮሚያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሁለት እጩዎችንም መርጧል።
በመሆኑም ፤ ለተመረጡት የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ናጂብ ከድር፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ኢንጂነር አሚን አባፊጣ እንዲሁም የቦርድ አባላት መልካምና ውጤታማ የሥራ ዘመን እንዲሆንላችሁ በኢትዮጵያና ኦሮሚያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች እና በራሴ ስም ከልብ እመኛለሁ።
በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት የምክር ቤቱን ተቋማዊ አቅም በማጠናከር፣ የአባላትን ጥቅም በማስጠበቅና የግሉን ዘርፍ ሚና በማሳደግ የሚጠበቅባችሁን ኃላፊነት በብቃት እንደምትወጡም እተማመናለሁ።
የተሰጣችሁን ኃላፊነት በሚጠበቀው ብቃት እና የንግዱ ማኅበረሰብ በሚፈልገው የአፈፃፀም ጀረጃ ልክ እንድትወጡም አስፈላጊውን ትብብር እና ድጋፍ ለማድረግና በቅርበትና በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆኔንም አረጋግጣለሁ።
በተጨማሪም ፤ ጉባኤው ለክልሉ ምክር ቤት በእጩነት እንድቀርብ ለጣለብኝ ከፍተኛ ኃላፊነት በዚሁ አጋጣሚ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
ይህም፤ በበለጠ ትጋት እንድሠራና ለኢትዮጵያ የንግድ ማኅበረሰብ እንዲሁም ለጅማና አካባቢዋ የግሉ ዘርፍ ዕድገትና ተወዳዳሪነት የበኩሌን ተጨማሪ አስተዋጽኦ እንዳደርግ አደራና ኃላፊነት የሰጠኝ በመሆኑ በድጋሚ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
በመሆኑም ፤ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የሚጠበቅብን ዋነኛ ተልዕኮ የምክር ቤቱን ተቋማዊ አቅምና አገልግሎት ማጠናከር፣ የአባላትን ጥቅምና መብት ማስጠበቅ፣ የንግድ ማኅበረሰቡን የጋራ ጥቅም ማስተባበር እንዲሁም የግሉ ዘርፍ በክልላዊና አገራዊ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን የእድገት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የኢንቨስትመንትና የተወዳዳሪነት ሚና ማሳደግ ነው።
እንዲሁም ፤ ምክር ቤቶች የአባላትን ጥቅም ከማስጠበቅ ባለፈም፣ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል የውይይትና የትብብር ድልድይ በመሆን፤ የንግድ ሥራ ከባቢውን ለማሻሻል የሚረዱ የፖሊሲ ማሻሻያ ሐሳቦችን ማቅረብ ሌላኛው የትኩረት አቅጣጫ ይሆናል።
ስለሆነም አዲሱ አመራር ከአባላት፣ ከባለድርሻ አካላትና ከሌሎች ተቋማት ጋር በቅርበት በመሥራት የምክር ቤቱን ተልዕኮ ወደ ተጨባጭ ውጤት እንደሚቀይር እምነቴ ነው።
በዚህ አጋጣሚም፤ የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከጅማና አካባቢዋ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን ጨምሮ በየደረጃው ከሚገኙ ከሁሉም ምክር ቤቶች ጋር በጋራ በመሥራት የንግድ ማኅበረሰቡን ጥቅም ለማስጠበቅ፣ የግሉን ዘርፍ ድምፅ ለማጠናከርና ለአገራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያበረክተውን ሚና ለማሳደግ ያለውን ቁርጠኝነት በድጋሜ ለማረጋገጥ እወዳለሁ።
የተከበሩ ሰብስብ አባፊራ አባጆቢር
የኢትዮጵያና ኦሮሚያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ፕሬዚዳንት

