በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና በክልሉ ገቢዎች ቢሮ በጋራ የተዘጋጀ የግሉ ዘርፍና የመንግስት ባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ተከናወነ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እና በክልሉ ገቢዎች ቢሮ በጋራ የተዘጋጀ የግሉ ዘርፍና የመንግስት ባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ተከናወነ።
በመድረኩም ለአርባ ምንጭ ከተማ መሠረት ልማት መስፋፋት የንግዱ ማህበረሰብ የድርሻውን እንዲያጠናክር ተጠየቀ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ቦጋለ ቢታኔ ለ3ኛ ጊዜ በተካሄደው በዚህ የምክክር መድረክ የንግድ ሐሳቦችን በዘመናዊ መንገድና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ እንዲሁም የንግዱ ማኅበረሰብ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የዘጠና ቀን ዕቅድ መያዙን ጠቁመው የተነሱ ጥያቄዎችና ሀሳቦች ህግና ስርአትን በጠበቀ መልኩ ምላሽ እንዲያገኙ በንቃት እንደሚከታተሉና እንደሚያስፈፅሙ አስታውቀዋል።
መድረኩ የንግዱ ማኅበረሰብና መንግሥት በቅንጅትና በታማኝነት በመሥራት ለኅብረተሰቡ የሚያስፈልጉ የመሠረተ ልማት ሥራዎች እንዲጠናከሩ በሚያስችሉ ሐሳቦች ዙሪያ ማብራሪያ የተሰጠበት ሲሆን፣ ፍትሐዊ የግብር አሰባሰብ ሥርዓትን ማጠናከር እና ከመንግስታዊ መዋቅሩ ጋር በተግባቦትና በቅርበት መስራት ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡

በአርባ ምንጭ ከተማ ለሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ስራዎች መጠናከር የንግዱ ማህበረሰብ ድርሻው የጎላ መሆኑን የከተማው ከንቲባ ኢንጂነር ሃብታሙ መለሰም (ዶ/ር) አስገንዝበዋል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንድማገኝ ደግፌ በወቅቱ እንደተናገሩት፣ በግብይት ወቅት ደረሰኝ መስጠትና መቀበል ግዴታ ነው፡፡
የንግዱ ማኅበረሰብ ግብርን በታማኝነት የመክፈል የዜግነት ግዴታ መሆኑን በሚገባ ተረድቶ ይህንኑ ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ ኢንጂነር ሀብታሙ መለሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትና የንግዱ ማህበረሰብ በከተማዋ የሚከናወኑ የመሠረተ ልማት ሥራዎች እንዲጠናከሩ የጀርባ አጥንት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የከተማዋን ዕድገት ለማፋጠንና የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለመሥራት የንግዱ ማኅበረሰብ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመው፣
የንግዱን ዘርፍ ምቹ ለማድረግ እንደሚሠራ አመልክተዋል፡፡
ጠንካራ ከተማ ለመገንባት ጠንካራ ገቢ መፍጠርና ፍትሐዊ በሆነ መልኩ በታማኝነት ግብር መክፈል ወሳኝ መሆኑን ከንቲባው አስገንዝበዋል።
ሕገ-ወጥ ንግድን መግታትና ፈጣን አገልግሎት መስጠት፣ ደረሰኝ ሳይሰጡ ግብይት መፈጸምን ጨምሮ ሕገ-ወጥ የንግድ ሥራዎችን ለመግታት በሕጋዊ መንገድ መሥራት እንደሚያስፈልግ ከንቲባው ገልፀው በመድረኩ የተነሱ የመልካም አስተዳደርና በርካታ ጥያቄዎችን እታች ወርዶ በመፈተሽ በጋራ ለመፍትሄ ለመስራት ቃል ገብተዋል።
እንዲሁም የሥራ ባህልን በማሻሻል ለከተማው ዕድገት ፈጣን አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ የተነሱ ጥያቄዎችን በ90 ቀናት ምላሽ ለመስጠት በንግድ ምክር ቤቱና በባለድርሻ አካላት ቅንጅት ውጤቱን ለመገምገም በመስማማት ተጠናቋል። ( የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት)
