የኢትዮ- ናይጄሪያ የቢዝነስ ፎረም በናይጄሪያ አቡጃ ተካሂዷል።

በናይጄሪያ የንግድ ፣ ኢንዱስትሪ፣ማዕድንና ግብርና ምክር ቤት(NACCIMA)፣ በኢትዮዽያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እና በአቡጃ የኢፌዴሪ ኢምባሲ በጋራ ያዘጋጁት ኢትዮ- ናይጄሪያ የቢዝነስ ፎረም በአቡጃ ንግድና ኢንዱስትሪ ም/ቤት የስብሰባ አዳራሽ ተካሂዷል።
በፎረሙ ላይ ከናይጄሪያ በኩል የናይጄሪያ የንግድ ፣ ኢንዱስትሪ፣ማዕድንና ግብርና ምክር ቤት አባላት የሆኑት እና የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ማለትም የግብርና፣ የማኑፋክቸርንግ፣ የማዕድን ልማትና የአገልግሎት ዘርፎችን የሚወክሉ ባለድርሻ አካላት በአካል እና በዲረ-ገፅ አማካኝነት የተሳተፉ ሲሆን በአገራችን በኩል የኢትዮዽያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ም/ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ዓይናለም አባይነህ ፣ የም/ቤቱ ፀሐፊ የሆኑት ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ እና የሚሲዮኑ ባልደረቦች ተሳትፈዋል።
በፎረሙ ላይ የNACCIMA ፕሬዛዳንት ዶ/ር ኢንጂነር ጃኒ ኢብራሂም፣ የኢትዮዽያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዓይናለም አባይነህ ፣ የም/ቤቱ ፀሐፊ ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ እና ም/ሚሲዮን መሪ ክቡር አምባሳደር ኢሳያስ ጎታ ባስተላለፉት መልእክት በሁሉቱ አገሮች መካከል ስላለው ታሪካዊ ግንኙነት ፣በየአገሮቹ ስላሉትምቹ የቢዝነስና ኢንቨስትመንት ሁኔታዎችንና እምቅ አቅሞች እና እነዚህን አቅሞች ለጋራ ጥቅም እውን በማድረግ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የቢዝነስና የኢኮኖሚ ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ርብርብ እንዲደረግ ጥሪ አስተላልፈዋል።የB2B ምክክሮችም ተደርገዋል።
የኢትዮዽያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት የስራ ሃላፊዎች በአቡጃ ቆይታቸው የንግድ ም/ቤቶች ስለተቋቋሙበት ዋነኛ ዓላማ ስለሆኑት ስለፖሊሲ አዲቮካሲ፣ ስለተቋም አስተዳደር፣ ስለአገልግሎት አሰጣጥ እና ስለፐቢሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የሚያስችሉ ውይይቶችን ከNACCIMA የስራ ሃላፊዎች ጋር ያደረጉ ሲሆን በአቡጃ ውስጥ የመስክ ጉብኝቶችን
አድረገዋል፡፡



