1ኛው የኦሮሚያ ንግድ ምክር ቤት ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት በአዲስ አበባና በቢሾፍቱ ከተሞች ይካሄዳል፡- የተከበሩ ሰብስብ አባፊራ

ከ20 በላይ ሀገራትና ከ200 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚሳተፉበት 1ኛው የኦሮሚያ ንግድ ምክር ቤት ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት በአዲስ አበባና በቢሾፍቱ ከተሞች እንደሚካሄድ የኦሮሚያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አስታወቀ።
የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት የተከበሩ ሰብስብ አባፊራ አባጆቢር ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፤ 1ኛው የኦሮሚያ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት ከህዳር 24 እስከ 28 ቀን 2019 በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል፣ እንዲሁም ከታህሳስ 1 እስከ 3 ቀን 2019 በቢሾፍቱ ከተማ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
በንግድ ትርኢቱ ከ20 በላይ ሀገራት የኢንዱስትሪ ምርቶቻቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን፣ በክልሉ የሚገኙ ከ200 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎችም ይሳተፋሉ ብለዋል።
ዋና ዓላማው የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማሳለጥ፣ የሀገር ውስጥ አምራቾችና አገልግሎት ሰጪዎች ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ሰፊ ግንኙነት እንዲፈጥሩ ማስቻል መሆኑን ተናግረዋል።
በኮንስትራክሽን ዕቃ አቅራቢዎች፣ በግንባታ ድርጅቶችና በሪል እስቴት አልሚዎች መካከል የገበያ ትስስር እንደሚፈጠርም ፕሬዚደንቱ አብራርተዋል።
በተጨማሪም አምራች ፋብሪካዎች፣ ዩኒየኖችና የህብረት ሥራ ማህበራት የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶቻቸውን በብዛት በማቅረብ፣ በማምረቻ ዋጋ ለሸማቾች እንዲሸጡ በማስቻል የኑሮ ውድነትን ጫና ለማቃለል መታለሙን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም ከ18 በላይ በሚሆኑ የዓለም ሀገራት በተዘጋጁ ኤክስፖዎች ላይ የኢትዮጵያን የንግድ ማህበረሰብ በማሳተፍና በሀገር ውስጥ ባዛሮችን በማዘጋጀት፣ ለክልሉና ለሀገሪቱ ነጋዴዎች ዘላቂ የገበያ ትስስር ሲፈጥር መቆየቱን አስታውሰዋል።
በዚህ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት ላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች፣ በክልሉ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች፣ የግብርና ዘርፍ ተዋናዮች እንዲሁም ሁለገብ የንግድና የኢንቨስትመንት ድርጅቶች ተሳትፈው ምርትና አገልግሎታቸውን እንደሚያስተዋውቁና ልምድ ይለዋወጣሉ ይጠበቃል ብለዋል።
የንግዱ ማህበረሰብና ሸማቹ ህዝብ በተጠቀሱት ቀናት በአዲስ አበባና በቢሾፍቱ ከተሞች በመገኘት የንግድ ትርኢቱን እንዲጎበኙም ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።
የንግድ ትርኢቱ በኦሮሚያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከኦሮሚያ ኢንዱስትሪና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ጋር በመተባበር የሚዘጋጁት መሆኑ ተገልጿል።
